በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምንለጥፋቸው ምሥሎች ምን አደጋን ሊያስከትሉብን ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖፕ ፍራንሲስ ራፐሮች የሚያዘወትሩትን ግዙፍ ካፖርት እና ትልቅ መስቀል አድርገው የሚያሳየው ዲፕፌክ ምሥል አነጋጋሪ ከነበሩ ሐሰተኛ ምሥሎች መካከል ይጠቀሳል።
በመጀመሪያ ዕይታ ምሥሉ ሐሰተኛ መሆኑን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው።
ምሥሉ የተሠራው በሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያው ‘ሚድጆርኒ’ እንደሆነ ይፋ ከመደረጉ በፊት ምሥሉን የተመለከቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛ እንደሆነ አምነዋል።
ይህ ምሥል ሊያሳድር ከሚችለው በላቀ ጉዳት ያደረሱ ምሥሎች፣ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እና የድምጽ ቅጂዎች የወደፊቱን ዓለም አስፈሪ እንዳደረጉት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የስሎቫኪያ ምርጫ ቀናት ሲቀሩት ከተወዳዳሪዎቹ አንደኛው ‘ምርጫውን አጭበርብሬያለሁ’ ሲሉ የሚሰማበት የድምጽ ቅጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቀቀ።ድምጹ ዲፕፌክ መሆኑ ከመታወቁ በፊት ተወዳዳሪው ምርጫውን ተሸነፉ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የተለያዩ ግዛቶች የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ዲፕፌኮች ላይ ዕገዳ መጣላቸው ይታወሳል።
በአሪዞና ግዛት ውስጥ አንድ የ15 ዓመት ታዳጊ ለእናቷ ስልክ ደወለች። ሳግ እየተናነቃት ‘እማዬ አጋቾች ይዘውኛል’ አለች።
አጋቾቹ ልጅቷን ሲያስፈራሩዋት ድምጻቸው ይሰማል። እናት ልጇን ለማስለቀቅ 1 ሚሊዮን ዶላር ተጠየቀች።
እናትየው ያን ያህል ገንዘብ እንደሌላት በመንገር አጋቾቹን ተማጸነች። በድርድር ገንዘቡን ቀንሰው፣ 50 ሺህ ዶላር ካልከፈለች ልጅቷን እንደሚገድሉ ነገሯት።
ይህ ሁሉ ሲሆን ልጅቷ የዳንስ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበረች። እናትየው ልጇ አለመታገቷን ያወቀችው የልጇ የዳንስ መምህራን ደውለው ሲነግሯት ነበር።
‘አጋቾቹ’ የታዳጊዋን ድምጽ በዲፕፌክ በማስመሰል ነበር ለእናቷ የደወሉት።
በፕሪቶሪያ በሚገኘው ስቲቭ ቢኮ አካዳሚክ ሆስፒታል የምትሠራው ደቡብ አፍሪካዊት ዩሮሎጂስት ቢሮ ስትገባ ከሥራ ባልደረቦቿ ያልጠበቀችው ዜና ደረሳት።
‘ይህ መድኃኒት ውጤታማ እንደሆነ በጥናት አረጋግጫለሁ’ ስትል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋረ ነበር።
ይህን አለማድረጓን ብታውቅም የተንቀሳቃሽ ምሥሉ አሳማኝነት አስደነገጣት። በእሷ ስም እየተዋወቀ የነበረው ሐሰተኛ መድኃኒት ነበር።
በሆንግ ኮንግ የአንድ ተቋም ፋይናንስ ሠራተኛ የተቋሙ ዋና የፋይናንስ ኃላፊ ነው ብሎ ላመነው ሰው 25 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል።
ሠራተኛው ‘የፋይናንስ ኃላፊው’ በቪዲዮ ካዋራው በኋላ ትዕዛዙን እንደሰጠው አምኗል። ኋላ ላይ ፖሊስ ሲያጣራ ግን ገንዘቡን የተቀበሉት የበይነ መረብ መዝባሪዎች ናቸው።
የቪዲዮ ጥሪ የተደረገለትም በዲፕፌክ አለቃውን በማስመሰል ነበር።
አገራት ዲፕፌክን ለመቆጣጠር የተለያዩ ሕግጋት እያወጡ ይገኛሉ። ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ሐሰተኛ ምሥል በመጠቀም ሰዎችን መጉዳት ወይም ማታለል ያስቀጣል። ይህም ሐሰተኛ የእርቃን ምሥሎችን ይጨምራል።
