ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በተረከቡ በሁለተኛው ሳምንት ያሳለፏቸው 10 ውሳኔዎች

ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን ከተረከቡ ሁለተኛ ሳምንታቸውን አጠናቀዋል።
የተጠናቀቀው ሳምንት ለእርሳቸው እና ለቡድናቸው ወሳኝ የሚባሉ ተግባራትን ያከናወኑበት ሆኖ ተመዝግቧል።
አሜሪካ የጋዛ መጻዒ ዕድል ላይ ያላትን ግብ እና የአሜሪካ የውጪ እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ከውሳኔዎቻቸው መካከል ጎልተው የታዩት ነበሩ።
ፆታቸውን የቀየሩ ወንዶች በሴቶች ስፖርት ላይ እንዳይሳተፉ ማገድ ደግሞ ሌላው ትራምፕ፣ አማካሪያቸው ኢላን መስክ እና ቡድናቸው ካሳለፏቸው ትልልቅ ውሳኔዎች መካከል ይገኙበታል።
ትራምፕ ከፈረሟቸው በርካታ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች መካከል የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የደኅንነት መረጃዎች እንዳይደርሳቸው የሚለው ሌላው ነበር።
ጋዛን የመጠቅለል ሃሳብ
ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በዋይት ሐውስ በጋራ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ነበር ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን "የመጠቅለል" እና "በባለቤትነት" የማስተዳደር ሀሳብ እንዳላት በሂደቱም ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ ቦታ እንደምታሰፍር ይፋ ያደረጉት።
ትራምፕ ባለፉት 15 ወራት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ፍርስርሷ የወጣውን ጋዛን መልሶ የመገንባት ሃሳብ አቅርበዋል።
"የጋዛ ሰርጥ በጦርነቱ ማብቂያ ላይ በእስራኤል ለአሜሪካ ሊሰጥ ይችላል" የሚለውን ሃሳባቸውን ሐሙስ ዕለት ትራምፕ ይህንን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የደገሙት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በስፍራው እየኖሩ የሚገኙትን ፍልስጤማውያን መልሶ የማስፈር ሃሳብ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ማፈናቀል በቋሚነት ሊሆን እንደሚችል ቢናገሩም ባለሥልጣናቶቻቸው ግን ከአካባቢው የሚነሱ ሰዎች ለጊዜው እንደሚሆን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ማንኛው ሰላማዊ ሰዎችን ያለፍላጎታቸው ማፈናቀል የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው።
የዩኤስኤይድ ሠራተኞችን እረፍት እንዲወጡ ማድረግ
የአሜሪካ ዋነኛ የውጭ እርዳታ ተቋም የሆነው፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤይድ) በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከአርብ እኩለ ሌሊት ጀምሮ እረፍት እንዲወጡ ይጠበቅ ነበር።
በፕሬዝዳንቱ ምክረ ሃሳብ የቀረበው ይህ ውሳኔ በርካታ የሰው ኃይልን የሚቀንስ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት 10 ሺህ ያህል ሠራተኞች መካከል ወሳኝ የሆኑ ጥቂት መቶዎች ብቻ እንዲቀሩት ያደርጋል።
ይህ ውሳኔ የተሰማው ከቀናት በፊት ሠራተኞቹ ዋሺንግተን ዲሲ ከሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት እንዲርቁ ከተነገራቸው በኋላ ነው።
ይህ የሠራተኞች ቅነሳ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርገውን ድጋፍ ክፉኛ የጎዳው ሲሆን፣ በተወሰኑ አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፕሮግራሞች እንዲቋረጡ አስገድዷል።
የትራምፕ አስተዳደር ይህንን በመላው ዓለም በእርዳታ እና በተለያዩ ድጋፎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያከፋፍለውን ድርጅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ጋር የማዋሀድ ዕቅድ እንዳላቸው ይነገራል።
በቻይና፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ ላይ ቀረጥ መጨመር
ትራምፕ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ሲጥሉ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በድንበሮቻቸው አካባቢ ያለውን የፀጥታ እና ቁጥጥር ሁኔታ ለማጠናከር ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ከእነዚህ አገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ ሊጥሉት የነበረውን የ25 በመቶ ታሪፍን ለ30 ቀናት አዘግይተውታል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በአሜሪካ እና በካናዳ ድንበር አካባቢ ያለውን ጥበቃ ለማጠናከር እና የስደተኞች እና አደናዛዥ ዕጽ ፍሰትን ለመቀነስ ተስማምተዋል።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንበም በበኩላቸው በአገራቸው ሰሜናዊ ድንበር ያለውን ጥበቃ እንደሚያጠናክሩ ነገልጹ አሜሪካ በበኩሏ ወደ ሜክሲኮ የሚገቡ ጦር መሳሪያዎችን ለመገደብ ተስማምታለች።
