በገዛ ጓደኛዋ ፎቶዋ በረቀቀ ሁኔታ ተቀናብሮ የወሲብ ቪዲዮዎች ድረ-ገጽ ላይ የወጣባት ወጣት

mobile phone

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለንበት ዘመናዊ ዓለም እጅግ በረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማሳሪያነት ያልሆኑ እና ያልተፈጠሩ ነገሮች ተቀነባብረው እንደ እውነት እየቀረቡ ነው።

በዚህም በርካታ ነገሮች እየተፈጠሩ በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ሆነዋል። ለመዝናኛ እና ለትምህርታዊ አገልግሎቶች ከሚውሉት ባሻገር ግን ጉዳትን በሚያስከትል መልኩ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

በዚህም ምክንያት በ20ዎቹ የእድሜዋ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ጆዲ ለጠላቷ የማትመኘው ነገር ገጥሟታል።

ፎቶግራፏ የእውነት በሚመስል ሁኔታ ተቀነባብሮ ልቅ የወሲብ ፊልሞች በሚታዩባቸው ድረ-ገጾች ላይ ምሥሏ ተሠራጭቶ አግኝታዋለች። ከዚህ እኩይ ተግባር ጀርባ ያለው ደግሞ የቅርቤ የምትለው ጓደኛዋ መሆኑ ጉዳቷን የከፋ አድርጎታል።

ጆዲ ጉዷን ያወቀችው ከአንድ ከማታውቀው ሰው የተላከላትን ማስፈንጠሪያ [ሊንክ] ከተላከላት በኋ ነው።

ሊንኩን ስትከፍተው ልቅ የወሲብ ድርጊቶች ወደሚታይበት ድረ-ገጽ ያመራታል። በዚያ ያየችውን ማመን አልቻለችም። በእርሷ ምስል የተቀናበረቸ ሴት ከበርካታ ወንዶች ጋር ወሲብ ስትፈጽም ትመለከታለች።

ይህ ጊዜ ጆዲ ‘ዲፕ ፌክ’ መደረጓ ገባት። ዲፕ ፌክ የአንድን ሰው ምሥል ወይም ድምጽ ለእውነት በቀረበ ሁኔታ በማቀናበር የሚዘጋጅ ይዘት ነው።

እርሷን መጉዳት የፈለገ ሰው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቅሞ ከማኅበራዊ ሚዲያዎቿ ትክክለኛ ፎቶግራፎቿን ከወሰደ በኋላ በልቅ የወሲብ ፊልሞች ላይ ያሉ ሴቶችን ከአንገት በላይ በጆዲ ምሥል ተክቷቸዋል።

በዚህም በቪዲዮቹ ላይ ያሉት ሴቶች ፊት የጆዲ ሆኗል።

“ያየሁትን ማመን አቃተኝ። እየጮህኩ እና እያለቀስኩ የምመለከተውን ነገር ባለማመን ስሜት ውስጥ ነበርኩ። ይህ ሕይወቴን እስከ ወዲያኛው እንደሚያበላሽ ገብቶኝ ነበር” ትላለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጆዲ በኢንተርኔት አማካይነት እንዲህ አይነት ጥቃት ሲፈጸምባት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ከአራት ዓመታት ገደማ በፊት ጆዲ ሴተኛ አዳሪ እንደሆነች ከሚጠቁም ጽሑፍ ጋር የእርሷን ፎቶ የሚለጥፉ በርካታ የትዊተር አካውንቶች ነበሩ።

በአንዱ ልጥፍ ላይ “ጆዲን ብታገኛት ምን ታደርጋታለህ” የሚል ጽሑፍ ጆዲ እርቃኗን ያሳያል።

ጆዲ ከአንገቷ በላይ ያለው ምሥል ከማኅበራዊ ገጿ ተወስዶ የተቀረው አካል ደግሞ ከሌላ ሴት ከተወሰደ በኋላ ተቀነባብሮ ትዊተር ላይ መለጠፉን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባትም።

ጆዲ እርሷን ለመጉዳት ይህን የሚያደርግ ሰው መኖሩን ተገንዝባለች። ጥያቄ የሆነባት ግን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ፎቶግራፎቿን የምታጋረው ከቤተሰብ አባላት እና ከቅርብ ጓደኞች ጋር ብቻ ሆኖ ሳለ እኔን መጉዳት የፈለገው ሰው ፎቶግራፎቼን እንዴት አገኘ የሚለው ነበር።

በዚህ መሃል ምስሏን የሚለጥፈው የትዊተር አካውንት እርሷ የምታውቃቸው ሌሎች ሴቶችን ምስልም እንደሚለጥፍ ተመለከተች።

በዚህ ወቅት ከዚህ ተግባር ጀርባ ያለ ሰው እርሷን እና እርሷ የምታውቃቸውን ሰዎች ምሥል የተለጠፉ ሴቶችን የሚያውቅ መሆን አለበት ብላ ገመተች።

ጆዲ በእነዚህ ምሥሎች ላይ ያሉ ሌሎች ሴቶችን ማግኘት ጀመረች። ከእነዚህ መካከል አንዷ ዴዚ ነበረች።

“ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት ህመም ነበር የተሰማኝ። ጉዳዩን በጥልቀት በመረመርን ቁጥር ብዙ ምሥሎችን ማግኘት ጀመርን” ትላለች ዴዚ።

