ናይጄሪያ በኢንተርኔት አማካይነት ሲያጭበረብሩ ነበር ያለቻቸውን ቻይናውያን አባረረች

የፎቶው ባለመብት, EFCC/X
ናይጄሪያ በኢንተርኔት አማካይነት ከሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ጋር በተያያዘ 50 የቻይና ዜጎችን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችን ማባረሯን የአገሪቱ የፀረ ምዝበራ ተቋም አስታወቀ።
በኢንተርኔት አማካይነት "በተደራጁ የውጭ ዜጎች በሚፈጸም የማጭበርበር የወንጀል ቡድኖች" ላይ በአገሪቱ ለሳምንት ያህል በተካሄደው ዘመቻ ነው በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉት ከ100 በላይ ግለሰቦች የተያዙት።
"እየተካሄደ ባለው በዚህ ዘመቻ ተይዘው ከናይጄሪያ እንዲባረሩ የተወሰነባቸው የውጭ አገራት ዜጎች አጠቃላይ ቁጥር 102" እንደሚደርስ የገለጸው ኮሚሽኑ "በበይነ መረብ ሽብር እና በኢንተርኔት ማጭበርበር" ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውንም ገልጿል።
አሁን ከናይጄሪያ የተባረሩት የውጭ ዜጎች ባለፈው አርብ በሌጎስ ከተማ በተካሄደው ድንገተኛ ዘመቻ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 192 ሰዎች መካከል ናቸው።
በናይጄሪያ በኢንተርኔት አማካይነት የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች በስፋት የሚካሄዱ ሲሆን፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ወንጀሎች ኮሚሽን እንደሚለው ባለፈው ዓመት በበይነ መረብ አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች በስፋት ካጋጠሙት ድርጊቶች መካከል ናቸው።
ኮሚሽኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የበይነ መረብ ወንጀለኞችን የለየ ሲሆን፣ ከናይጄሪያ ውጪ ከሚኖሩ የአገሪቱ ዜጎች ጋር የተገናኙ በርካታ ከፍተኛ የሳይበር ማጭበርበር ክሶችም አጋጥመዋል።
ጥቂቶቹ በአሜሪካ የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጭምር ያልተደረሰባቸው ናቸው።
ባለፉት ቀናት በተካሄዱ አሰሳዎች የተያዙ የውጭ አገር ዜጎች ከናይጄሪያ እንዲባረሩ የተደረገ ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ የውጭ ዜጎች እንደሚባረሩ ተነግሯል።
በናይጄሪያ የፀረ ምዝበራ ኮሚሽን በተመራው የኢንተርኔት አጭበርባሪዎችን የመያዝ ዘመቻ ከተያዙት 192 የውጭ ዜጎች መካከል 148 ቻይናውያን ናቸው።
ይህ በበይነ መረብ አማካይነት ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በሚጠረጠሩ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የተካሄደው ዘመቻ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ባለፈው ታኅሣሥ ከተያዙት 800 ከሚደርሱ ተጠርጣሪዎች 148 ቻይናውያን፣ እና 40 የፊሊፒንስ ዜጎች ይገኙበታል።
የተያዙት የውጭ ዜጎች ከናይጄሪያውያን ጋር በመተባበር በኢንተርኔት እና በክሪፕቶከረንሲ ዝውውር ማጭበርበር ውስጥ የተሳተፉ ናቸው ተብለዋል።
የፀረ ምዝበራ ኮሚሽኑ እንደሚለው በአገሪቱ ውስጥ በኢንተርኔት አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች የበረከቱት በሥራ አጥነት መስፋፋት፣ ወጣቶች ቶሎ ለመክበር ካላቸው ፍላጎት እና ደካማ የቁጥጥር ሥርዓት በመኖሩ ነው።
ባለፈው ዓመት የኢንስታግራም ማኅበራዊ መድረክ ባለቤት ሜታ በናይጄሪያ ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አካውንቶች ሰዎችን በበይነ መረብ በኩል በወሲባዊ ምሥሎች በማስፋራራት እና በማጭበርበር ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል በሚል እንዲወገዱ አደርጓል።
እንዲህ ዓይነቶቹ አጭበርባሪዎች በኢንተርኔት አማካይነት ወጣት ሴት መስለው በመቅረብ ያጠመዷቸው ሰዎችን የራቁት ምሥሎች እንዲላኩላቸው በማድረግ ያንን ተጠቅመው እያስፈራሩ ገንዘብ ይቀበላሉ።
ባለሙያዎች እና ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እየተስፋፋ ካለው ማጭበርበር እራሳቸውን እንዲጠብቁ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።















