ምዕራባውያን ታዳጊዎችን በኢንተርኔት እያደኑ የሚያጭበረብሩት ናይጄርያውያን

"የራቁት ምስልህ እንዲሁም ሕይወትህን ሊያመሳቅል የሚችለው ነገር ሁሉ በእጄ ነው።"
አሜሪካዊው ታዳጊ ኢቫን ቦትለር ይህንን ልብ የሚያርድ መልዕክት የተቀበለው በማኅበራዊ ሚዲያ የመልዕክት መቀበያ በኩል ነው።
መጀመርያ ላይ መልዕክቱ የደረሰው ከሴት መስሎት የነበረ ቢሆንም ግን በኋላ ላይ ግን የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች መላካቸው ታውቋል።
ይህ መልዕክት በደረሰው 90 ደቂቃ ውስጥ የ16 ዓመቱ ታዳጊ ቦትለር ራሱን አጥፍቷል።
አጭበርባሪዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ወጣት ሴት መስለው በመቅረብ ያጠመዷቸው ሰዎችን የራቁት ምሥሎች እንዲላኩላቸው በማድረግ ያንን ተጠቅመው እያስፈራሩ ገንዘብ ይቀበላሉ።
ለዚህ ደግሞ ተጋላጭ የሆኑት በአሜሪካ እና በአውሮፓ የሚኖሩ ታዳጊዎች ናቸው።
በቅድሚያ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ምስሎችን ወይንም ቪዲዮዎችን እንዲልኩ ያደርጓቸው እና ገንዘብ ካልከፈሉ ለጓደኞቻቸው ወይንም ለሌሎች አሳልፈው እንደሚሰጡ ያስፈራሯቸዋል።
የኢቫን እናት ካሪ "የዛን ዕለት ማታ መሞቱን ሲነግሩን ማመን አልቻልኩም። ይህ በእኛ ቤተሰብ ላይ እንዴት እንደሆነ ማመን አልቻልኩም" ብላለች።
በሚዙሪ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ከባለቤቷ ብራድ ጋር ሆና ልጇ ብሩህ፣ ሳቂታ፣ አሳ ማጥመድ እና አደን የሚወድ፣ ስፖርት የሚያዘወትር ልጅ እንደነበር ትናገራለች።
እንደ አውሮፓውያኑ በጥር 2024 ጄኒቲ60 (JennyTee60) በመባል የሚታወቅ አካውንት ላይ ሴት ናት ብሎ ያሰባትን ልጅ ማውራቱን ይናገራሉ።
ነገር ግን በዚህ አካውንት የምታወራው ሴት አልነበረችም፤ አጭበርባሪዎች ነበሩ።
በደቂቃ ውስጥ "ጄኒ" ወጣ ያሉ ምስሎችን እንድታጋራው ማሰመን ቻሉ።
ይህንን እንዳደረገ ወዲያው ምንም ርህራሄ ያልታየበት ውንጀላዎቸን በእርሱ ላይ ማቅረብ ጀመሩ።
ልጃቸው ከሞተ ሁለት ዓመት የሞላው ቢሆንም ወላጆቹ አሁን ሐዘናቸው ትኩስ ነው።
ለልጃቸው ሞት መልስ ለማግኘት ያደረጉትም ጥረት ምንም ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።
እንደ ሜታ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ድርጅቶች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ምንም ዓይነት መረጃ ለማጋራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል።
ቤተሰቡ ደግሞ ምንም እንኳ ለኤፍቢአይ ያመለከቱ ቢሆንም የፍርድ ቤት ማዘዣ ግን የላቸውም።
ነገር ግን አጭበርባሪዎቹ አንድ ወሳኝ የሆነ አሻራ ትተው አልፈዋል።
ኢቫን የፌስቡክ አካውንቱን መግቢያ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት ወቅት የአይፒ አድራሻቸውን ትተው ሄደዋል።
ያ የዲጂታል አሻራ በቀጥታ አጭበርባሪዎቹ ወደሚገኙበት ናይጄሪያ የሚያደርስ ነው።
እነዚህ የኦንላየን አጭበርባሪዎች ራሳቸውን በሚጠቀሙበት ኢሜል "ያሁ ቦይስ" በመባል ይጠራሉ።