ጆዲ እና ዴዚ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሁለቱም ጓደኛ የሆነ እና ፎቶግራፋቸውን ሊያገኝ የሚችለውን ሰው ለመለየት ጥረት ጀመሩ።

በመጨረሻም ከዚህ ተግባር ጀርባ ያለው የጆዲ የቀድሞ ፍቅረኛ መሆን አለበት ሲሉ ደመደሙ።

ጆዲ የቀድሞ ፍቅረኛዋን ይህን እንዴት ታደርጋለህ ስትል ለማፋጠጥ ሞከረች። ሁለቱም ሴቶች የጆዲን የቀድሞ ፍቀረኛ “ብሎክ” አደረጉት።

ለጥቂት ወራት ምስላቸውን ይዘው የሚወጡ ልጥፎች ቆሙ።

ቆመው ግን አልቀሩም።

ከጥቂት ወራት በኋላ ጆዲ ማንነቱን መግለጽ ካልፈለገ ሰው የኢሜይል መልዕክት ይደርሳታል።

ሊንኩን ስትከፍት የእርሷ ምሥል ያረፈበት ልቅ ምሥል ትመለከታለች።

ይህ ምሥሏ ያለበት ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያዋ ላይ የለጠፈችው የቀድሞ ፍቅረኛዋን ‘ብሎክ’ ካደረገች በኋላ ስለነበረ ይህን ሁሉ ሲፈጽም የነበረው የቀድሞ ፍቅረኛዋ ሳይሆን ሌላ ሰው መሆኑን ተገነዘበች።

ጆዲ እና ዴዚ ዳግም ተገናኝተው ይህን ተግባር ሊፈጽሙ አይችሉም ያሏቸውን ቤተሰብ እና ጓደኛ መዘርዘር ጀመሩ። ይህ አካሄዳቸው የሚጠረጥሩትን ሰው መለየት አላስቻላቸውም።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ማንነቱን መግለጽ ያልፈገው ግለሰብ በድጋሚ ሌላ ሊንክ በኢሜይል ይልክላታል።

ይህ ሊንክ ሌላ የተቀነባበረ ምሥል ይዞ ብቅ ይላል። የእርሷ ትክክለኛ ፊት በሌላ ሴት ሰውነት ላይ ተገጥሞ ተመለከተች።

ጆዲ ምስሏን ስለጥፍ ከነበረው አሌክስ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ጆዲ ምስሏን ስለጥፍ ከነበረው አሌክስ ጋር ካምብሪጅ በሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ ፊት ለፊት

ምሥሉን እንደተመለከተች አንድ ነገር ተረዳች።

በዚህ በዲፕ ፌክ የተቀናበረ ምሥል ላይ ጥቅም ላይ የዋለው ፎቶግራፏ የት እና ከማን ጋር እንደተነሳችው ታስታውሳለች።

ያን ፎቶ ኬምብሪጅ ከሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ ፊት ለፊት የተነሳቸው የቅርብ ጓደኛዬ ከምትለው አሌክስ ዎልፍ ጋር ነው። ይህን ፎቶ ከአሌክስ ጋር ከተነሳች በኋላ ምሥሉን ያጋራችውም ለእርሱ ብቻ ነው።

“ማመን አልቻልኩም” ትላለች ጆዲ የቅርብ የምትለው ጓደኛዋ ሕይወቷን ሊያመሰቃቅል ከሚችል ድርጊት ጀርባ መኖሩን ስትረዳ።

ማንነቴ በዚህ መልኩ ሲጠፋ የሚያጽናናኝ አሌክስ ነበረ ትላለች።

“ሴቶች በተለይም በኢንተርኔት አማካይነት የሚደርስባቸውን ጉዳቶች ጠንቅቆ ያውቃል። የሴቶች መብት ተሟጋች አድርጌ ነበር የምቆጥረው” ትላለች ብዙ ሰለማታውቀው “የቅርብ ጓደኛዋ” ስትናገር።

ጆዲ ጉዳዩን ወደ ሕግ ከወሰደችው በኋላ የ26 ዓመቱ አሌክስ ዎልፍ የጆዲን ጨምሮ የ15 ሴቶችን ፎቶግራፍ ኢንተርኔት ላይ በመለጠፉ ጥፋተኛ ተባለ።

ለ20 ሳምንታት በእስር እንዲያሳልፍ እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች ለእያንዳንዳቸው 100 ፓውንድ እንዲከፍል ተፈረደበት።

ዎልፍ “በድርጊቱ በጣም ማፈሩን እና ማዘኑን” ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በየቀኑ ስላደረስኩት መከራ አስባለሁ። በቀሪው ሕይወቴ ስፀፀት እንደምቀጥል ምንም ጥርጣሬ የለኝም” በማለት ጆዲን እና ሌሎች ሴቶችን ይቅርታ ጠይቋል።

ለጆዲ ግን ይህን የፈጸመው የቅርቤ የምትለው ጓደኛዋ መሆኑ “የመጨረሻ ክህደት እና ውርደት” ሆኖባታል።