ፌስቡክ ላይ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ እንደሚችሉ የሚጠቁም ‘ፖስት’ ስናይ ምን እናድርግ?

ራስን ለማጥፋት ማሰብ

የፎቶው ባለመብት, VLADIMIR VLADIMIROV

ናዝራዊት ተስፋዬ ትባላለች። በፌስቡክ ገጿ ላይ “አንዳንዴ. . .በቂ ነው” የሚል ጽሑፍ አጋራች። ከጽሑፉ ጋር የባለ መስመር ወረቀት ምሥል አያይዛም ለጥፋለች።

ወረቀቱ መግቢያ ላይ “Dear Lord” የሚል ጽሑፍ ይነበባል። መጨረሻው ላይ ደግሞ “Amen” ተብሎ በጥቁር እስክሪብቶ ተጽፏል። ወረቀቱ መሃል ላይ የእንባ ጠብታዎች ይታያሉ።

ናዝራዊት ይህንን ጽሑፍ እና ምሥል ባጋራች በሁለት ቀናት ልዩነት “ብንሄድ ይሻለናል. . .” የሚል ጽሑፍ ለጠፈች። ከዚያ በኋላ ሕይወቷን ማጥፋቷ ተሰማ።

ቢቢሲ ናዝናዊት ራሷን ማጥፋቷን ከቤተሰቦቿ ማረጋገጥ ባይችልም በስፋት ግን እየተነገረ ነው።

ይህ አሳዛኝ ክስተት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ በየዓመቱ 700 ሺህ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ።

ራሳቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች ባልተናነሰ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ሰዎች እንዳሉ እና አንድ ጊዜ ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ ሰዎች በድጋሚ ራሳቸውን ለማጥፋት የመሞከር ዕድላቸው እንደሚሰፋም የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።

ከ15 ዓመት እስከ 29 ዓመት ባሉ ሰዎች ዘንድ ራስን ማጥፋት አራተኛው ለሞት የሚዳርግ ምክንያት ነው።

77 በመቶ የሚሆነው ራስን ማጥፋት የሚከሰተው ደግሞ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ በዓለም ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ራሳቸውን የሚያጠፉባቸው መንገዶች መርዝ መጠጣት፣ ራስን ማነቅ እና ራስን በጥይት መምታት ናቸው።

ሰዎች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የስንብት የሚመስል መልዕክት ካጋሩ በኋላ ራሳቸውን እንዳጠፉ ይሰማል።

ከእነዚህ አንዷ ደግሞ ናዝራዊት ናት። ናዝራዊት የጽሑፍ መልዕክቶቹን እና ምሥሉን ካጋራች በኋላ ነው ሕይወቷን እንዳጠፋች የተነገረው።

ለመሆኑ ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋት ሐሳብ ውስጥ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ እንደሚችሉ ጠቋሚ የሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎች አልያም ምሥሎች የሚያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችስ ምን ማድረግ አለባቸው?

ይህንን በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሥነ ልቦና ባለሙያ ቴዎድሮስ ድልነሳ፣ በአብዛኛው ራስን የማጥፋት ሐሳብ እና ድርጊት ከአእምሮ ጤና መዛባት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።

“ራስን የማጥፋት ሐሳብ፣ ራስን ስለማጥፋት ማሰላሰል እንዲሁም ድርጊቱም ከአእምሮ ሕመም ወይም ከአእምሮ ጤና መዛባት ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ።

ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚደርሱት በአንዳች የአእምሮ ጤና መዛባት ምክንያት እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።

የአእምሮ ጤና መዛባት እንዳለ ሆኖ ራስን ለማጥፋት ገፊ የሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች እንዳሉ ይናገራሉ። በተለይም ደግሞ ስሜትን መግራት ወይም ስሜትን መቆጣጠር የሚያቅታቸው ሰዎች ቶሎ ቅጽበታዊ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ።

“ይህ ውሳኔ ብዙውን ጊዜ ከድባቴ ጋር አብሮ ስለሚሄድ ለረዥም ጊዜ አሰላስለውት ነው ሰዎች ራስ ማጥፋት ላይ የሚደርሱት” ሲሉ ቴዎድሮስ ያስረዳሉ።

ድባቴ ወይም Depression ውስጥ ያሉ ሰዎች ራስን ወደ ማጥፋት ሊሄዱ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ራስን ማጥፋትን ከአሳሳቢ የጤና ችግሮች መካከል አካቶታል።