ዕድሜያቸው በ20ዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኘው እነዚህ ወጣት ወንዶች በድህነት ጉስቁል ባለ መንደር እየኖሩ ቅንጡ መኪና መንዳት እና በገንዘብ ባህር መዘፈቅ ያልማሉ።
ቢቢሲ በናይጄሪያ ሌጎስ ያገኘው ኦላ አንድን ሰው በወሲብ አማልሎ ማጭበርበርን ቀለል አድርጎ ነው የሚናገረው።
"የውሸት የሴት ስም በመጠቀም የሴት አካውንት ትከፍቻለሽ" ይላል።
የሴቷን ስም የሚመርጠው ማጭበርበሩን ማከናወን በሚፈልግበት አገር የሚገኙ የሴት ስሞችን ከሚሰጠው ስም አመንጪ ድረ ገፆችን "fake generators" በመጠቀም ነው።
"የምትፈልጊውን አገር ሰው ስም የሚሰጥሽ ሳይት ነው"
ገጹ ከተከፈተ በኋላ ዒላማ ማድረግ ይጀመረዋል።
በቀን ቢያንስ አንዱ ገንዘብ ይልካል በሚል ተስፋ በመቶዎች ለሚቆጠሩ መልዕክት ለሚልኩት አጭበርባሪዎቹ በሌላ ወገን ያሉት ወንዶች ከስም ውጭ ማንም ናቸው።
'ይህ እኮ ጭካኔ ነው፤ የሰውን ሕይወት ያበላሻል' የተባለው ኦላ "ገንዘቡን ስለምፈልገው ምንም ሐዘን አይሰማኝም" ሲል መልሷል።
ለኦላ የአሜሪካ ወይንም የብሪታኒያ ታዳጊዎች ገንዘብ አይከፍሉም ብሎ ማመን ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።
በእርሱ እምሮ በምዕራባውያን አገራት መወለድ መታደል ነው።
ለምንድን ነው እነዚህን ታዳጊዎች ላይ የምታተኩረው ተብሎ ሲጠየቅ "ምክንያቱም የወሲብ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። ደግሞ ወጣት ወንዶች ምስላቸው ለትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው፣ ለወላጆቻቸው እና ለጓደኞቻቸው መላኩ ያስፈራቸዋል" ብሏል።

ኦላ የማጭበርበር ድርጊቱን ብቻውን ነው የሚሰራው።
ነገር ግን ሌሎች በሌጎስ ተመሳሳይ ማጭበርበሮች በኢንተርኔት አማካኝነት ወጣት ሴት መስሎ በመቅረብ ያጠመዷቸው ታዳጊዎችን የራቁት ምሥሎች እንዲላኩላቸው በማድረግ ያንን ተጠቅመው እያስፈራሩ ገንዘብ መቀበል እንዴት ወደ የተደራጀ የወንጀል ስራ እንደተለወጠ ያሳያሉ።
እነዚህ የወንበዴዎች ቡድን መሪዎች አሏቸው። የሥልጣን ተዋረዶች እና በጋራ በመሆን ሃብት በማሰባሰብ የሚሰሩ ወንጀሎች ትርፉን ከፍ እንዲያደርጉ ሆነው ተደራጅተዋል።
በሌጎስ የድሆች መንደር ማኮኮ ውስጥ ሃስል ኪንግደምስ (Hustle Kingdoms) እየተባሉ የሚጠሩት በኢንተርኔት የማጭበርበር ወንጀል ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ይገኛሉ።
እነዚህ ከሚዲያ ዓይን ተሰውረው የማጭበርበር ስራ የሚያከናውኑ ታዳጊዎችን ለመቅረጽ ፈቃድ ማግኘት እና ብዙ ማሳመን ይጠይቃል።
በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ፣ በርካታ ታዳጊ ወጣቶች ላፕቶፖቻቸውን ጭናቸው ላይ አስቀምጠው ይሰራሉ።
ስልኮቻቸው በሙሉ መልዕክቶች ሲገቡላቸው የሚያሰሙትን ድምጽ አሁንም አሁንም ያቃጭላል።
በቤቱ ውስጥ ያለው ድባብ የስልክ የጥሪ ማዕከል ይመስላል።
የማኅበራዊ ሚዲያ አድራሻ ይቀባበላሉ፤ ጽሑፎች ይላላካሉ፣ አዲስ የሚጭበረበር ከተገኘ ይነጋገራሉ።
እያንዳንዱ ወጣት የራሱን ሚና ተጫውቷል፣ ነገር ግን የሚገኘው ገንዘብ ሁሉ ወደ ላይ፤ ወደ አለቃቸው መሄድ አለበት። አለቃው ጎስት ይባላል።
እዚያም ልምድ ያካበቱ አጭበርባሪዎች አዳዲስ ምልምል ሰልጣኞቻቸውን ያስተምራሉ።
ማባበያው ፈጣን ገንዘብ ማግኘት የሚል ነው።
ነገር ግን ከዚህ ማማለያ ጀርባ ግን የበለጠ በአስራዎቹ ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን ለወንጀል ተግባር መመልመል አለበት።
በእድሜ ከፍ ያሉ "አማካሪዎች" በጀብድ የተሞሉ የስኬት ታሪኮቻቸው እና የሚያሳይዋቸው ማኅበረሰባዊ ደረጃ አማላይ ነው።
ከዚህ ባሻገር ከእያንዳንዱ ማጭበርበር የሚወስዱት ድርሻ፣ የሚከመርባቸው ዕዳ ታዳጊዎቹን ከዚህ የወንጀል ሽክርክሪት ለማምለጥ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል።
ይህ የማጭበርበር ስልት የተደራጀ፣ ቀልጣፋ እና የማያቋርጥ በተቻለ መጠን ብዙ ገንዘብ ለማግኘት የተነደፈ ሥርዓት ነው።
ኢቫንን ያጭበረበረው፣ ፎቶውን እነዲልክ ያደረገው የሃስትል ኪንግደም አካል ሊሆን ይችላል? ወይንስ ብቻውን ነው የሚሰራው?
መሪው ጎስት "እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው" በመሆኑ በዋናነት የገንዘብ ማጭበርበሮችን የሚፈጽመው በፍቅር ግንኙነት ስም እንጂ በወሲብ በማማለል አይደለም።
ይህንን የሚያደርጉት "ክፉ ልብ" ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ይላል።
በዚህ ሃስል ኪንግደም ውስጥ በወሲብ ስም ማጭበርበር እንደ አሳፋሪ ተግባር ይታያል።

ያሁ ቦይስ በመባል ይታወቁ የነበሩት አሁን "ያሁ ፕላስ" (Yahoo Plus) ወደሚል መሸጋገራቸውን ይናገራሉ።
ይህም ማጭበርበሮችን ለመባረክ የአካባቢውን ባሕላዊ የእምነት አባቶች መጎብኘት እና ዒላማ የሚደረግበት ሰው የበለጠ ታዛዥ ያደርገዋል ወይም አጭበርባሪዎችን እንዳይያዙ ይከላከላል ብለው የሚያምኑትን ድግምት ማስደገምን ያካትታል።
በናይጄሪያ ባህል ውስጥ ባህላዊ ሐኪሞች ለረዥም ጊዜ ሰፊ ቦታ ተሰጥቷቸዋል።
ስለዚህ ለአንዳንድ የቡድኑ አባላት ወደ እነዚህ ሰዎች መሄድ አዲስ ሲም ካርድ የመግዛት ያህል ተፈጥሯዊ ነበር።
በቅርቡ ሰዎችን በወሲብ በማማለል ገንዘብ ወደ ማጭበርበር ውስጥ የገባው የ20 ዓመቱ አዴ የበለጠ ገንዘብ እንዳገኝ ይረዳኛል ብሎ ወዳመነው የ"መንፈሳዊ አባት" ዘንድ ሄዷል።
ወደዚህ "መንፈሳዊ አባት" ዘንድ ሲኬድ የምትሰዋ ነጭ እርግብ ይዞ መሄድ እና ከተሰዋች በኋላም የአካል ክፍሏን መብላት ይጠይቃል።
ይህ መንፈሳዊ ስርዓት ከሃብት እና ከጥበቃ ጋር የተገናኘ ነው።
ወደ እዚህ ግለሰብ ዘንድ በቀን ስድስት ወይንም ሰባት የያሁ ቦይስ አባላት ይመጣሉ።
ለያዴ ይህ ጥንቆላ ሳይሆን የንግድ ወጪው አካል ነው።
ይህ የማጭበርበር ወንጀል የሚፈጸመው በተለምዷዊው መንገድ ብቻ አይደለም። የ21ኛው ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጂን 'ዲፕፌክ' ተጠቅመው እና ራቼል የምትባል ሴት ቀጥረው የሚፈልጉትን ሰው ፊት በማለዋወጥ የማጭበር ሥራዎችን ይሰራሉ።
ይህንን መተግበሪያ በ3500 ዶላር እንደገዛው ገልጸ የተከፈለበትን ይመልሳል ሲል ተናግሯል።

