"ትራምፕ ካናዳን ወደ አሜሪካ መጠቅለል የሚሹት ከልባቸው ነው" ጀስቲን ትሩዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተሰናባቹ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ ትራምፕ ካናዳን ወደ አሜሪካ ስለመጠቅለል የሰጡት አስተያየት ለፌዝ እንዳልነበረ ተናገሩ።
ትሩዶ ይህን ያሉት የትልልቅ ኩባንያ መሪዎችን ቶሮንቶ ላይ ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
"ትራምፕ ካናዳን የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት ማድረግ ይፈልጋል፤ ይህን የሚፈልገው ደግሞ ከልቡ ነው" ብለዋል።
ይህም ፍላጎት የመነጨው ካናዳ ውድ የተፈጥሮ ሃብት ስለታደለች ነው ብለዋል።
"ትራምፕ ይህን ሃብት ለመቀራመት አቋራጩ መንገድ ካናዳን የአሜሪካ ግዛት ማድረግ አንደሆነ በመረዳቱ ነው" ሲሉም ትሩዶ ጨምረው ገልጸዋል።
ትሩዶ ይህን ያሉት በቶሮንቶ በዝግ እየተካሄደ በነበረው የካናዳና-አሜሪካ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ነው።
ምንም እንኳ ጉባኤው ለሚዲያ ዝግ የነበረ ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድምጽ ተቀድቶ ወጥቶ በአንዳንድ የካናዳ ሚዲያዎች ተዘግቧል።
በዚህ ጉባኤ ላይ ከ100 የኩባንያ መሪዎች በላይ ተገኝተዋል። ጉባኤውን ያሰናዳው ደግሞ በቅርቡ የተሰየመው የአሜሪካ-ካናዳ አማካሪ ምክር ቤት ነው።
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ነበር የካናዳ ምርቶች ላይ የ25% ታሪፍ የጫኑት። ከካናዳ በሚገባ የነዳጅ ምርት ላይ ደግሞ 10% ታሪፍ በይነው ነበር።
ይህ ታሪፍ ተግባራዊ ቢደረግ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ይሆን ነበር።
ሆኖም ትራምፕ ከካናዳና ሜክሲኮ መሪዎች ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ ታሪፉ ለአንድ ወር እንዲዘገይ ወስነዋል።
ትራምፕ "ለካናዳ የሚሻላት የአሜሪካ 51ኛው ግዛት መሆን ነው" የሚለውን አስተያየታቸውን በተደጋጋሚ ተናግረውታል። በማኅበራዊ ገጽ ሰሌዳቸው በተደጋጋሚ ጽፈውታል።
በአንድ ወቀትም የካናዳን ጠቅላይ ሚኒስትርም "አገረ ገዥ' በሚል ጠርተዋቸው ያውቃሉ።
ትራምፕ ለመጀመርያ ጊዜ ይህን ካናዳን የመጠቅለል ሐሳብ ያነሱት ከትሩዶ ጋር ባለፈው ታኅሣሥ ወር በነበራቸው አንድ የእራት ግብዣ ላይ ነበር።
ያን ጊዜ የካናዳ ባለሥልጣናት ነገሩ ቀልድ መስሏቸው ስቀወላቸው ነበር።
ነገር ግን ትራምፕ ነገሩን እየደጋገሙት መምጣታቸው ጉዳዩ ፌዝ እንዳልነበረ ካናዳዊያን መረዳት ጀምረዋል። በተለይ ትሩዶ በዚህ የቢዝነስ መሪዎች ጉባኤ ላይ የሰጡት አስተያየት ካናዳ በትራምፕ የተደቀነባትን ስጋት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሆኗል።
አንድ በጥር ወር የተደረገ ጥናት ከካናዳዊያን መሀል 20% የሚሆኑት ብቻ ናቸው ከአሜሪካ ጋር መቀላቀልን የሚሹት። 80% የሚሆኑት ግን ሐሳቡን ፍጹም የሚቃወሙ ሆነው ተገኝተዋል።
ካናዳ 51ኛው የአሜሪካ ግዛት ለመሆን ሐሳቡ በአሜሪካ የሕግ መወሰኛውና የሕግ አውጪው ምክር ቤት ከፍተኛ ድምጽ ማግኘት አለበት።
በካናዳ የትራምፕ አቋም እና የታሪፍ ማስፈራሪያ ትልቅ ጭንቀት ፈጥሯል። አብዛኛው የካናዳ የውጭ ንግድ (3/4ኛው) ለአሜሪካ ነው የሚሸጠው።
ትራምፕ እንዳስፈራሩት በነዚህ ምርቶች ላይ ታሪፍ ከጣሉ የካናዳ ኢኮኖሚ ይደቃል። በርካታ ካናዳዊያነም ሥራ ያጣሉ።
ይህን ስጋት ለመገዳደር በካናዳ አንዳንድ አውራጃዎች ዜጎች የአገር ምርት ብቻ እንዲገዙ 'ከአሜሪካ የሚገባ ምርት እንዳይገዙ' ሰፊ ዘመቻ ተጀምሯል።
በርካታ ካናዳዊያን ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን የሽርሽር ጉዞም ሰርዘዋል።












