የትራምፕ ጥቃት ዒላማ የሆነው ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሚመለምለው አይኤስ-ሶማሊያ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • ፀሐፊ, ሜሪ ሃርፐር
    • የሥራ ድርሻ, የሶማሊያ ተንታኝ

በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ ተራሮች ውስጥ የመሸጉትን እና በአፍሪካ ውስጥ የእስላማዊ መንግስት (አይኤስ) ቡድን ማዕከል የሆኑትን ታጣቂዎች ማደን እና መውጋት ከባድ ሥራ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን በተለመደው የዶናልድ ትራምፕ ዘይቤ፤ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በአካባቢው የአየር ጥቃት እንዲፈጸም ካዘዙ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ "አታመልጡንም፣ እንገላችኋለንም" ሲሉ ለጥፈዋል።

ትራምፕ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ፑንትላንድ ውስጥ ከፍተኛ የአይኤስ ጥቃቶችን አቀነባባሪ እና ሌሎች ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት "[ታጣቂዎች] የሚኖሩባቸውን ዋሻዎች ማውደሙን እና በምንም መልኩ በንጹሃን ሰዎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ብዙ አሸባሪዎችን መግደሉን" ተናግረዋል።

"ባይደን እና ጓደኞቹ ሥራውን ለመጨረስ በፍጥነት እርምጃ አልወሰዱም። እኔ ግን ያንን አደረግኩ" ሲሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ያልቻሉትን እሳቸው ማሳካታቸውን በኩራት ገልጸዋል።

በአዲሱ አስተዳደር የአሜሪካ የመጀመሪያው ትልቅ ወታደራዊ ዘመቻ ሶማሊያ ዒላማ መሆኗ አሜሪካ ችላ ልትላቸው ማቀዷ ያሰጋቸውን ሶማሊያውያንን ያስገረመ ነበር።

ምንም እንኳን በጆ ባይደን ቢቀለበስም በትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመ 700 የሚጠጉ አሜሪካ ወታደሮች ሶማሊያን ለቅቀው መውጣታቸው ይታወሳል።

የሶማሊያ መንግሥት በቅርቡ አንድ የወትዋች (ሎቢ) ቡድን መቅጠሩ ነገሩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አመልካች ነው። መሠረቱን ዋሽንግተን ያደረገው የሎቢ ድርጅት ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ያደረገው በዓመት የ600,000 ዶላር ክፍያ ስምምነት ነው።

በባይደን የሥልጣን ዘመን በሶማሊያ የሚገኙ የአሜሪካን ወታደሮች ልዩ ዘመቻ ያካሂዱ ነበር፣ ዋኛ የሶማሊያ ጦር አባላትን ማሠልጠን እና መደበኛ የአየር ጥቃትም ይፈጽሙ ነበር።

የአይኤስ ሶማሊያ ታጣቂዎች የመሸጉበት ተራራ

የፎቶው ባለመብት, @PuntlandSSR

የምስሉ መግለጫ, የአይኤስ ሶማሊያ ታጣቂዎች የመሸጉበት ተራራ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአየር ጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሜሪካ "ልዩ ኃይላችንን በማሠልጠን ላይ የሚገኙትን አሜሪካውያን አማካሪዎች እንዳታስወጣ" ሲሉ ተማጽነዋል።

ከጥቃቱ በኋላ በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የኤክስ ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ "ዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ያላትን ያልተቋረጠ ድጋፍ" እውቅና በመስጠት "በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ አመራር ያለውን ቀጣይነት" በደስታ ተቀብሏል።

ነገር ግን የአየር ድብደባ በመሬት ላይ ካሉት ወታደሮች የተለየ ነው እና ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው የአየር ላይ ጥቃትን አላቆሙም። እንዲያውም ወደ 400 ያህል ከፍ አድርገዋቸዋል።

ተቀማጭነቱን ናይሮቢ ያደረገው ሳሃን የተባለው የምርምር ተቋም አማካሪ ማት ብራይደን "ጥቃቱ የአሜሪካ መንግሥት በሶማሊያ የሚያደርገውን ወታደራዊ ተሳትፎ ያጠናክራል ማለት አይደለም" ብለዋል።

"በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የመሪነት ቦታ እንደሚይዙ የሚጠበቁ በርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ታማኝ አጋር እንደሆነ አይገነዘቡም፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሚሰጠውን ከፍተኛ የደኅንነት ድጋፍ በጣም አነስተኛ በሆነ ውጤት ላይ በጥልቅ ይተቻሉ።"

የፑንትላንድ የፀረ-ሽብርተኝነት አካሄድ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ግንኙነቷን ካቋረጠችው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ከወሰደው የተለየ ነው።