በአሜሪካ ላለፉት ሦስት ዓመታት ለኤፍቢአይ አጭበርባሪዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ወጣት ሴት መስለው በመቅረብ በማጥመድ እያስፈራሩ ገንዘብ ይቀበላሉ በሚል የሚቀርቡ ክሶች ከእጥፍ በላይ ጨምረዋል።
እአአ በ2024 ደግሞ በከፍተኛው ሁኔታ ጨምሮ 55,000 ደርሷል።
በዩኬ፣ በየወሩ 110 ተመሳሳይ አቤቱታዎች ለብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ ይደርሳሉ።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እርምጃ እየወሰድን ነው ቢሉም ተቺዎቻቸው ግን የበለጠ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ።
በደቡብ ካሮላይና የሚኖረው ብራንደን ጉፊን በ2022 ልጁ ጋቪን በኢንስታግራም ላይ ዒላማ ከተደረገ በኋላ ራሱን አጥፍቷል።
ያኔ ዕድሜው ገና 17 ነበር።
ልጁ ከመሞቱ በፊት ብራንደን ሜታ ከአጭበርባሪዎች ሊጠብቀው አልቻለም በማለት ክስ ለመመስረት ሲዘጋጅ ነበር።
እሱን ለማጥመድ ከተጠቀሙባቸው አካውንቶች ውስጥ አንዱ ተነስቷል። ሌሎች ግን አሁንም አሉ። ለብራንደን ይህ ሁኔታ በጣም አሳፋሪ ነበር።
ሜታ እአአ በ 2024 ከናይጄሪያ ጋር የተገናኙ 63,000 የማጭበርበሪያ አካውንቶችን በአንድ ጊዜ መሰረዙን ተናግሯል።
ከእነዚህ መካከል 2,500 በምዕራባውያን ታዳጊዎች ላይ ያነጣጠረ የተደራጀ የወንጀል መረብ አካል ነበሩ።
ሆኖም ተቺዎች እነዚያ ቁጥሮች የችግሩን ስፋት ያጎላሉ እንጂ የተወሰደውን እርምጃ በቂነት አያሳይም ብለው ይከራከራሉ።
የሜታ ቃል አቀባይ ኩባንያቸው በወሲብ እያማለሉ ማጭበርበርን ከመረጠ ብቻ ሊያጠፋው ይችላል የሚለው ሀሳብ "ከእውነት የራቀ ነው" ብለዋል።
ድርጅቱ የአጭበርባሪዎችን መረብ በማስተጓጎል የሕግ አስከባሪዎችን በመደገፍ ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ "በዓለም አቀፍ ደረጃ በደህንነት ላይ የሚሰሩ ወደ 40,000 የሚጠጉ ሰዎች አሉን፣ በዚህ አካባቢ ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል" ሲል ቃል አቀባዩ ተናግሯል።
የኩባንያው አመራሮች በሕፃናት ጥበቃ ዙሪያ የሚቀርብላቸውን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ችላ ማለታቸውን ውስጠ አዋቂዎች ይመሰክራሉ።
በመድረኩ ሕፃናትን ለመጠበቅ በቂ እርምጃ እንደማይወስዱም እንዲሁ።
የኩባንያው ቃል አቀባይ ግን እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ሲገኝ እርምጃ እንደሚወስድ እና የሕግ አካላት ፍትኅ እንዲያሰፍኑ ትብብር እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።
'ኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን' የተባለው ተቋም ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት በሚስጥር ሪፖርት የሚደረጉለትን የእርቃን እና ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምስሎች ከኢንተርኔት እንዲወገዱ እና እንዳይዛመቱ ያደርጋል።
የረድኤት ድርጅቱ ምስሎቹ ድረ ገፅ ላይ ገና ካልወጡ ደግሞ እንዳይወጡ የመከላከል ስራ ይሰራል።















