በኬንያ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በተነሳ እሳት 17 ተማሪዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በማዕከላዊ ኬንያ በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ በተነሳ እሳት 17 ተማሪዎች ሞቱ።
ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም. በተነሳው ቃጠሎ ከሞቱት 17 ተማሪዎች በተጨማሪ ሌሎች 14 ተማሪዎች በቃጠሎ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሀገሪቱ ፖሊስ ገልጿል።
በዚህም ምክንያት የሟቾች ቁጥር ሊጨመር እንደሚችል ተሰግቷል።
በማዕከላዊ ኬንያ ኜሪ ግዛት በሚገኘው ሂልሳይድ ኢንዳራሻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የእሳት አደጋው እንዴት እንደተነሳ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የፖሊስ ቃል አቀባይ ሬሲላ ኦንያንጎ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
አደጋውን “አሰቃቂ እና አሳዛኝ” ብለው የገለጹት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ መንስዔው እንዲጣራ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
“ለእሳት አደጋው ተጠያቂ የሆኑ በሕግ ይጠየቃሉ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የእሳት አደጋውን መነሻ የሚያጣራ መርማሪ ቡድን አደጋው ወደደረሰበት ግዛት መጓዙን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል።
የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል አጃንስ ፈረንስ ፕሬስ እንደተናገሩት፤ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ተማሪዎች ማንነታቸውን መለየት በማይቻልበት ሁኔታ አካላቸው ተቃጥሏል።
እስካሁን ድረስ የሟቾቹ ማንነትም ይሁን ጾታ እና ዕድሜ አልተገለጸም።
የኬንያ ቀይ መስቀል በበኩሉ አደጋውን ተከትሎ ለተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
በሀገሪቱ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የእሳት አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
እአአ 2017 ላይ በሞይ የሴቶች ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ ሆነ ተብሎ በተለኮሰ እሳት 10 ተማሪዎች ሕይወታቸው አጥተዋል።
ከመዲናዋ ናይሮቢ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ማቻኮስ ግዛት ደግሞ ከ20 ዓመታት በፊት በደረሰ የእሳት አደጋ ከ67 በላይ ተማሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።