አሜሪካንን እና ቱርክን የመሳሰሉትን ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች በሚሰጥ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ያልሆነ እና በራሱ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 12,000 የሚጠጉት እዚያው ሶማሊያ ውስጥ ይገኛል።

የፑንትላንድ የፀጥታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሙባረክ እንዳመለከቱት ከሰሜን-ምሥራቅ የተወጣጡ ወታደሮች ከአይኤስ ጋር ሲዋጉ የቆዩት ከጥቂት እርዳታ እና ድጋፍ ጋር ነው።

"በመሬት ላይ እየተጋለን እና እየሞትን ሳለ ለአየር ጥቃቱ ብዙ እውቅና መስጠት ፍትሃዊ አይደለም" ብለዋል ሙባረክ።

የአይኤስ-ሶማሊያ መሪ አብዱልቃድር ሙሚን

የፎቶው ባለመብት, al-kataib

የምስሉ መግለጫ, የአይኤስ-ሶማሊያ መሪ አብዱልቃድር ሙሚን

"ቀሪው ዓለም ምንም ቢሠራ እኛ የምንዋጋው አይኤስን ነው ይህም ዓለም አቀፍ ችግር ነው" ይላሉ።

"ከኬንያ፣ ከኢትዮጵያ እና ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በስተቀር ብዙ ድጋፍ ያደረገልን የለም። አሜሪካኖች ከአንድ በላይ የአየር ጥቃት ይፈጽሙ እንደሆነ አናውቅም" ሲሉ ያክላሉ።

ፑንትላንድ ባለፈው ዓመት ሙሉ በሙሉ "ሂላክ" ወይም "መብረቅ" የተሰኘውን የማጥቃት ዘመቻዋን ከጀመረች በኋላ ኃይሏ 48 ዋሻዎችን እና የአይኤስ መከላከያዎችን - እና በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ፈንጂዎችን መውደሟን ተናግራለች።

ምንም እንኳን አይኤስ በሶማሊያ ለአስር ዓመታት ያህል ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም፣ የሀገሪቱን ሰፊ ክፍል የሚቆጣጠረው እና የአልቃይዳ በጣም ስኬታማ አጋር ነው ተብሎ ከተገለጸው አልሸባብ እስላማዊ ቡድን ያነሰ ስጋት ፈጥሯል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይኤስ በአገር ውስጥ፣ በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ጉልህ እየሆነ መጥቷል።

የፑንትላንድ ባለሥልጣናት እና ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአይኤስ-ሶማሊያ መሪ፣ ባለ ብርቱካናማ ጢሙ፣ እና መነጽር ለባሹ አብዱልቃድር ሙሚን፣ አሁን የአይኤስ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊ ነው ይላሉ።

አንዳንድ ሪፖርቶች ባለፈው ግንቦት አሜሪካ ባደረገው የአየር ጥቃት መገደሉን ቢጠቁሙም፤ ነገር ግን እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም።

ሙሚን የአይኤስ መሪ ሆነም አለሆነም፤ በሕይወት ኖረም ሞተም አይኤስ-ሶማሊያ ለውጭ ሀገራት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

የፑንት ላንድ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የፑንትላንድ ወታደሮች

ትራምፕ እንዳሉት "በዋሻ ውስጥ ተደብቀው ያገኘናቸው እነዚህ ገዳዮች አሜሪካን እና አጋሮቻችንን አስፈራርተዋል።"

በዋሽንግተን ዲሲ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ፀረ-ሽብር ማዕከል ዳይሬክተር ትሪሺያ ባኮን እንዳሉት "አይኤስ-ሶማሊያ በእስላማዊ መንግሥት አውታረመረብ ውስጥ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ እንዲሁም ከአህጉሪቱ ባሻገር ብዙ ኃላፊነቶችን ወስዷል" ብለዋል ።

የአይኤስ ቅርንጫፎች በአህጉሪቱ ከሞዛምቢክ እስከ ማሊ፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስከ ናይጄሪያ እየሠሩ ባሉበት፣ አይኤስ-ሶማሊያ እንደ ወሳኝ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።

ባኮን አይኤስ-ሶማሊያ ከአፍሪካም አልፎ እንደሚመለከት አስጠንቅቀዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም የአይኤስ ጥቃቶችን ለማመቻቸት እና አስተዋፅኦ ለማድረግ ተመቻችቶ ተቀምጧል። በምዕራቡ ዓለምም ጥቃቶችን ለማነሳሳት ይፈልጋል" ይላሉ።