ሰዎች ከባድ በሆነ የመኖር ስቃይ ስሜት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ከምክንያታዊ አስተሳሰብ እና ውሳኔ ውጪ እንደሚሆኑ የሚያስረዱት ቴዎድሮስ፣ በዚህ ወቅት ሰዎች ሊያሳዩዋቸው ከሚችሉ ምልክቶች መካከል እርዳታ እንዲደረግላቸው እጅ መዘርጋት መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህ በእንግሊዘኛው “Cry for help” የሚባለው እና ሰዎች እርዳታ እንዲደረግላቸው እጃቸውን የሚዘረጉበት ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ሊታይ እንደማይችልም አያይዘው ይናገራሉ።

“እንደተለመደው አይነት ‘እርዱኝ’ ሳይሆን የስንብት የሚመስሉ መልዕክቶች ይተዋሉ። ለምሳሌ ደውለው እንዴት ናችሁ? ብለው ከጠየቁ በኋላ ስንብት የሚመስል ነገር መናገር ወይም የድሮውን አንስቶ ‘ድሮ'ኮ እንደዚህ ነበር’ ሊሉ ይችላሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን Facebook ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በFacebook. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የFacebook ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

የማኅበራዊ ሚዲያ ‘ስንብት’

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሕይወትን ስለማጥፋት የሚያሰላስሉ ሰዎች እርዳታ እንዲደረግላቸው እጃቸውን ከሚዘረጉበት መንገድ አንዱ ማኅበራዊ ሚዲያ ሆኗል።

“ድሮ ደብዳቤ ይተዉ እንደነበረው በዚህ ዘመናዊ ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያ የስንብት ደብዳቤ ሊጻፍ ይችላል” ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ሰዎች ከተለመደው በተለየ ሁኔታ መልዕክት እያስተላለፉ እንደሆነ ወይም ራሳቸውን ስለማጥፋት እያሰላሰሉ እንደሆነ ለማወቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚጽፉት ጽሑፍ ማወቅ ይቻላል? የሚል ጥያቄ ለባለሙያው ሰንዝረናል።

እሳቸው እንደሚሉት፣ ሰዎች በአእምሯቸው እየተመላለሰ ያለው ሐሳብ ወይም ስሜት ራስን ወደማጥፋት የሚያመራ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።

“ትልቁ ምልክት የባህሪ ለውጥ ነው። የባህሪ እና የአስተሳሰብ ለውጥ ያሳያሉ። [የማኅበራዊ ሚዲያ] ጽሑፉ ላይ በጣም ጨለምተኛነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ብቸኝነት፣ ሕይወት ዋጋ የለውም የሚል ስሜት፣ መኖር ምን ያደርጋል? የሚል ስሜት፣ እኔ ብቻ ሳልሆን ዓለምም ዋጋ ቢስ ነው የሚል ስሜትን የመሰሉ ዕይታዎች ይታያሉ።”

እነዚህን ምልክቶች ባለሙያው “በድንገት እና በብዛት የሚከሰቱ ምልክቶች” ሲሉ ይገልጿቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ አብዛኞቹ ሰዎች ራሳቸውን ወደ ማጥፋት የሚሄዱት ሕይወት የሚፈጥረውን ጫና ለመቋቋም በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ነው።

የገንዘብ ችግር፣ የጤና እክል፣ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ የሚፈጠር ምስቅልቅል፣ የጥቃት ሰለባ መሆን፣ በጦርነት ወይም ግጭት ውስጥ ማለፍ፣ የብቸኝነት ስሜት፣ መገለል እና የሚወዱትን ሰው ማጣት በምክንያትነት ከተዘረዘሩት መካከል ይጠቀሳሉ።

በእነዚህ ወይም በሌላ ራስን ወደ ማጥፋት የሚገፋፉ ስሜቶች ውስጥ ሆነው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጽፉ ሰዎችን ከጽሑፋቸው መረዳት እንደሚቻል የሥነ ልቦና ባለሙያው ቴዎድሮስ ያስረዳሉ።

“በተለይም የምናውቃቸው ሰዎች ከሆኑ በጽሑፋቸው ለይተን ማወቅ እንችላለን” ይላሉ።

ሌላው ባለሙያው እንደ ምልክት የሚጠቅሱት ለሞት ትልቅ ዋጋ ሰጥቶ መጻፍን ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሞተ ሲባል ጤናማ በሚባል የአእምሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ‘ነፍሱ በሰላም ትረፍ’ የሚል የሐዘን መልዕክት ሲጽፉ ይስተዋላል።

