በትግራይ በተካሄዱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ የቀረበባቸው ኮሎኔል ተወልደ ምን ይላሉ?

የፎቶው ባለመብት, SM
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸውን በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የወርቅ ማዕድን ማውጣት ላይ እንደተሰማሩ ገልጸው ነበር።
ከእነዚህ መካከል የትግራይ ኃይሎች የመረጃ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል ተወልደ ገብረ ትንሳዔ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል በሚል ስማቸውን ጠቅሰው ከስሰዋቸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ በፕሬዝዳንቱ ስር በነበረ ኮሚቴ እንደተጠና የተነገረ ባለ 66 ገጽ ጥናት የኮሎኔሉ ስም በተመሳሳይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አንስቶ ከስሷቸዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሰጡት ቃለ መጠይቅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ በቀድሞ ፕሬዝዳንቱ እንደወጣ የሚነገርለት ሰነድ ያረጋገጠ ቢሆንም የመንግሥት ሰነድ በማኅበራዊ ሚድያ እንዲበተን ማድረጋቸውን አውግዞታል።
ጽሕፈት ቤቱ "የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ ፕሬዝዳንት የመንግሥት መሪ በመሆናቸው ብቻ የያዙት እና ለማንም ይፋ ያልተደረገውን ምሥጢራዊ ሰነድ በማኅበራዊ ሚድያ እንዲበተን ማድረጋቸው ከሞራልም፣ ከሥነ ምግባርም አንጻር ሲታይ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ለሽግግር ፍትሕ እንቅፋት እንደሆነ" ገልጿል።
የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ አቶ ጌታቸው ረዳ በፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የሰጡት ቃለ መጠይቅ የትግራይ ኃይሎች አዛዦችን "ስም የማጥፋት ዘመቻ" በማለት ተቃውሞታል።
ከአንድ ወር በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን በፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ሥር በተቋቋመ ግብረ ኃይል ተጣርቶ የተገኘውን ውጤት ለማስፈጸም ቁርጠኝነት ያለው መንግሥት ባለመኖሩ ምክንያት ለሚመለከተው ሌላ አካል አሳልፈው መስጠታቸውን በራሳቸው የፌስ ቡክ ገጽ ላይ አጋርተዋል።
ቢቢሲ ትግርኛ በአቶ ጌታቸው ረዳ አንደበት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትክክለኛ መሆኑ በተረጋገጠው ሰነድ ላይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ስማቸው የተጠቀሰውን ኮሎኔል ተወልደ ገብረ ትንሳዔን ያናገረ ሲሆን "ስሜ ጠልሽቷል" ሲሉ የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ያቀረቡበቸውን ክስ በይፋ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜም "የእርሳቸው ደጋፊ በሆኑት የማኅበራዊ ሚዲያዎች ስሜን ሲያጠለሹ ቆይተዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በወቅቱ ጉዳዩን በሚመለከት ለአቶ ጌታቸው ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን የተናገሩት ኮሎኔል ተወልደ፣ ለማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎቹ "'ችግር የለውም. . . ራሴ ምላሽ እሰጣቸዋለሁ' እያለ ሲያታልለን ቆይቷል" ብለዋል።
ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ለመጨረሻ ጊዜ ከአቶ ጌታቸው ጋር የተሰበሰቡት ከሦስት ወር በፊት ነበር ያሉት ኮሎኔል ተወልደ፣ "ከሁለት ዓመት በፊት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን ሲረከብ በሚገባ ስላልተወጣው ሥልጣኔን አልተቀበሉትም ባላቸው መሪዎች ላይ የስም ማጠልሸት ዘመቻ ነው የጀመረው" ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ሦስት ከፍተኛ የትግራይ ወታደራዊ አመራሮች "በወርቅ ቁፋሮ እና ንግድ፣ የመንግሥት ገንዘብ በመዝረፍ" እንዲሁም "በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል" ሲሉ ወንጅለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በቃለ ምልልሱ ላይ በስም ጠቅሰው የወነጀሏቸው ሦስቱ አመራሮች፤ ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ ኃይለ፣ ብርጋዴር ጄነራል ኃይለሥላሴ ግርማይ እና ኮሎኔል ተወልደ ገብረተንሳዔ ናቸው።