"ዓለም አቀፍ አጋሮች ፑንትላንድ በቡድኑ ላይ ለምታደርገው ጥረት የበለጠ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው።"

ብራይደን አይኤስ በየመን ቀይ ባሕርን አቋርጠው በኢራን ከሚደገፉ የሁቲ አማፅያን ጋር ሊመሳጠር እንደሚችልም ይናገራሉ።

"እንደ አልሸባብ ሁሉ አይኤስ-ሶማሊያም በየመን ከሚገኙት የሁቲዎች የጦር መሳሪያ እና ሥልጠና አግኝቷል ይህም የአሜሪካ መንግሥት እና አጋሮቹ ስጋት ነው" ብሏል።

የጦር አውርፕላን

የፎቶው ባለመብት, @USAfricaCommand

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የውጭ አገር ተዋጊዎች ቡድኑን በመቀላቀል አይኤስ በቁጥር እና ያለው ጥንካሬ እንዲያጎለብት አድርገውታል።

የአይኤስ-ሶማሊያ ምልምል ዋና ምንጭ በፑንትላንድ የወደብ ከተማ ቦሳሶ ባሕር አቋርጠው ወደ ውጭ አገር ለመሻገር ተስፋ የሰነቁ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው ተብሎ ይታሰባል።

አይኤስ በባሕረ ሰላጤው ሀገራት ከሚያገኙት የተሻለ ክፍያ የሚያቀርብላቸው ሲሆን፣ የቡድኑ ከፍተኛ አዛዦች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

"አይኤስ-ሶማሊያ ውስጥ 80 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት የውጭ ተዋጊዎች መሆናቸውን ገምግመናል፣ በአብዛኛው ከሰሜን አፍሪካ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከታንዛኒያ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ተዋጊዎች ናቸው" ብለዋል አቶ ሙባረክ።

ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ ኃላፊ ማይክል ላንግሌይ አይኤስ በሰሜናዊ ሶማሊያ በአንድ ዓመት ውስጥ "በሁለት እጥፍ" ያደገ መስሏቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ቡድኑ በታኅሣሥ ወር ፑንትላንድ ባሪ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የጦር ሰፈር በመምታት ካካሄዳቸው እጅግ የተራቀቁ ጥቃቶች መካከል አንዱን ፈጽሟል።

ቡድኑ አንድም ሶማሌያዊ በጥቃቱ አልተሳተፈም ሲል መግለጫ አውጥቷል። 12ቱ አጥቂዎች ከሰባት ሀገራት ማለትም ከታንዛኒያ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሞሮኮ፣ ከሊቢያ፣ ከቱኒዚያ፣ ከየመን እና ከኢትዮጵያ የመጡ ናቸው።

እንቅስቃሴው ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድም የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።

የአሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የሶማሊያ ባለሙያዎች የአይኤስ የፋይናንስ መሠረት ቁልፍ አካል የሆነው የአል-ካራር ጽህፈት ቤት በፑንትላንድ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ እና ከዚያም ባሻገር ላሉ የቡድኑ ቅርንጫፎች የገንዘብ እና እውቀትን ይሰጣል።

የአሜሪካ የግምጃ ቤት የውጭ ሀብት ቁጥጥር ቢሮ (OFAC) እንዳስታወቀው አይኤስ ሶማሊያ በ2022 የመጀመሪያ አጋማሽ በአገር ውስጥ የንግድ ድርጅቶች፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች፣ አርብቶ እና አርሶ አደሮች ላይ ግብር በመጣል 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡን አስታውቋል።

የፑንትላንድ ጦር ታጣቂዎቹን ማሳደዱ የሚሳካለት ከሆነ የአየር ድጋፍ ጠቃሚ ይሆናል።

የአሜሪካው ጥቃት ብዙም ሳይቆይ የፑንትላንድ ፖሊስ የአይኤስ-ሶማሊያ ገዳይ ቡድን መሪ አብዲራህማን ሺርዋ አው-ሰይድ እጁን መስጠቱን ተናግሯል።

ነገር ግን ባለሙያዎች በሶማሊያ ያሉትን የአይኤስ ህዋሶች ለማደን እና ሌሎች ቡድኖች እንዳይፈለፈሉ ለማቆም እንዲህ ዓይነት አየር ጥቃት ተከታታይነት ያለው መሆን አለበት ይላሉ።

አሜሪካ እና ያልተጠበቀው መሪዋ በሶማሊያ ሰሜናዊ ምሥራቅ ተራሮች ላይ የቦምብ ድብደባ የመቀጠል ፍላጎት ይኑራቸው አይኑር ግልፅ አይደለም።