ምናልባትም ራሳቸውን ስለማጥፋት እያሰቡ ያሉ ሰዎች ግን የሞተውን ሰው ‘ተገላገለ’፣ ‘እሱስ አረፈ’፣ ‘ወደዚያው መሄድ ነው’ በሚሉ ሞትን ዋጋ በሚሰጡ የተጋነኑ ቃላት መግለጽ ሊታይ ይችላል።

መቆዘም፣ ብቸኝነት፣ ተስፋ መቁረጥ ሌላው የሚታዩ ምልክቶች ናቸው።

ምልክቶቹ ሁሌም ግልጽ ናቸው ማለት ግን አይደለም። “አንዳንዴ ምልክቱ ምሥጢራዊ ይሆናል። ግልጽ ካልሆነ ደግሞ የዚያን ሰው ሁኔታ ማጣራት ይኖርብናል” ይላሉ።

ምንድን ነው የተከሰተው? ምን ልርዳህ ወይም ምን ልርዳሽ? የሚለው ነገር በራሱ ችግሩን መቅረፍ ባይችልም እንኳን ሰዎቹን እንደሚረዳቸው ባለሙያው ያስረዳሉ።

“ከዚያ በኋላ ለቤተሰብ ወይም ሌላ ቅርብ ለሆነ ሰው ማሳወቅ ያስፈልጋል። ሰዎች ራሳቸውን ሊጎዱ የሚችሉበትን መንገድ ማስወገድ ያስፈልጋል” ይላሉ።

ምን ይደረግ?

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ምልክቶች ሲታዩ፣ የተፈጠረውን መጠየቅ እና የእርዳታ እጅ መዘርጋትን ተከትሎ ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለሌሎች የቅርብ ወዳጆቻቸው ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

በዚህ መንገድ ሰዎቹ ራሳቸውን ሊጎዱባቸው የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ እንደሚቻል ይገልጻሉ።

“ራሳቸውን ሊጎዱባቸው የሚችሉ ነገሮች መወገድ አለባቸው። ምላጭ፣ ገመድ፣ ሽጉጥ ወይም መድኃኒቶች ማስወገድ ማለት ነው።”

በቀጣይም የቅርብ ክትትል ማድረግ እና አብሮ መሆን እንዳለ ሆኖ በአፋጣኝ ወደ አእምሮ ሕክምና ባለሙያ መወሰድ እንዳለባቸው ባለሙያው ይመክራሉ።

ሰዎቹ ወደ ሕክምና መሄድ አልፈልግም ቢሉም እንኳን የግድ ወደ ሕክምና እንዲሄዱ መደረግ እንዳለበት ያስረግጣሉ።

“ምክንያቱም ራስን የመጉዳት ሐሳብ የጤንነት አይደለም” ሲሉም ያክላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው፣ ሰዎች ሕይወታቸውን ሊያጠፉባቸው የሚችሉ መሣሪያዎችን ማሸሽ እንዳለ ሆኖ፣ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ መርዳት ቁልፍ ነገር ነው።

ከጤና ተቋማት ባሻገር የትምህርት ቤቶችን፣ የመሥሪያ ቤቶችን እንዲሁም ሌሎች ተቋማትንም ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነም ተገልጿል።

ራስን ማጥፋት ጨምሮ የአእምሮ ሕመም በአጠቃላይ እምብዛም የማይወራለት እና ትኩረትም የተነፈገው መሆኑን ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ራሳቸውን ስለማጥፋት የሚያስቡ ሰዎች ወይም ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ ሰዎች ስለ ችግሩ በግልጽ የማያወሩትም ለዚሁ ነው። ይህም የሚያስፈልጋቸውን ማኅበራዊ እና የሕክምና ድጋፍ እንዳያገኙ መሰናክል ይሆናል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው፣ እስካሁን ድረስ ራስን ማጥፋት የመከላከል አሠራርን በጤና ማዕቀፋቸው ውስጥ ያካተቱ አገራት ጥቂት ናቸው።

ብሔራዊ የራስ ማጥፋት መከላከያ ማዕቀፍ ያላቸው 38 አገራት ብቻ ናቸው።

በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ራስን የማጥፋት አሃዝ በዓመት ከ100 ሺህ ሕዝብ መካከል ከ5.02 እስከ 15.71 እንደሚደርስ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ ያለው ዓመታዊ ራስን የማጥፋት መጠን መካከለኛ ሲሆን፤ በዓመት ከ100,000 ሕዝብ መካከል ራስን የማጥፋት ምጣኔ 9.63 ነው።

ማኅበሩ እንደሚለው በዚህ አሃዝ መሠረት በየቀኑ 30 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ።