በርሃብ የከሱ ሁለት እስራኤላውያን ታጋቾች ቪድዮ መለቀቁ ከምዕራባውን መሪዎች ትችት አስነሳ

ሰውነቱ የከሳው ኤቭያታር ዴቪድ

የፎቶው ባለመብት, Other

በጋዛ ታግተው የሚገኙ እና በርሃብ ሰውነታቸው የከሳ ሁለት እስራኤላውያንን የሚያሳይ ቪድዮ በታጋቾቻቸው መለቀቁ ከምዕራባውያን መሪዎች ወቀሳን አስነሳ።

ቀይ መስቀል በበኩሉ ለታገቱ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ የሚችልበት መንገድ እንዲመቻችለት ጥሪ አቅርቧል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፤ "ለፕሮፓጋንዳ እየተለቀቁ ያሉ የታጋቾች ምስሎች አስጸያፊ ናቸው" ያሉ ሲሆን እስራኤላውያኑ "ያለ ቅድመ ሁኔታ" መለቀቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እነዚህ ጥሪዎች የቀረቡት፤ እስራኤላዊው ታጋች ሮም ብራስላቭስኪ ከስቶ እና መመንመኑን የሚያሳይ ቪዲዮ ሐሙስ ዕለት በ'ፓለስቲኒያን ኢስላሚክ ጂሃድ' ከተለቀቀ እንዲሁም ሀማስ የሌላኛው ታጋች ኤቭያታር ዴቪድን በረሃብ የመነመነ ሰውነት የሚያሳይ ምስል ቅዳሜ ዕለት ካሰራጨ በኋላ ነው።

የእስራኤሉ መሪዎች ሀማስ ታጋቾችን እያስራበ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

የሀማስ የጦር ክንፍ በበኩሉ ሆነ ብሎ ታጋቾችን እያስራበ ነው የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጓል። ቡድኑ፤ በጋዛ የርሃብ ቀውስ መከሰቱን በመጥቀስ ታጋቾች፤ ታጣቂዎች እና ህዝቡ የሚመገቡትን እየተመገቡ ነው ብሏል።

ከጋዛ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ እሁድ ዕለት የእስራኤል ወታደሮች በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች እርዳታ ፍለጋ ላይ በነበሩ ፍልስጤማውያን ላይ ተኩስ ከፍተዋል። በዚህም ቢያንስ 27 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎች አስታውቀዋል።

የእስራኤላውያኑ ታጋዮች የሆኑት የ21 ዓመቱ ብራስላቭስኪ እና የ24 ዓመቱ ዴቪድ ከኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ታፍነው የተወሰዱት ሀማስ መስከረም 26/ 2016 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ነው።

ሁለቱ ግለሰቦች፤ መጀመሪያ ከታገቱት 251 ሰዎች እና እስራኤል አሁንም ድረስ በጋዛ ውስጥ ታግተዋል ብላ ከምትጠቅሳቸው 49 ታጋቾች መካከል ናቸው። ከ49ኙ እስራኤላውያን ውስጥ 27 ያህሉ ታጋቾች እንደሞቱ ይታመናል።

ቪዲዮዎቹ ከተለቀቁ በኋላ ከሁለቱ የታጋቾች ቤተሰቦች ጋር የተነጋገሩት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፤ "ከባድ ድንጋጤ" እንዳደረባቸው ገልጸዋል። ሁሉንም ታጋቾች ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት "በቀጣይነትና ያለማቋረጥ እንደሚቀጥል" ነግረዋቸዋል።

ኔታንያሁ እሁድ ዕለት በቀጣናው ከሚገኘው ቀይ መስቀል ኃላፊ ጋር ባደረጉት ንግግር፤ ተቋሙ ለታጋቾቹ ምግብ እና የህክምና እንክብካቤ ለማቅረብ በአስቸኳይ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ "የታገቱት ሰዎች ለህይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ" በሰጡት ቪድዮዎች "መደንገጡን" ተናግሯል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ፤ ታጋቾች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ፣ የህክምና ድጋፍ ለመስጠት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት የሚችልበት መንገድ እንዲመቻችለት በድጋሚ ጥሪውን አቅርቧል።

የሀማስ የጦር ክንፍ የሆነው አል አቃሳም ብርጌድስ በበኩሉ፤ ወደ ጋዛ የሚሄዱ ሰብአዊ ኮሪደሮች መደበኛ እና ቋሚ ሁኔታ ከተከፈቱ እንዲሁም በእርዳታ ክፍፍል ጊዜ የአየር ድብደባው ከተቋረጠ፤ ለእስረኞች ምግብ እና መድኃኒት ለማድረስ ለሚቀርብ ማንኛውም የቀይ መስቀል ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።

እስራኤላዊው ታጋች ሮም ብራስላቭስኪ

የፎቶው ባለመብት, Other

የቀይ መስቀል ድርጅት፤ በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን ለመርዳት አልቻለም በሚል በእስራኤል ከፍተኛ ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል።

ከተለቀቁት ቪድዮዎች በአንዱ ላይ፤ ብራስላቭስኪ ምግብ እና ውሃ እንደጨረሰ እንዲሁም በዚያ ቀን ሶስት "የፋላፍል ቁርጥራጮችን" ብቻ እንደበላ በለቅሶ ሲናገር ይታያል። መቆምም ሆነ መራመድ እንደማይችል እና "በሞት ደጃፍ ላይ" መሆኑንም ገልጿል።

በሁለተኛው ቪዲዮ የሚታየው ዴቪድ ደግሞ፤ "ለቀናት ምግብ አልበላሁም... የሚጠጣ ውሃ እንኳን አላገኘሁም" በማለት ሲናገር እና መቃብሩ እንደሚሆን የገለጸውን ጉድጓድ ሲቆፍር ይታያል።

የጀርመን ቻንስለር ፍሪድሬክ ሜርስ በምስሎቹ "እንደተደናገጡ" ገልጸው፤ የታጋቾች መለቀቅ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ለሚፈጸም ተኩስ አቁም አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሀማስ "አሰቃቂ ጭካኔን" እንደሚያንጸባርቅ የገለጹት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ፤ ሀገራቸው ታጋቾችን ለማስለቀቅ፣ ተኩስ አቁምን ለማስፈን እና ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ለማስቻል ያለመታከት መስራቷን እንደቀጠለች ተናግረዋል።

ይህ ጥረት፤ "እስራኤል እና ፍልስጤም በሰላም ጎን ለጎን የሚኖሩበትን" የሁለት ሀገር መፍትሄን በሚያመጣ የፖለቲካ መፍትሄ ሊታጀብ እንደሚገባ ተናግረዋል። በቅርቡ ፈረንሳይን ጭምሮ ካናዳ እና ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠችው ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና የመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።