የትግራይ ኃይሎች የመረጃ መምሪያ ኃላፊ የነበሩትን ኮሎኔል ተወልደን (ዕምበብ) በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በነበራቸው ሚና ተጠያቂ ያደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ኤርትራውያንን "እንደ ንብረት ይሸጡ" ከነበሩ ሰዎች አንዱ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
በትግራይ በኩል የነበረው ዓላማ የኤርትራን ሠራዊት ለማፍረስ "ሰዎች እንዲመጡ ማድረግ" የሚል እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ይህ ዘመቻ በስተኋላ ላይ ገንዘብ ያላቸውን ኤርትራውያንን ወደ "ማፈን. . . ማገት. . . መሸጥ" መሸጋገሩን ተናግረዋል።
ኤርትራውያን ወጣቶች ከተያዙ በኋላ በውጭ አገራት ቤተሰቦች ያሏቸውን በመለየት፤ እያንዳንዱ ሰው "በትንሹ አራት ሺህ ዶላር እንዲያስገባ ይደረግ" እንደነበር አቶ ጌታቸው በቃለ መጠይቃቸው ላይ ገልጸዋል።
ኮሎኔል ተወልደ ለቀረበባቸው ውንጀላ በሰጡት ምላሽ "እኔ በእንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ሊያሳትፍ የሚችል ሥነምግባርም ሆነ ሰብዕና የለኝም" ብለዋል።
አክለውም "እኔ ብቻ ሳልሆን እዚያ በሰነዱ ላይ ስማቸው የተጠቀሱት በስሬ የሚገኙት እኔ የምመራቸው ባልደረቦቼ እንደዚህ ዓይነት ተግባር ላይ የሚሳተፉ አይደሉም" ብለዋል።
ኮሎኔል ተወልዶ ፈጽመውታል የተባለው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር "በሕግ እና በሥርዓት ተጣርቶ እጄ በሕገወጡ ሥራ ውስጥ ከተገኘ ለመቀጣት የሚያስፈራኝ ነገር የለኝም" ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ድብቅ እስር ቤቶች እንዳሏቸው የሚያመለክት ክስ አቅርበውባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, TG
በዚያ ስብሰባ ላይ የተጠቀሱት ድብቅ እስር ቤቶች የት ነው ያሉት? እነማንስ ናቸው የታሰሩበት? የሚል ጥያቄ ቀርቦ አንደነበር ጠቅሰው "ይህንን ጉዳይ በሚዲያ ወጥቼ መናገሬ ተሳስቻለሁ ማለቱን የህወሓትም ሆነ የሠራዊቱ አዛዦች ያውቃሉ" ብለዋል።
ኮሎኔል ተወልደ ይመሩት የነበረ ክፍል ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ ትግራይ መጥተው በሕገወጥ መሳሪያ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን "ከነትጥቃቸው እና ማስረጃቸው ይዞ ለፖሊስ ያስረከብናቸው ሰዎች ነበሩ" ብለዋል።
ነገር ግን በወቅቱ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛዎች ላይ ጉዳዩ አጀንዳ በመሆኑ እና ጫና በመፈጠሩ በሕገወት መሳሪያዎች ንግድ ተያዙ ያሏቸው ግለሰቦች መለቀቃቸውን ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው ከፋና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር የተሰማሩት ሰዎች "የውጭ አካውንት ከፍተው. . . በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያገቱ" ኤርትራውያንን "የሚሸጡ" የትግራይ ሠራዊት አመራሮች እንደነበሩ ተናግረዋል።
ይህ በኤርትራውያን ላይ ሲካሄድ የቆየው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፤ በስተመጨረሻ ወደ ትግራይ ተወላጆችም መዞሩንም በቃለ ምልልሳቸው ላይ አመልክተዋል።
ኮሎኔል ተወልደ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተሰራጨው ሰነድ እና በእርሳቸው ላይ ስለ ቀረበው ውንጀላ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ነገር ግን እስካሁን ድረስ በእርሳቸውም ሆነ በስራቸው በነበሩ ሌሎች ባልደረቦቻች ላይ የቀረበ እንድም ክስ እንደሌለ ተናግረዋል።
አክለውም "በትግራይ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዳለ ታምኖ በፕሬዝዳንት ታደሰ የተቋቋመ ኮሚቴ ይህንኑ የሕገወጥ ድርጊት ለማጣራት ሥራ ላይ እንደነበረ አውቃለሁ" ብለዋል።
"በእኔ ስር የነበረች ፀረ መረጃ የምትባል ክፍል ከዚህ ጋር በተያያዘ በስህተት ታግዳ ነበር። ያ ኮሚቴ ባጣራው መሠረት ይቅርታ ተጠይቀን ሥራዋን መቀጠሏን አውቃለሁ" ብለዋል።
"በጌታቸው ረዳ የተበተነው ሰነድ ላይ የእኔ እና የባልደረቦቼ ስም አንዳለ አውቃለሁ" ያሉት ኮሎኔል ተወልደ፣ "ቢሆንም እስካሁን በራሴ እና በሌሎች በሰነዱ ላይ የተጠቀሱ ሰዎች ላይ የቀረበ ይፋዊ ክስ የለም።"
ከዚህ በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ኤርትራውያን እንዲሁም የትግራይ ተወላጆች ትግራይ ውስጥ ታግተው ገንዘብ ተጠይቀው መክፈላቸውን ተናግረዋል።
እንደ አንድ ከፍተኛ የፀጥታ ኃላፊ ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው እርሳቸውን እንደሆነ የተጠየቁት ኮሎኔል ተወልደ፣ ኤርትራውያን እና ታዳጊ የትግራይ ሴቶችን "ወደ አረብ አገር እንወስዳችኋላን በሚል የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት እንደሚፈጸም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አጥንቼ አቅርቤያለሁ" ብለዋል።
"በዚህ ጥናት መሠረት ኤርትራውያንን አግተው ገንዘብ የተቀበሉ ሰዎች እንዲያዙ አድርገናል። ይህንን ከትግራይ ክልል ፖሊስ ማረጋገጥ ይቻላል።"
ከሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ጋር በተያዘ ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተጠየቁት ኮሎኔል ተወልደ "ከቢሮ ውጪ በመሆኔ ይህንን ያህል ብሎ ቁጥሩን ለመናገር ይከብደኛል። ግን ደግሞ ከሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ እስከ አረብ አገራት ድረስ መረባቸውን የዘረጉ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋልን ግን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ" ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በቃለ ምልልሳቸው ላይ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውሩ ተጧጡፎ እንዲቀጥል የሚያደርጉ ሰዎች አሁንም መኖራቸውን ገልፀው ነበር።
አቶ ጌታቸው በትግራይ ወታደራዊ አመራሮች ተፈጽመዋል ካሏቸው ወንጀሎች ጀርባ "የፖለቲካዊ አመራሩ እጅ አለበት" ብለዋል።
የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በወንጀል ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች እርምጃ ሳይወሰድባቸው የቀረው፤ በፀጥታ አመራሮቹ እምቢተኝነት መሆኑንም በቃለ ምልልሳቸው ላይ ተናግረዋል።
ኮሎኔል ተወልደ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ስለነበራቸው የቆየ ትውውቅ አጋርተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚተዋወቁት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ባድመ ግንባር በአንድ ክፍል ውስጥ ሆነው ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ስምንት ሰዎችን የሚይዘው የዚህ ክፍል ኃላፊ እንደነበሩ ኮሎኔሉ ይናገራሉ።
በአንድ አጋጣሚም ኮሎኔሉ ከፍተኛ ድብደባ በነበረበት ወቅት ለዚያኔው ወታደር የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከፍተኛ ድብደባ ስለነበር ቶሎ በልና ምሽግህ ውስጥ ግባ" ካሏቸው በኋላ ምሽግ ውስጥ ያልነበሩት ሌሎች ሰባቱ አባላት መገደላቸውን ይናገራሉ።
በዚህም ሁኔታ የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር "ህይወታቸውን እንደታደጉት" ያወሳሉ።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ1997 በደቡብ አፍሪካ ተማሪ በነበሩበት ጊዜ ኮሎኔል ተወልደም ህክምና ለማድረግ ወደዚያው ባቀኑበት ጊዜ ዐቢይ ለአንድ ሳምንት ያህል እንዳስታመሟቸው በመግለጽ፤"የሁለቱ ወዳጅነት የጠነከረ ነበር" ይላሉ።
የትግራይ ጦርነት ተቀስቀሶ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰራዊት ሽረ እንዳስላሴን በተቆጣጠሩ ማስግስት ኮሎኔሉ በከተማው ያስገነቡት ባለ ሶስት ኮኮብ ሆቴል እንደወደመባቸው ገልጸዋል።
ሆቴሉ በማን እንደወደመ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኮሎኔል ተወልደ "ሆቴሉን ማን እንዳወደመው በግሌ ያጣራሁት ነገር የለም። ቢሆንም ሆቴሉ የወደመበት ሁኔታ ተኩስ ባልነበረበት እና ሌሊት ሰው በተኛበት አጋጣሚ መሆኑን" እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በጦርነቱ ወቅት "በኤርትራ ወታደሮች" እናታቸው ትንኮሳ እንደደረሰባቸው እና የታላቅ ወንድማቸው ልጅ ምሶሶ ላይ ታንቆ መገደሉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል ይህንን ባያጣራም የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ጦርነት በሰብዓዊነት የሚፈጸም ወንጀል፣ እና ከባድ የጦር ወንጀሎች መፈጸሙን የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ ሪፖርቶች መውጣታቸው ይታወሳል።
ኮሎኔል ተወልደ በአሁኑ ጊዜ "ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ" ከአገር ውጪ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን ሰዎች እንደማይመለሱ እና እንደሸሹ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሰራጨቱን ቢቢሲ ጠቅሶ ኮሌኔሉን ጠይቋቸዋል።
እሳቸውም "አቶ ጌታቸው ፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ስለኔ ከተናገሩ በኋላ ብዙ ሰዎች ደውለው 'ባትመለስ'፣ 'አገር ብትቀይር'፣ 'ስትገባም በሌላ መንገድ ብትመለስ' የሚሉ ምክሮችን ለግሰውኛል። እኔ ግን ከአገር የወጣሁት በህጋዊ መንገድ ሲሆን ስመለስም በዚሁ ሁኔታ ነው" ሲሉ እና ጉዳያቸውን ሲጨርሱ ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ ለቢቢሲ አስረድተዋል።












