የተባበሩት መንግሥታት በሱዳን ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ኃይል እንዲሰማራ ጠየቀ

የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብድል ፋታህ አል ቡሩሃን
የምስሉ መግለጫ, የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብድል ፋታህ አል ቡሩሃን

የተባበሩት መንግሥት የባለሙያዎች ቡድን ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እየደረሰ ባለባት ሱዳን “ገለልተኛ ኃይል” እንዲሰማራ ጠየቀ።

የባለሙያ ቡድኑ የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅ አልቻሉም ብሏል።

17 ወራት ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወትን ከመቅጠፉ በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በማፈናቀል በአገሪቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የሱዳን ጦርነት የተጀመረው በአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብድል ፋታህ አል ቡሩሃን እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) መካከል ሱዳን እንዴት ትመራ በሚለው ላይ መግባባት ሳይደረስ ከቀረ በኋላ ነው።

ይህ ጦርነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰ ስለመሆኑ በሰብዓዊ መብት ቡድኖች ሲገለጽ ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት እውነታ አጣሪ ቡድን ባወጣው መግለጫ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱም ቡድኖች ከጦር ወንጀል ጋር ሊስተካከል የሚችል በደል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስለመፈፀማቸው ማስረጃ አለ ብሏል።

በመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ላይ ሱዳን “ሰላማዊ ዜጎች ከፍተኛውን ዋጋ የሚከፍሉባትለ፤ በትርምስ ውስጥ ያለች አገር” ተብላ ተገልጻለች።

ባለፉት 17 ወራት በጦርነቱ ምክንያት አብዛኛዎቹ ሰላማዊ የሆኑ ከ18 ሺህ የማያንሱ ሰዎች መገደላቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።

በድርጅቱ ሪፖርት ላይ ሁለቱም ወገኖች ዒላማቸውን ያልጠበቁ ጥቃቶችን በመኖሪያ መንደሮች መፈጸማቸውን እንዲሁም ጾታዊ ጥቃቶች ማድረሳቸው ተመልክቷል።

የመንግሥታቱ የባለሙያዎች ቡድን የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዦች ተዋጊዎቻቸው ሕጋዊ ካልሆኑ ተግባራት እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፉ ጨምሮ ጠይቋል።

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት

በኦማር አል በሽር ጠንከራ ክንድ ስር የነበረችው ሱዳን፤ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ዳርፉር በነበረው ጦርነት ስሟ በመጥፎ ቢነሳም አንጻራዊ መረጋጋት የነበራት አገር ነበረች።

አል-በሽር በሕዝባዊ አብዮት ከመንበራቸው ከወረዱ በኋላ አገሪቱ በሥልጣን ሹክቻ ተወጥራ ቆይታ ነበር። ከዚያም የካርቱም እና ኦማድሩማን ጎዳናዎች የሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት በሚጠይቁ ዜጎች ይጥለቀላቁ ጀመር።

አል-በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ባሉት ዓመታት አለመረጋጋት፣ ፖለቲካዊ ውጥረት እና የኑሮ ውድነት ሕዝቡን ከማማረሩ ባሻገር ሚያዚያ 2016 ዓ.ም. አገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አበደል ፋታህ አል ቡሩሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ለማሸማገል በአሜሪካ፣ በሳዑዲ እና ግብጽ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላመጡም።