በዩኬ በጾታዊ ትንኮሳ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ስደተኛ 'በዚህ ሳምንት' ከአገር እንደሚባረር ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Sky
በጾታዊ ትንኮሳ እስር ተፈርዶበት በስህተት ከተለቀቀ በኋላ በድጋሚ በቁጥጥር ስር የዋለው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በዚህ ሳምንት ከአገር እንደሚባረር የዩኬ ፍትህ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ተናገሩ።
ሐዱሽ ቅባቱ ከእስር ቤት በስህተት ከተለቀቀ ከ48 ሰዓታት በኋላ በሰሜን ለንደን ፊንስበሪ የመናፈሻ ስፍራ እሁድ ዕለት በቁጥጥር ስር ውሏል።
ሐዱሽ በኢፒንግ ስደተኞች በሚቆዩበት ሆቴል እየኖረ ሳለ የ14 ዓመት ታዳጊ ላይ እና አንዲት ሌላ ሴት ላይ ጾታዊ ትንኮሳ በመፈጸም የ12 ወራት እስር የተፈረደበት ባለፈው ወር ነበር።
በስህተት ከእስር ቤት ከመለቀቁ በፊት ከአገር ሊባረር በዝግጅት ላይ እንደነበር ተገልጿል።
የፍትህ ሚኒስትሩ በማረሚያ ቤቱ የተፈጸመውን ስህተት ያጣራው ገለልተኛ ቡድን ሪፖርት ሰኞ ዕለት ለፓርላማው እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እና "ይህ ዳግም እንዳይከሰት ማድረግ አለብን" ብለው ነበር።
ሐዱሽ ለመጀመርያ ጊዜ በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ሲሆን፣ በአነስተኛ ጀልባ ወደ ዩኬ ከገባ በኋላ በኢፒንግ ይኖርበት በነበረው የስደተኞች መቆያ ሆቴል አካባቢ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኖ ነበር።
የሜት ፖሊስ ሐዱሽ ከሕግ ውጭ ከማረሚያ ቤት ውጭ በመሆን በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጾ ወደ ለንደን እስር ቤት ወስዶታል።
በፊንስበሪ የመናፈሻ ስፍራ ውሻውን እያንሸራሸረ እንደነበር የተናገረ አንድ የዓይን እማኝ ሐዱሽ በበርካታ ፖሊስ አባላት ታጅቦ ሲወሰድ ማየቱን ተናግሯል።
የ40 ዓመቱ ጃክ ኒል ሆል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል "ለመጨረሻ ጊዜ በሃክኔ አካባቢ መታየቱን አውቅ ነበር። እናም 'ያ ሰው በሚገርም ሁኔታ ሰውዬውን ይመስላል፤ ነገር ግን አንድ ዓይነት ልብስ አይደለም የለበሰው፤ ግን እርሱን ይመስላል' " ብዬ ነበር ብሏል።
"እጆቹ ላይ ካቴና ታስሮ ከመናፈሻው አካባቢ ሲወጣ አይቻለሁ። ለማምለጥ ምንም ሙከራ አላደረገም" ሲል አክሏል።
ሜት ፖሊስ እሁድ ዕለት ማንነቱን ያልገለፀው ሰው ሐዱሽን የሚመስል ሰው በፊንስ በሪ መናፈሻ አካባቢ በሚገኝ የአውቶብስ ማቆሚያ ማየቱን በመግለጽ ጥቆማ እንደሰጠው ተናግሯል።
በጥቆማው መሠረት ወደ አካባቢው ፖሊሶች ከተላኩ ከ16 ደቂቃ በኋላ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ሐዱሽ ቅባቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በድጋሚ ከዋለ በኋላ ቀድሞ ለብሶት ከነበረው ከማረሚያ ቤቱ ልብስ የተለየ ለብሶ ነበር።
የኢሴክስ ፖሊስ ሐዱሽ ቅባቱ በስህተት መልቀቁን ያወቀው አርብ ዕለት ነበር።
ፖሊስ ሐዱሽን በሚፈልግበት ወቅት እርሱ ወደ ምሥራቅ ለንደን ባቡር ተሳፍሮ ሄዶ ነበር።
ሐዱሽ ከዚያ በኋላ በኬልምስፎርድ ከተማ የተለያዩ ሰዎችን በመቅረብ ድጋፍ ሲጠይቅ በዋና መንገዶች ላይ በሚገኙ ካሜራዎች ታይቷል።
ሜት ፖሊስ አክሎም ሐዱሽ ወደ ለንደን ለመሄድ በርካታ ባቡሮች መሳፈሩን ተናግሯል።
ፖሊስ ሐዱሽ አርብ ምሽት በዳልስተን አካባቢ ወደሚገኝ ቤተመጻህፍት ሲገባ የሚያሳይ በደህንነት ካሜራ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቷል።
በመስከረም ወር የክልምስፎርድ ከተማ ፍርድ ቤት ሐዱሽ ታዳጊ ሴትን ለመሳም መሞከሩን እንዲሁም በርካታ ግልጽ የሆኑ ወሲባዊ አስተያቶችን መስጠቱን የሚገልጽ ክስ ቀርቦለት አዳምጧል።
በሚቀጥለው ቀን ተመሳሳይ ልጅን በማግኘት ጾታዊ ትንኮሳ ከመፈፀሙ በፊት ሊስማት ሞክሮ ነበር ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ሥራ ለመፈለግ እንዲረዳው ሲቪውን በማዘጋጀት የምታግዘው ሌላ ሴት ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ፈጽሟል።
ሐዱሽ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት 38 ዓመቱ እንደሆነ ቢናገርም ዳኛው ግን 41 ዓመቱ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ መኖሩን ገልጸዋል።
ሐዱሽ ምንም እንኳን የቀረበበትን ክስ በሙሉ ቢክድም በአምስት ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሎ የ12 ወራት እስር ተፈደርዶበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውንም ሴት ለአምስት ዓመታት እንዳይቀርብ ወይንም እንዳያናግር የሚያግድ የክልከላ ትዕዛዝ የተላለፈበት ሲሆን፣ ለ10 ዓመት ያህል የጾታዊ ትንኮሳ ፈጻሚዎች ምዝገባ ላይ እንዲፈርም ተወስኗል።