ፕሬዝዳነት ትራምፕ ያስቀመጡት ታሪፍ በተወሰኑ ባለሙያዎች ዕይታ ግሽበትን የሚያባብስ ውሳኔ እንደሆ ይታመናል።
ለሠራተኞች የወራት ደሞዝ ሰጥቶ ማሰናበት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሥራቸው ለመልቀቅ ለሚስማሙ ሁሉም የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የስምንት ወር ደመወዛቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ትራምፕ የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መጠን ለመቀነስ በያዙት ዕቅድ ነው ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት።
ይኹን እንጂ የዚህ ዕቅድ ማብቂያ ከመድረሱ ከሰዓታት በፊት ፍርድ ቤት ጊዜያቂ ዕግድ ጥሎበታል። ይህም ሰኞ ዕለት የፍርድ ቤት ክርክር እስኪካሄድ ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
የትራምፕ አስተዳደር እስከ 10 በመቶ የሚደርሱት ወይም 200 ሺህ የሚሆኑት ሠራተኞች የቀረበላቸውን አማራጭ ይቀበላሉ ተብሎ እንደሚጠብቅ የቢቢሲ አሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
በአሜሪካ የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ሠራተኞች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ይሆናል።
ይህንን የትራምፕን ዕቅድ የሚተቹ ወገኖች ሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ የፌደራል ሠራተኞች ማኅበራት በበኩላቸው ማንኛውም ሠራተኛ የፕሬዝዳንቱን ማማለያ ከመቀበሉ በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል።
ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ላይ የተጣለ ማዕቀብ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ የገንዘብ እና የቪዛ ዕቀባ ጥለዋል።
የቪዛ ዕቀባው የአሜሪካ ወይም የአጋሯቿ ዜጎች ላይ ምርመራ የሚያደረጉትን እና የሚረዱ ግለሰቦች እንዲሁም ቤተሰቦቻችን ዒላማ ያደረገ ነው።
መቀመጫውን ዘ ሔግ ያደረገው ይህ ፍርድ ቤት በዓለም የተለያዩ ክፍሎች በዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ እና በጦር ወንጀሎች የተጠረጠሩ አካላትን የሚመረምር እና የፍርድ ውሳኔ የሚያሳልፍ ነው።
ትራምፕ ይህንን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የፈረሙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ዋሽንግተንን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት ነው።
ባለፈው ጥቅምት ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ኔታኒያሁ በጋዛ ፈጽመውታል ባለው የጦር ወንጀል ምክንያት የእስር ትዕዛዝ አውጥቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ይህንን ክስ እስራኤል አትቀበለውም። በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ የሐማስ የጦር አዛዥ ላይም የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል።
ከ120 አገራት በላይ የዚህ ፍርድ ቤት አባል ሲሆኑ፣ አሜሪካ የዚህ ዓለም አቀፍ ተቋም አባል አይደለችም። በተደጋጋሚም በአሜሪካ ዜጎች ላይ በፍርድ ቤቱ የሚተላለፍ ውሳኔዎችን ውድቅ አድርጋለች።
በሶማሊያ አይኤስ ላይ የተፈጸመ ጥቃት
ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ጥቃት አቀነባባሪዎች ላይ የአየር ድብደባ እንደተፈፀመ ተናግረዋል።
"በአየር ድብደባ የሚኖሩበትን ዋሻ አውድመናል፤ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳናደርስ በርካታ ሽብርተኞች ገድለናል" ሲሉ ተናግረዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ቢሮ በኤክስ ገፁ ላይ "አሜሪካን ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የምታደርገውን ድጋፍ" አድንቋል።
ከመንግሥታት ድርጅት ተቋማት መውጣት
ትራምፕ አሜሪካ በበርካታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማስቆም እርምጃ ወስደዋል።
ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ አሜሪካን ከዋናው የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ (UNRWA) ለመውጣት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ይኸው ትዕዛዝ አሜሪካ ከአሁን በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (UNHRC) እንደማትሳተፍ እና በመንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያላት አባልነት ላይ በ90 ቀናት ውስጥ ግምገማ እንደምታካሂድ ይገልጻል።
ስደተኞችን ወደ ጓንታናሞ መላክ
ትራምፕ ሰነድ አልባ ስደተኞን በመያዝ ከአሜሪካ ለማባረር ማቀዳቸውን ካስታወቁ በኋላ የመጀመሪያውን የስደተኞች ቡድን በኩባ ወደሚገኘው የአሜሪካ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር፣ ጓንታናሞ ቤይ ልከዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እስረኞቹ ከቬንዙዌላ እስር ቤቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ብሏል። በርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ሲቢኤስ እንደዘገበው ወደ ጓንታናሞ የተላኩት አስር እስረኞች ናቸው።
እርምጃው የመጣው ያሉት የስደተኞች ማቆያ ስፍራዎቹ 30,000 የሚጠጉ ሰዎችን ለመያዝ እንዲችሉ ተደርገው እንዲስፋፉ ትራምፕ ካዘዙ በኋላ ነው።
የባሕር ኃይል ጣቢያው ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ለዓመታት ለማኖር ሲያገለግል ቆይቷል።
በ2002 ከተከፈተ ጀምሮ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች፣ በእስር ላይ ይገኛሉ።
እንደ አሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ በማቆያ ጣቢያው በአሁን ጊዜ 15 ሰዎች በእስር ላይ ይገኛሉ።
ስደተኞችን ወደ መጡበት አገር የሚመልሱ በረራዎች በዚህ ሳምንት ወደ ሕንድ ተደርገዋል።
ፆታቸውን የቀየሩ በሴቶች ስፖርት እንዳይወዳደሩ ማገድ
ዶናልድ ትራምፕ ፆታቸውን ወደ ሴት የቀየሩ ሰዎች በሴቶች የስፖርት ዘርፎች ላይ እንዳይወዳደሩ የሚከለክለውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረመዋል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ፆታቸውን ከወንድ ወደ ሴት የቀየሩ ሰዎችን በሚመለከት መመሪያ፣ ደንብ እና ሕጋዊ ትርጓሜዎችን የሚሰጥ ሲሆን፣ የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔውን እንዲያስፈጽም እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ የሚያዝ ነው።
ይህ ትዕዛዝ በ2028 በሎስ አንጀለስ የሚካሄደውን የኦሊምፒክ ውድድርን እንደሚያካትት ጠቅሰው ፆታቸውን የቀየሩ አትሌቶች ለመወዳደርም ሆነ አሜሪካን ለመጎብኘት ቪዛ አንደማይሰጣቸው ተናግረዋል።
ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጥ ድጋፍን ማቋረጥ
በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባወጣችው አዲስ የመሬት ሕግ ምክንያት ደስተኛ አለመሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀው ነበር።
የጥቂት ነጮች አገዛዝ የነበረው የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት ከወደቀ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ የአገሪቱን አብዛኛውን መሬት ነጮች በግል ንብረትነት ይዘው መቆየታቸው በአገሪቱ ውስጥ ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
ይህንን የመሬት ይዞታን ፍትሐዊ ለማድረግ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ እና ለሕዝብ ጠቅም አስፈላጊ የሆኑ የመሬት ይዞታዎች ያለካሳ ለመውረስ የሚያስችል ሕግ በመውጣቱ "የዜጎችን መብት የሚጥስ ነው" ሲሉ ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አውጥተዋል።
በዚህም መሠረት አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ የምትሰጠው እርዳታ እና ድጋፍ የሚቋረጥ ይሆናል፤ ነጭ ገበሬዎች እና ቤተሰቦቻቸው በስደተኝነት ወደ አሜሪካ መግባት የሚፈልጉ ከሆነ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ ፕሬዝዳንት ራማፎሳን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞችን አስቆጥቷል። ሌሎችም ጥያቄዎችን አስነስቷል።












