ፎቶዎቿ በጓደኛዋ ዲፕፌክ በተባለው ቴክኖሎጂ ወሲባዊ ይዘት እንዲኖራቸው የተደረጉባት ወጣት

ሀና

የፎቶው ባለመብት, Nikki Short/BBC

አውስትራሊያዊቷ ሀና ግራንዲ ከሶስት ዓመት በፊት በየካቲት ወር ነው አንድ ኢሜል የደረሳት።

ኤሜል ማስፈጠንሪያ ይዟል። "ይህ ማስፈንጠሪያ ስሱ መረጃ ይዟል" የሚል መልዕክት አብሮት ተለጥፏል።

ማስፈንጠሪያውን ለመንካት ብዙ አመነታች። ምክንያቱም መጀመሪያ የጠረጠረችው አጭበርባሪዎች ይሆናሉ ብላ ነው።

ከብዙ ማመንታት በኋላ ስትጫነው ገፁ በርካታ የሀናን እርቃን ፎቶዎችን ይዟል። ከፎቶዎቹ ጋር እሷን መድፈር የሚያስደስታቸው ሰዎች እንዳሉም ይነበባል።

ፎቶዎቿ ብቻ ሳይሆኑ የሀና ሙሉ ስም፤ የኢንስታግራም ገጿ፤ የምትኖርበት የነበረው ሥፍራ አድራሻ እንዲሁም ስልኳ ቁጥሯ ተቀምጧል።

ይሄኔ ነው ፎቶዎቿ የቅርብ ጓደኛ በምትላቸው ሰዎች አማካይነት ሾልከው መውጣታቸው የገባት።

ዘ ዲስትራክሽን ኦፍ ሀና የተባለው ድረ-ገፅ ከላይ የሐሳብ መስጫ ሳጥን አለው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እሷ ላይ እንዴት አድርገው ወሲባዊ ብዝበዛ ማድረስ እንደሚፈልጉ ሐሳብ የሚሰጡበት ነው።

ወረድ ብሎ ደግሞ ከ600 በላይ ፎቶዎች ተደርድረዋል። ፎቶዎቹ የሀና ፊት እንዲገጠምላቸው ተደርጓል። በጣም አሰቃቂ የሆኑ የፅሑፍ መልዕክቶችም አሉበት።

"ቤቷ ተደብቄ ቆይቼ ብቻዋን ስትሆን ከኋላ ይዣት. . . ስትሰቃይ መስማት እፈልጋለሁ" ይላል አንዱ ፅሑፍ።

ሌሎችም ከዚህም በላይ አሰቃቂ የሆኑ ፅሑፎች ተለጥፈዋል።

ይህ ከሆነ ሶስት ዓመት ቢያልፈውም የ35 ዓመቷ ሀና እና ፍቅር ጓደኛዋ ክሪስ ቬንቹራ ድረ-ገፁን ያገኙት ጊዜ የተሰማቸውን "ከባድ ድንጋጤ" አሁንም አይረሱትም።

ሁለቱ ድረ-ገፁን ሲበረብሩ የቅርብ ጓደኛቸውን ፎቶ እና ሌሎች 60 የሚሆኑ ሲድኒ የሚኖሩ ሴቶችን ፎቶ አግኝተዋል።

የተረዱት ነገር ዲፕፌክ በተባለው ቴክኖሎጂ የተሠሩት ፎቶዎች ከሴቶቹ የማኅበራዊ ሚድያ ገፅ የተገኙ ናቸው። ይሄኔ ነው ሀና እና ክሪስ ምርመራቸውን የጀመሩት።

ኮምፒውተራቸውን ከፍተው የእያንዳናቸውን ሴቶች ማኅበራዊ ሚድያ በማፈላለግ ጓደኞቻቸውን መመርመር ያዙ። ይህን የሚያደርጉት ሁሉም በጋር ያላቸው ጓደኛ ማነው የሚለውን ለማጣራት ነው።

በአራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሶስት ተጠርጣሪዎችን ነጥለው አወጡ። ከተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲ የቅርብ ጓደኛቸው የነበረው አንድሪው ሀይለር ነው።

