እስራኤል በጋዛ ከተማ ወረራ እቅዷ ላይ የተሰነዘረባትን ዓለም አቀፍ ትችት ውድቅ አደረገች

የጋዛ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Mahmoud Abu Hamda/Anadolu via Getty Images

የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማ ወረራ እቅድን ማጽደቁን ተከትሎ ከአለም መሪዎች እየተሰነዘሩ ያሉ ትችቶችን እስራኤል ውድቅ አድርጋ ወረራውን እንደምትገፋበት አስታወቀች።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እስራኤልን የሚያወግዙ እና በማዕቀብ የሚያስፈራሩ አገራት "ከአቋማችን አያነቃንቁንም" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ጠላቶቻችን አንድ ጠንካራ በጽኑ ኃይል የምንመልስ ሆነው ያገኙናል" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ87 በላይ የጋዛ ሰርጥ እስራኤል ወታደራዊ ቀጣና እንዳደረገችው ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።

የእስራኤል የጋዛ ከተማን የመውረር እቅዷ ተመድን ጨምሮ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ ባሉ አገራት ውግዘትን አስከትሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ጀርመን ወደ እስራኤል የምትልከውን የጦር መሳሪያዎች እንድታቆም ምክንያት ሆኗል።

ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት እና ከጋዛ አስተዳዳሪነቱ ማስወገድን ጨምሮ አምስት መርሆዎችን ይዟል የተባለው ጦርነቱን የመቋጨት እንዲሁም የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድ የጸደቀው አርብ ዕለት ነው።

የእስራኤል መከላከያ ጦርነቱን ለመቋጫት መርሆዎች ያላቸውንም ዘርዝሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አምስቱ ተብለው የተዘረዘሩት ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ ሁሉንም ታጋቾች መመለስ (በሕይወት ያሉ እንዲሁም የሞቱትን አስከሬኖቻቸውን)፣ የጋዛ ሰርጥን ከወታደራዊ ትጥቅ ነጻ ማድረግ፣ ጋዛን የሚያስተዳድረውን ሐማስን በማስወገድ እንዲሁም ዌስት ባንክን ከሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ውጪ የሆነ አማራጭ የሲቪል መንግሥት ምሥረታን ያካተተ ነው።

እቅዱ መጀመሪያ ላይ የጋዛ ከተማን ሙሉ ወረራ በመፈጸም አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያንን ወደ ደቡባዊ ግዛቶች ማፈናቀል ላይ ያተኮረ መሆኑን የእስራኤል ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው አስፍረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኙ የስደተኛ ካምፖችን እንዲሁም ታጋቾች አሉባቸው የሚባሉ ስፍራዎችን ይወራሉ ተብሏል።

ከሳምንታት በኋላ ሁለተኛ ዙር ጥቃቷን እስራኤል እንደምትጀምር የተገለጸ ሲሆን፤ የሰብዓዊ እርዳታዎች እንደሚገቡ ሚዲያዎቹ ዘግበዋል።

የእስራኤል የጋዛ ወረራ እቅድ ማጽደቋ በአገሪቱ ከሚገኙ አንዳንድ ወታደራዊ ባለስልጣናትን ጨምሮ በጋዛ ቤተሰቦቻቸው ከታገቱ አካላት ተቃውሞ ገጥሞታል።

ሐማስ የጋዛ ከተማን ወረራ እቅድ "አዲስ የጦር ወንጀል" ሲል ያወገዘው ሲሆን "ይህም [እስራኤልን] ዋጋ የሚያስከፍል ነው ብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የኒውዚላንድ እና የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች "እቅዱን ውድቅ" የሚያደርግ የጋራ መግለጫ አርብ ዕለት አውጥተዋል።

አገራቱ የጋዛን ቀዉስ "የበለጠ የሚያከፋ ነው" ሲሉም አቋማቸውን አስታውቀው፤ የጋዛን ግዛት "የመጠቅለልም ሆነ ወይም ሰፈራን የማስፋፋት ሙከራዎች አለም አቀፍ ህግን ይጥሳል" ሲሉ ተችተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ተርክ የጋዛ ወረራ ዕቀድ "ለከፋ የግዳጅ መፈናቀል፣ ለበለጠ ግድያ፣ መቋቋም ለማይቻል ስቃይ፣ ለከፉ ውድመቶች እና አሰቃቂ ወንጀሎች" የሚዳርግ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል አብዛኛውን የጋዛ ሰርጥን ተቆጣጥራ የምትገኝ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት 87 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ቀጣና ወይም ጋዛውያን በአስገዳጅ የሚፈናቀሉባቸው ቦታዎች እንደሆኑ አስታውቋል።

ለጥቂት ጊዜ የቆየው የተኩስ አቁም መጋቢት ወር ላይ መፍረሱን ተከትሎ እስራኤል ሁሉንም የድንበር አካባቢዎች "አደገኛ የውጊያ ቀጣና" በሚል ፈርጃ በቀጣዮቹ ወራት እነዚህ ቀጣናዎች እየሰፉ መጥተዋል።

በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል። አንዳንዶች በተደጋጋሚ የተናፈናቀሉ ሲሆን በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።

የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ከዚህ ቀደም ተዘግቦ ነበር።

በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ ተገልጾ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ያለውን ሰፈራ በማፍረስ በአውሮፓውያኑ 2005 ጦሯን አስወጥታ ነበር።

ሆኖም ከግብፅ ጋር በጋራ በመሆን የጋዛን ፀጥታ እና መዳረሻ ተቆጣጥራ ትገኛለች።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።