አሜሪካዊው ታዳጊ በእርቃን ፎቶ ምክንያት ራሱን እንዲያጠፋ ያደረጉት ናይጄሪያዊያን ወንድማማቾች ተፈረደባቸው

አንድ የ17 ዓመት አሜሪካዊ ታዳጊን በእርቃን ፎቶ ያጭበረበሩት ሁለት ናይጄሪዊያን ወንድማማቾች የ17 ዓመት እስር ተፈደረባቸው።
የሌጎስ ነዋሪ የሆኑት ኦጎሺ የተባሉት ወንድማማቾች ጆርዳን ዲሜይ የተባለው አሜሪካዊ እርቃን ምስል እንዲልክላቸው ያደረጉት በበይነ-መረብ ሴት መስለው በመቅረብ ነው።
ወጣቱ አሜሪካዊ ከአጭበርባሪዎቹ ጋር በኢንስታግራም ካወራ ከስድስት ሰዓታት በኋላ ራሱን አጥፍቷል።
አሜሪካ ውስጥ የሳይበር ወንጀል እየበረከተ የመጣ ሲሆን በተለይ ናይጄሪያዊያን ስማቸው በስፋት ይነሳል።
ሁለቱ ናይጄሪያዊያን ወንድማማቾች በዩናይትድ ስቴትስ በእርቃን ምስል በማስገደድ በተደረገ ማጭበርበር ፍርድ የተሰጠባቸው የመጀመሪያዎቹ ሆነዋል።
የጆርዳንን ምስል ይዛ ችሎት የቀረበችው እናቱ ጄን ቡታ “በጣም ተሰብሪያለሁ” ስትል በእንባ ታጅባ ቃሏን ስትሰጥ ታይታለች።
ምንም እንኳ ወንጀለኞቹ ፍርድ ማግኘታቸው መልካም ነው ብትልም ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ምንም ዓይነት ጥሩ ነገር እንደማይገኝ ተናግራለች።
ጆርዳን ዲሜይ በሚሺጋን ግዛት በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት መልካም ስም ያለው ታዳጊ ነበር።
የ24 ዓመቱ ሳሙዔል ኦጎሺ እና የ21 ዓመቱ ሳምሶን ኦጎሺ ኢንስታግራም ተጠቅመው በጆርዳን ዕድሜ ያለች ቆንጆ ሴት መስለው ነው ማውራት የጀመሩት።
ከታዳጊው የእርቃን ምስሎች ከተላከላቸው በኋላ ገንዘብ ካልተላከላቸው ካልላከላቸው የእርቃን ምስሎቹን በበይነ መረብ እንደሚለቁ በማስፈራራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች ወስደውበታል።

የፎቶው ባለመብት, Nigeria Police
ጆርዳን የሚችለውን ያክል ገንዘብ ከላከላቸው በኋላ ፎቶዎቹን የሚያሰራጩ ከሆነ ራሱን እንደሚያጠፋ አስጠንቅቋቸው ነበር።
ወንጀለኞቹ ለዚህ ማስጠንቀቂያ “ጥሩ. . . ቶሎ አድርገው። ካልሆነ ቶሎ እንድታደርገው እናደርጋለን” ማለታቸው ተመልክቷል።
የሟች አባት የሆነው ጆን ዳንዔል ሚሺጋን ለሚገኘው ማርኩዌት የፌዴራል ችሎት ሲናገር ልጁን አልጋ ክፍል ውስጥ ሞቶ ካገኘው ጀምሮ ሲያቃዠው ነው የኖረው። አክሎ ቤተሰቡ ከዚህ ትውስታ ለማምለጥ በሚል ቤት እንደቀየረ ተናግሯል።
ሁለቱ ወንድማማቾች ባለፈው ሚያዚያ በሚሺጋን እና በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች ተመሳሳይ የማጭበርበር ድርጊት መፈፀማቸው አምነው ጥፋተኛ መሆናቸውን ተቀብለዋል።
38 አሜሪካዊያን የወጣቶቹ ሰለባ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 13 የሚሆኑት ታዳጊዎች መሆናቸው ተዘግቧል።
ወንድማማቾች ብርቱካናማ ቦላሌ ለብሰው እጃቸው በካቴና ተጠፍሮ ነው ችሎት ፊት የቀረቡት።
አቃቤ ሕግ ወንድማማቾቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በዕፅ መጠቀም እና ናይጄሪያ ውስጥ ባለው የማጭበርበር ባሕል ምክንያት ነው ብሏል።
የችሎቱ ዳኛ ወንድማማቾቹ ጆርዳን መሞቱን ሰምተው እንኳ ሌሎች ግለሰቦችን ሰለባ ማድረጋቸው የፈፀሙት ወንጀል “ለነብስ ቅንጣት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ወንድማማቾቹ የጆርዳንን ቤተሰብ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ይህ የመጀመሪያው በተባለ የፍርድ ሂደት የአሜሪካ ፖሊስ ወጣቶቹን አሳዶ ሌጎስ ድረስ በመሄድ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው በኋላ ነው ለፍርድ ሂደት ይዟቸው የተመለሰው።
በጆርዳን ሞት እጁ አለበት የተባለ ሌላ ግለሰብ እንዲሁም በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠረ አንድ ተጨማሪ ግለሰብ ከናይጄሪያ ተይዘው ሊመጡ ይችላሉ እየተባለ ነው።
የሕግ አካላት እና የተለያዩ ጥናቶች ናይጄሪያ መሰል የማጭበርበር ወንጀለኞች የሚፈፀሙባት ሀገር ናት ይላሉ።
ባለፈው ሚያዚያ አንድ አውስትራሊያዊ ታዳጊ ተማሪ ራሱን ካጠፋ በኋላ ሁለት ናይጄሪያዊያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ሁለት ናይጄሪያዊያን የ15 ዓመቱ አሜሪካዊ እና የ14 ዓመቱ ካናዳዊ ራሳቸውን ለማጥፋታቸው ምክንያት ናቸው ተብለው ፍርዳቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።












