ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ለአራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት የኦነግ አመራሮች በዋስ ተለቀቁ

ከግራ ወደ ቀኝ፡ ዳዊት አብደታ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ኦልጅራ (ዶ/ር)፣ ገዳ ገቢሳ (ዶ/ር)፣ ኬነሳ አያና እና አብዲ ረጋሳ።

የፎቶው ባለመብት, Lammii Gammachuu

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ፡ ዳዊት አብደታ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ለሚ ቤኛ፣ ገዳ ኦልጅራ (ዶ/ር)፣ ገዳ ገቢሳ (ዶ/ር)፣ ኬነሳ አያና እና አብዲ ረጋሳ።

ሰባት ከፍተኛ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አመራሮች ከአራት ዓመታት እስር በኋላ ክስ ሳይመሰረትባቸው በዋስ ተለቀቁ።

ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. ከእስር የተለቀቁት የኦነግ አመራሮች አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ኬነሳ አያና፣ ለሚ ቤኛ፣ ዶ/ር ገዳ ኦልጅራ፣ ገዳ ገቢሳ እና ዳዊት አብደታ ናቸው።

እነዚህ አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት ከእስር እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ተወስኖ የነበረ ቢሆንም በእስር ቤት እንዲቆዩ ስለመደረጋቸው ጠበቆቻቸው እና ፓርቲው ሲገልጹ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያለ ክስ በእስር የቆዩ የኦነግ ፓርቲ ፖለቲከኞች ከእስር እንዲለቀቁ ሲጠይቁ ነበር።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ፖለቲከኞቹ ከእስር እንዲለቀቁ በጠየቀበት መግለጫ ፍርድ ቤት ግለሰቦቹ ከእስር እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም መንግሥት ግን ምንም አይነት ሕጋዊ ምክንያት ሳይኖረው አስሮ ይዟል ብሎ ነበር።

ክስ ሳይመሰረትባቸው አራት ዓመት ለሚሆን ጊዜ በእስር የቆዩት ፖለቲከኞቹ “ቡራዩ ከሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በዋስ መለቀቃቸውን” የፓርቲው ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ በማሕበራዊ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ለሚ ገመቹ “የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ፖለቲከኞች እንደለቀቀው ሁሉ በኦሮሚያ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የኦነግ አባላትን እና ደጋፊዎችን እንዲለቅ እና የተዘጉ የፓርቲው ቢሮዎችን ከፍቶ ሥራችንን እንድንሰራ መንገድ እንዲከፍት እንጠይቃለን” ብለዋል።

ከፍተኛ የኦነግ አመራሮቹ የፖሊስ አባልን በመግደል እንዲሁም ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ትናንት ከእስር ከተለቀቁት መካከል አንዱ የሆኑት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አብዲ ረጋሳ ጥር 2012 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ቡራዩ ውስጥ የፖሊስ አባል ገድለዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ያሉበት ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ ቆይተው ነበር።

ለሚ ቤኛ፣ ዳዊት አብደታ፣ ኬነሳ አያና እና ሚካኤል ቦረን ደግሞ ሐምሌ 2012 ዓ.ም. የአርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከበርካታ ፖለቲከኞች ጋር ነበር በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ከሰባቱ ፖለቲከኞች ረዘም ላለ ጊዜ በእስር የቆዩት አብዲ ረጋሳ እና ሚካኤል ቦረን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው።

የእነዚህ ፖለቲከኞች ነጻ መውጣት የተሰማው መንግሥት ለ2017 አዲስ ዓመት እስረኞችን “በምህረት” እየለቀቀ ባለበት ጊዜ ነው።

ይሁን እንጂ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች የተለቀቁት በምህረት ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።