ሐሰተኛ የእርቃን ምሥል ወይም ሐሰተኛ የልቅ ወሲብ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ በመልቀቅ ከሰዎች ገንዘብ ለማግኘት የሚሞክሩም አሉ።
የ76 ዓመቱ ሕንዳዊ እርቃኗን ካለች ሴት ጋር ምሥላቸው በዲፕፌክ ተሠርቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ተለጥፎ ራሳቸውን ለማጥፋት መሞከራቸው አነጋጋሪ ዜና ሆኖ ነበር።
በተለይም ታዳጊዎች ላይ የሚያደርሰው ጫና ቀላል አይደለም።
ሴቶች ላይ በበይነ መረብ ከሚደርሱ ጥቃቶች መካከል በዲፕፌክ የሚሠሩ ምሥሎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ይጠቀሳሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ግጭት ለማስነሳት ወይም ሁከትን ለማባባስ ሐሰተኛ ምሥሎች ሲሠራጩ ይስተዋላል።
እውነተኛ ምሥልን ወይም ተንቀሳቃሽ ምሥልን ከሐሰተኛው ለመለየት አስቸጋሪ እንደሆነ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችም ያስረዳሉ።
ሰዎች ያዩትን ወይም የሰሙትን ነገር በቀላሉ ለማመን ቅርብ መሆናቸውን እና ሐሰተኛ ምሥሎች፣ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንዲሁም የድምጽ ቅጂዎች ስሜትን በመኮርኮር ማሳመን የሚችሉ መሆናቸውን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰው ሠራሽ አስተውሎትና በሮቦቲክስ ፒኤችዲውን እየሠራ ያለው የ‘ጉዞ ቴክኖሎጂስ’ መሥራች ዳንኤል ጌታቸው ዲፕፌክ ጉዳቱ የሚጎላው “በቀላሉ የሚታመን” ስለሆነ ነው ሲል ያስረዳል።
በተለይም የፖለቲካ ይዘት ካለው “የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው” ይላል ባለሙያው።
ዲፕፌክ (Deepfake) የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤት ሲሆን ሐሰተኛ ምሥልን፣ ተንቀሳቃሽ ምሥልን ወይም ድምጽን ለእውነት በቀረበ ሁኔታ ማዘጋጀት ይችላል።
ዳንኤል እንደሚለው፣ ከምናውቀው እውነታ ጋር በጣም በሚመሳሰል መልኩ ስለሚሠራ ለመለየት ይከብዳል።
“የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ራሱ የሚታለሉበት ደረጃ ደርሷል” ሲል ያክላል።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ መረጃዎች ግጭት እና ነውጥ በሚያቀጣጥሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ዲፕፌክ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍ ያለ ነው።
“በቀላሉ በፎቶሾፕ የተቀናበረ ምሥል እንኳን ሰዎችን እያሸበረ ነው። በጣም ለእውነት የቀረበ ሲሆን ደግሞ አደጋው የባሰ ይሆናል” ይላል ዳንኤል።
ጥላቻ ከመንዛት እና ለነውጥ ከመጋበዝ በተጨማሪ በግለሰቦች ደረጃም ሕይወትን እስከማመሰቃቀል ደርሷል።
ለዚህም ነው እያንዳንዱን መረጃ በተገቢው መንገድ ማጣራት አስፈላጊ እንደሆነ ባለሙያው የሚመክረው።
በተይም ደግሞ ስሜትን የሚኮረኩሩ ወይም የሚያጋግሉ መረጃዎች ሲሆኑ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል።
ከዚህ በተቃራኒው የመዝናኛው ዘርፍ ዲፕፌክን በአወንታዊ መንገድ እየተጠቀመበት ነው።
ለምሳሌ የተዋንያንን የልጅነት ወይም የእርጅና መልክ ለማምጣት ዲፕፌክ ጥቅም ላይ ይውላል።
የ‘ፋስት ኤንድ ፊውሪየስ’ ተዋናይ ፖል ዋከር ፊልሙ ተቀርጾ ሳያልቅ ቢሞትም በዲፕፌክ ምሥሉን በመጠቀም ፊልሙ ተጠናቋል።
ዳንኤል እንደሚለው፣ ለቴክኖሎጂ እምብዛም ቅርበት በሌለው ማኅበረሰብ ውስጥ ዲፕፌክ የሚፈጥረው አደጋ ከፍተኛ ይሆናል።
“በገጠሪቱ ኢትዮጵያ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ይህን ብሏል የሚል ተንቀሳቃሽ ምሥል ቢወጣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ነው” ሲል የዲፕፌክ ውጤት የሚያስከትለውን ስጋት ያስረዳል።
እውነተኛውን ከሐሰተኛው ለይቶ ለማወቅ በጣም ፈታኝ በሆነ መንገድ እየተሠራ ከመምጣቱ አንጻር፣ ባለሙያዎች የጥንቃቄ ምክሮች ያስቀምጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድን መረጃ ያጋራውን አካል ማንነት ማጣራት እና በምሥሉ ወይም በተንቀሳቃሽ ምሥሉ እንደ ዓይን ወይም እጅ እንቅስቃሴ ያሉ ተፈጥሯዊ የማይመስሉ ነገሮችን መለየት በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ዲጂታል ዓለም በጣም እየተራቀቀ ሲመጣ እውነተኛው ዓለም የትኛው ነው? እስከምንል ድረስ ውዝግብ ውስጥ እንደምንገባ ዳንኤል ይናገራል።
ዲፕፌክ ገንዘብ ማግኛ፣ የፖለቲካ አቋም መግፊያ፣ አንዳች አሉታዊ ስሜት መፍጠሪያም እየሆነ ነው።
ዩኒቨርስቲዎች ለምርምር እንደ ማሳያ ሥራ አድርገው የሠሯቸውን መተግበሪያዎች በአሉታዊ መንገድ የሚጠቀሙ እንዲሁም በአንዳንድ መንግሥታት ድጋፍ የሚለቀቁም ዲፕፌኮች እንዳሉ ዳንኤል ያስረዳል።
ዲፕፌክን መቆጣጠር ካባድ የሆነውም በይበልጥ ለሰው ልጆች የቀረበ ቴክኖሎጂ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነ ያስረዳል።
ሰዎች፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሚፈልጉትን እየፈጠሩ እና ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ያላቸው ቁርኝት እየጨመረ ነው።
“ይሄ ቅርርብ ሲጨምር ቁጥጥር ማድረግን ከባድ ያደርገዋል” ይላል ባለሙያው።
“በፍጥነት የምናምነው ነገር ነው አጥፊያችን የሚሆነው” የሚለው ዳንኤል፣ ለማረጋገጥ መሄድ ያለብንን ርቀት ከግምት ሳናስገባ በቀጥታ ያንን ነገር ማመናችን ተጋላጭ እንደሚያደርገን ያስረዳል።
“መረጃዎችን ማጣራት አስፈላጊ ነው። ከተለያየ ምንጭ ለማጣራት መሞከር አለብን” ሲል ይመክራል።
ሌላው የጥንቃቄ ምክሩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምናጋራውን መረጃ ይመለከታል።
የዕለት ከዕለት ሕይወታችንን እና የግል መረጃዎቻችንን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በዘፈቀደ መልቀቅ ኋላ ላይ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችልም ይናገራል።
“ማኅበራዊ ሚዲያ ለእኛው መልሶ አደጋ ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ የምንለጥፈው ፎቶ፣ የምናጋራው መረጃ ‘ዲጂታል ፉት ፕሪንት’ ወይም ዲጂታል አሻራ ሆኖ ይቀመጣል” ይላል።
“ሲስተሙ ስለ እኛ ማንነት እና ስለ ፍላጎታችን ከምንተወው መረጃ ይማራል። ኋላ ላይ ተጋላጭ የሚያደርገንም ይህ ነው። መረጃችን ኢንተርኔት ላይ በበዛ ቁጥር የግል ሕይወታችን ውስጥ ገብቶ እስከማቃወስ ይደርሳል” ሲል ዳንኤል ያክላል።
በተለይም የሕጻናትን ምሥል እና ተንቀሳቃሽ ምሥል ተጠቅሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ገጽ ከፍቶ፣ ውሏቸውን እና ሕይወታቸውን ማስተላለፍ ያለውን አደጋ ይጠቅሳል።
“ሲስተሙ መልካቸውን፣ ድምጻቸውን እና ባሕሪያቸውን እንዲማር ያደርጋል። እነዚህ መረጃዎች ልጆቹን ዒላማ የሚያስደርጉ ወይም ቤተሰብን ማጥመጃ ሊሆኑ ስለሚችሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ሲልም ይመክራል።