ሀና

የፎቶው ባለመብት, Supplied

የምስሉ መግለጫ, በዲፕፌክ የተሠራ የሀና እርቃን ፎቶ

አንዲ ሲሉ የሚጠሩት ጓደኛቸው የሁሉም ሰብሳባ፣ አሳቢ እና መልካም ሰው ነበር። በተለይ ለሴቶች እጅግ አሳቢ እና ሩህሩህ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሶስቱን ተጠርጣሪዎች መርምረው ሲያበቁ በስተመጨረሻ ቀልባቸው አንዲ ላይ አረፈ።

ሀና በነጋታው ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራች። "በዚያኑ ቀን እጁን ጠፍረው በቁጥጥር ሥር የሚያውሉት መስሎኝ ነበር" ይላል ክሪስ።

ነገር ግን ፖሊስ ጣቢያ የገጠማቸው ከጠበቁት የተለየ ነው። መኮንኖቹ ሊረዷቸው ፈቃደኛ አይደሉም። እንደውም አንዱ ፖሊስ ፎቶውን ተመልክቶ "ይህ ልብስ ያምርብሻል" አላት።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ የሀናን ጉዳይ በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ሀና በፖሊስ ላይ ያላት መተማመን መነመነ።

ጥንዶቹ የፖሊስ ነገር አልሆን ሲላቸው ጠበቃ እና የዲጂታል መርማሪ ቀጥረው ለጥያቄያቸው ምላሽ ለማግኘት የጀመሩትን ጉዞ ቀጠሉበት።

ይህ ሁሉ ሲሆን ጉዳዩን አንዲ የተባለው ጓደኛቸው እንዳይሰማ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባቸው።

በመኖሪያ ቤታቸው ዙሪያ ካሜራ ገጠሙ። ሀና የልብ ምቷን የሚቆጣጠር ሰዓት ማድረግ ጀመረች። ሀና በከፍተኛ ፍርሀት ተዋጠች።

ጥንዶቹ ለምርመራ እና ለጥበቃ ያወጡት ወጭ ከ20 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር በላይ ነው።

በስተመጨረሻ አንድ መርማሪ ተመደበላቸው። ይህ በሆነ በሁለት ሳምንት ጊዜ ፖሊስ ወደ አንዲ ቤት ሄዶ ምርመራ አደረገ። ተጠርጣሪው ሁሉንም ነገር አመነ።

እፎይታ ያገኘችው ሀና ለጓደኞቿ እየደወለች ዜናውን ማብሰር ጀመረች።

ሀና እና ጓደኞቿ

የፎቶው ባለመብት, Ethan Rix/ABC News

የሀና ጉዳይ አውስትራሊያን ነቀነቀ።

ለአስር ዓመት ያክል የዘርፉ ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ አማካይነት ወንጀል ሊፈፀም ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ነበር።

በተለይ ዲፕፌክ በተባለው እና የሰዎችን ፎቶ እንዳሻው በሚያደርገው ቴክኖሎጂ አማካይነት በተለይ ሴቶች ወሲባዊ ብዝበዛ ሊደርስባቸው እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል።

አንዲ በቁጥጥር ሥር ሲውል በዲፕፌክ ወሲባዊ ፎቶ ሠርቶ መልቀቅ በአውስትራሊያ ወንጀል አልነበረም። የ39 ዓመቱ ግለሰብ የተከሰሰው የኢንተርኔት ወንጀል በመፈፀም ሲሆን ይህ ደግሞ አነስተኛ ቅጣት ያለው ነው።

ነገር ግን ጉዳዩን ሲዳኙ የነበሩት ዳኛ ጄን ከልቨር ወንጀለኛው ምንም መፀፀት አላሳየም በማለት ቅጣቱን ከበድ አድርገው የ9 ዓመት እስር ፈረዱበት።

አውስትራሊያ በቅርቡ በዲፕፌክ አማካይት ወሲባዊ ፎቶ ማጋራት ወንጀል ነው የሚል ሕግ አፅድቃለች።