በዩኬ በወሲባዊ ጥቃት የተከሰሰው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የ12 ወራት እስራት ተፈረደበት

ሀዱሽ ቅባቱ

በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢሴክስ ግዛት ኤፒንግ ከተማ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ቅባቱ በቀረበበት ወሲባዊ ትንኮሳዎች ክስ የ12 ወራት እስራት ተፈረደበት።

ዛሬ በዋለው ችሎት ስደተኛው ሀዱሽ የ12 ወራት እስራት ውሳኔ ተላልፏል።

የኮልቸስተር ከተማ ፍርድ ቤት ነሐሴ 29/ 2017 ዓ. ም. በዋለው ችሎት ሀዱሽን በ14 ዓመት ታዳጊ እንዲሁም አዋቂ ሴት ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎችን በማድረስ ጥፋተኛ ነው ማለቱ ይታወሳል።

ብይኑን ያስተላለፉት ዳኛ፣ ሀዱሽ እንግሊዘኛ እንደማይችል በመጥቀስና የአእምሮ ጤና እክል እንደገጠመው በመናገር ስለ ጥፋቱ ለመናገር "ዳተኛ" ነበር ብለዋል።

"ደጋግመህ አልቅሰሀል፣ ሀፍረት ተሰምቶኛልም ብለሀል ጥፋተኛነት የሚሰማህና ያፈርከው በፈጸምከው ድርጊት ሳይሆን ድርጊትህ አንተ ላይ ባሳደረው ጫና ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

"14 ዓመቷ እንደሆነ አውቀህ ነበር። እሷም ነግራሀለች። እሷና ጓደኞቿ የደንብ ልብስ መልበሳቸውንም አይተሀል" ሲሉም ዳኛው አክለዋል።

ዳኛው "ታዳጊዋ ያሳየኸውን ባህሪ እንደማትፈልገው ግልጽ ብታደርግልም አንተ ግን ታዳጊዎቹን ከመከታተል አልታቀብክም" ብለዋል።

ሀፍቱ ወሲባዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባት የተገለጸው ሌላዋ አዋቂ ሴትን በተመለከተም ዳኛው "ድርጊትህን እንድትፈጽም የሚጠቁም ምንም ነገር አላለችም። በችላ ባይነትና በስሜታዊነት ነው ድርጊቱን የፈጸምከው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትንኮሳው የተፈጸመባት ሴት ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካል በመውሰዷም ምስጋና አቅርበዋል።

ዳኛው "ድርጊትህ ለሴቶች ያለህን ንቀት ያሳያል" ሲሉም ብይኑን ከማስተላለፋቸው በፊት ተናግረዋል።

"ለራሷ መብት የቆመች ጠንካራ ሴት ናት። ከሷ በባሰ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆነችውም ታዳጊም ከለላ ሆናለች" ብለዋል።

በዛሬው የችሎት ውሎ ዐቃቤ ሕግ በሀዱሽ ወሲባዊ ትንኮሳ የደረሰባትን የ14 ዓመት ታዳጊ ምስክርነት በፍርድ ቤት አቅርቧል።

"ከጓደኞቼ ጋር በወጣሁ ቁጥር ወደኋላ ዞር እያልኩ አያለሁ። የትምህርት ቤት የደንብ ልብሴን እለውጣለሁ። የደንብ ልብሴን ስለብስ የተጋለጥኩ ያህል ይሰማኛል" ማለቷን ገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ ስቱዋርት ኮወን እንዳሉት ሀዱሽ "የዩኬ ሕግ ይሄንን ያህል ጥብቅ መሆኑን አላወቅኩም ነበር" ብሏል።

የተከሳሹ ጠበቃ ሞሊ ዲያስ ሀዱሽ "ከዚህ ቀደም ጥፋት አልፈጸመም። ዩኬ ለመድረስ ባለፈባቸው የአውሮፓ አገራት ሲያልፍም ምንም አላጠፋም" ብለዋል።

ተከሳሹ "ከባድና ረዥም መንገድ ተጉዞ" ወደ ዩኬ እንደደረሰ ጠቅሰው "ፍላጎቱ በፍጥነት ከዩኬ መባረር ነው" ብለዋል።

ተከሳሹ የአእምሮ ጤናው እክል እንደገጠመውም ጠቅሰዋል።

ሀዱሽ በኤፒንግ ከተማ ማዕከል ተቀምጠው ከነበሩ ሁለት የ14 ዓመት ታዳጊዎች መካከል አንደኛዋን መነካካቱን እንዲሁም ልጅ መውለድ እንደሚፈልግ ተናግሯል ተብሏል።

ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች ማድረስን ጨምሮ አምስት ክሶች የቀረቡበት ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ገብረሥላሴ ቅባቱ ጋር ተያይዞ ባረፈበት 'ዘ ቤል' በተሰኘው የጥገኛ ጠያቂዎች ሆቴል አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ሀዱሽ ነሐሴ ላይ ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ በታዳጊዋ ልጅ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳን በማድረስ፣ ህጻንን ለወሲባዊ ድርጊት በማነሳሳት እንዲሁም በወሲባዊ ጥቃት ሙከራ ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን ዳኛው የእስር ቅጣት እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀው ነበር።

ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የገባው ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር የዋለውም ከስምንት ቀናት በኋላ ሐምሌ 1 ነበር።

ከአገሩ ከወጣ ዓመታትን እንዳስቆጠረ ከሰሞኑ በነበረውለችሎት ያስረዳው ሀዱሽ በሊቢያ አቋርጦ ወደ ጣሊያን ከዚያም ፈረንሳይ መድረሱን ተናግሮ ነበር።

ሀዱሽ ቅባቱ

ከፈረንሳይም በትንሽ ጀልባ ተሳፍሮ 'ኢንግሊሽ ቻናልን' አቋርጦ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገባ ሲሆን፣ ለዚህ ጉዞውም 1800 ዩሮ መክፈሉን አስረድቷል።

ሀዱሽ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት የስፖርት መምህር እንደነበረ ለፍርድ ቤት ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱ የሀዱሽ ዕድሜ 41 ነው ቢልም እሱ ግን ዕድሜው 38 መሆኑን በዚህ ወቅት ገልጿል።

በኮልቸስተር ከተማ ለሦስት ቀናት መቆየ ችሎት ላይ፣ "አራዊት አይደለሁም" "እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ እንዲህ አይነት ነገሮችን አላደረግም፤ እነዚህ ልጆች ናቸው፤ ንጹህ ልጆች" ሲል የቀረበበትን ክሶች ውድቅ አድርጎ ነበር።

ነገር ግን የፍርድ ቤቱ ዳኛ ክርስቶፈር ዊልያምስ ሀዱሽ "የምስክርነት ቃሉን ለመስጠት ሲል የፈጠራቸው ናቸው" ሲሉ አጣጥለውታል።

በከተማዋ ማዕከል ሰኔ 30/ 2017 ዓ.ም የትምህርት ቤት ጓደኞች ተሰባስበው ባገኛቸው ወቅት ሀዱሽ ስሙን ቶማስ እንዳላቸው እና 2500 ዩሮ ከፍሎ ዩኬ እንደገባ እንደነገራቸው በስፍራው የነበረ አንድ ታዳጊ ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር።

በተጨማሪም ለአንደኛዋ "አፍሪካ ነይ፤ ጥሩ ሚስት ትሆኛለሽ" እንዳለም ይሄው ታዳጊ ለፍርድ ቤት አስረድቷል።

ታዳጊዎቹ በወቅቱ ፒዛ እየበሉ የነበሩ ሲሆን "ከአንቺ አንድ ልጅ እፈልጋለሁ፤ ከጓደኛሽ ደግሞ አንድ ልጅ" ሲል መናገሩን አንደኛዋ ታዳጊ ለፖሊስ ተናግራለች።

ሀዱሽ በማግሥቱ አንደኛዋን ታዳጊ ቆንጆ አንደሆነች እንዲሁም ሊስማት መሞከሩን እና እጁን ጭኗ ላይ ማሳረፉን ምስክሮች ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ልጅቷ በከፍተኛ ሁኔታ መደንገጧን ለመርማሪዎች ገልጻ "አይ አይሆንም 14 ነው ዕድሜ" ስትለውም "ዕድሜ ምንም ለውጥ የለውም" በማለት ምላሽ መስጠቱን አክላለች።

ሁኔታው "አጥወለወለኝ። አንድ አዋቂ ሰው እንዴት ይህንን መፈጸም ምንም ችግር የለውም ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም ነበር" ብላለች።

የጥፋተኛነት ውሳኔውን ያሰውተላለፉት ዳኛ ዊልያምስ "የ14 ዓመት ልጅ እንደነበረች ታውቃለህ" ሲሉ ተናግረው በወቅቱ የትምህርት ቤት ዩኒፎርም መልበሷን አስታውሰዋል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ባሉት ሳምንታት ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤል ሆቴል አቅራቢያ ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ አሰምተዋል።በተመሳሳይ መልኩ ዘረኝነትን የሚቃወሙ የድጋፍ ሰልፎች ተደርገዋል።

ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት 16 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።