በወሲባዊ ትንኮሳ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ በስህተት ከእስር ቤት ተለቅቆ በዩኬ ፖሊስ እየታደነ ነው

ሀዱሽ ገብረሥላሴ

የፎቶው ባለመብት, Essex Police

የምስሉ መግለጫ, ሀዱሽ ገብረሥላሴ

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በአንዲት ታዳጊ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽሟል ተብሎ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ በስህተት ከእስር ቤት ተለቅቆ በፖሊስ እየተፈለገ ነው።

ሀዱሽ ገብረሥላሴ የተባለው ኢትዮጵያዊ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በሕገወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከገባ በኋላ በ14 ዓመት ታዳጊ ላይ በፈጸመው ወሲባዊ ትንኮሳ ነበር ለእስር የተዳረገው።

ከፈረንሳይ በትንሽዬ ጀልባ ተሳፍሮ ወደ ዩኬ የገባው ሀዱሽ ኤፒንግ ከተማ ውስጥ ፈጽሞታል በተባለው ወንጀል በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ መስከረም አጋማሽ ላይ የአስራ ሁለት እራት እስር ተፈርዶበት ሳለ ነው በስህተት ከእስር መለቀቁ የታወቀው።

ግለሰቡ ከእስር ቤት መውጣቱን በተመለከተ መጀመሪያ ላይ የዘገበው 'ዘ ሰን' የተባለው ጋዜጣ ሲሆን፣ መልሶ ለመያዝ ፖሊስ አሰሳ እያካሄደ ነው።

የእስር ቤት ምንጮች እንዳሉት ሀዱሽ ከታቀደለት ከዩናይትድ ኪንግደም የመባረር ውሳኔ በፊት ወደ ስደተኞች የማቆያ ማዕከል ሊላክ ነበር።

የኢትዮጵያዊውን እስረኛ ከእስር መውጣት ተከትሎ የእስር ቤቶች አስተዳደር ስለክስተቱ ምርመራ የጀመረ ሲሆን፣ አንድ የፖሊስ መኮንን ምርመራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ውጪ እንዲሆን ተደርጓል።

ሀዱሽ በቀረበበት ክስ ምክንያት በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ይኖርበት ከነበረው የስደተኞች መቆያ ሆቴል ውጪ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር እስከ መጋጨት የደረሱባቸው የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገው ነበር።

ሀዱሽ ሰኔ መጨረሻ ገደማ አንዲት ታዳጊን ለመሳም መሞከሩ እና በርካታ ወሲብ ነክ ንግግሮችን መናገሩ ባለፈው መስከረም ወር ለተሰየመው ፍርድ ቤት ተገልጾ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተከታዩ ቀን ደግሞ ታዳጊዋን በድጋሚ አግኝቶ ወሲባዊ ትንኮሳ ከመፈጸሙ በፊት ሊስማት ሞክሯል። በተጨማሪም የሥራ ማመልከቻ በመጻፍ ሥራ እንዲያገኝ ልትረዳው በነበረች ሴት ላይ ወሲባ ትንኮሳ መፈጸሙን የሚገልጽ ክስ ለፍርድ ቤት ቀርቧል።

በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ የተባለው ሀዱሽ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ የአንድ ዓመት እስር እና ወሲባዊ ጥቃት እንዳይፈጽም ለመከላከል ለአምስት ዓመታት ማንኛዋንም ሴት እንዳይቀርብ ዕግድ ተጥሎበታል።

በተጨማሪም ለአስር ዓመታት በወሲባዊ ጥቃት ፈጻሚዎች መዝገብ ላይ ሰፍሮ በየጊዜው እንዲፈርም ትዕዛዝ ተላልፎበታል።

የእስር ቤቶች አገለግሎት ቃል አቀባይ እንዳሉት "ፍርደኛው በስህተት ከተለቀቀ በኋላ በአስቸኳይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ ከፖሊስ ጋር እየሠራን ነው"።

"ኅብረተሰቡን መጠበቅ ቀዳሚ የምንሰጠው ጉዳይ በመሆኑ እስረኛው እንዴት ለእስር ቤት ሊወጣ እንደቻለ ለማወቅ ምርመራ ጀምራናል።"

የዩናይትድ ኪንግደም የፍትሕ ሚኒስት ዴቪድ ላሚ ፍርደኛው ከነበረበት እስር ቤት በወጣበት ሁኔታ "በእጅጉ ማዘናቸውን" ገልጸዋል።

ላሚ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት "ግለሰቡ በአስቸኳይ እንዲያዝ ከፖሊስ ጋር እየሠራን ሲሆን፣ በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ምርማራ እንዲደረግ አዝዣለሁ።

"ሀዱሽ በእኛ ጎዳናዎች ላይ መቆየት የለበትም፤ ለፈጸመው ወንጀል ከአገር መባረር አለበት" ሲሉ ሚኒስትሩ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

አካባቢውን ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት ማሪ ጎልድማን እንዴት ግለሰቡ በስህተት ሊለቀቅ እንደቻለ ይፋዊ ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

"ይህ የወከልኩትን ሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ የሚዳርግ በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው" ያሉት የፓርላማ አባሏ፣ "ከእስር ቤት አገለግሎት መልስ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

የወግ አጥባዊ ፓርቲ መሪዋ ኬሚ ባዴኖች "በሌበር ፓርቲ ስር ያለው የአገሪቱ አጠቃላይ ሥርዓት እየፈረሰ ነው" በማለት የእስረኛውን ማምለጥ ተቀናቃኛቸው ገዢ ፓርቲ ለመውቀስ ተጠቅመውበታል።

የሪፎርም ዩኬ ፓርቲ መሪ የሆኑት ናይጀል ፋራጅ በበኩላቸው "[ሀዱሽ] አሁን በኢሴክስ ከተማ ጉዳናዎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ነው። ብሪታኒያ ችግር ላይ ናት" ገዢውን ፓርቲ ወርፈዋል።

በወሲባዊ ትንኮሳ የተከሰሰው የኢትዮጵያዊው ሀዱሽ ጉዳይ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች የቀሰቀሰ ከመሆኑ፣ አሁን ከእስር ቤት በስህተት መለቀቁ ደግሞ ፖለቲከኞች በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ገዢውን ሌበር ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት ነው።