በኢትዮጵያ የአንድ ወጣት የተቆረጠ ብልት 7 ሰዓታት በፈጀ ቀዶ ሕክምና መልሶ ተገጠመ

ቀዶ ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ የአንድ ወጣት የተቆረጠ ብልት ሰባት ሰዓታትን በፈጀ ቀዶ ሕክምና ሊቀጠል መቻሉን የአለርት ሆስፒታል ገለጸ።

ግለሰቡ በራሱ ላይ ጉዳቱን የፈፀመው ቅዳሜ ጥር 09/2018 ዓ.ም. ሌሊት ስድስት ሰዓት ላይ እንደሆነ በአለርት ሆስፒታል የቀዶ ጥገና እና ሪኮንስትራክቲቭ ክፍል ኃላፊ ዶክተር አብዱረዛቅ አሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚያው ሌሊት ወደ ጤና ተቋም እንደተወሰደ የተናገሩት ዶ/ር አብዱረዛቅ፤ ብልቱን መልሶ መግጠም ይቻል እንደሆነ ወጣቱ ካመራበት የጤና ተቋም ስልክ የተደወለላቸው እሑድ ጠዋት ላይ እንደነበር ገልጸዋል።

"ብልቱ የተቆረጠበትን ሰዓት በማስላት መጥቶ ቢገጠም ብልቱ ሊሠራ ይችላል ብለን ስላሰብን ውሳኔ አሳልፈን ወደ ቀዶ ሕክምናው ገባን" ይላሉ።

ዶ/ር አብዱረዛቅ እንዳሉት የግለሰቡ ብልት ሙሉ በሙሉ ተቆርጦ ስለነበር ሆስፒታሉ እስከሚደርስ ድረስ ለዘጠኝ ሰዓት ያህል የደም ዝውውሩ ተቋርጦ ኦክስጅን እያገኘ አልነበረም።

ነገር ግን "ብዙም መድማት አልነበረውም፤ የነበረው ሕመም መጠነኛ ነበር" ሲሉ ወደ ሆስፒታላቸው ሲገባ ጤንነቱ አስጊ ሁኔታ ላይ እንዳልነበር ተናግረዋል።

ወጣቱ ወደ ሆስፒታል ያመራው ብልቱ ከተቆረጠ ከሰዓታት በኋላ ቢሆንም 5 ሴንቲ ሜትር ሙሉ የብልቱ ክፍል ቁራጭ በበረዶ ውስጥ ሆኖ ወደ ሆስፒታሉ መወሰዱ ሕክምናውን የተሻለ እንዳደረገው ዶ/ር አብዱረዛቅ አስረድተዋል።

ዶ/ር አብዱረዛቅ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ብልትን መልሶ የመግጠም ሕክምና ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ በፊት ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ባይሆንም የተቆረጠ ብልትን ወደ ቦታው የመመለስ ሕክምና ተሞክሮ ነበር።

ነገር ግን መልሶ መግጠም የተቻለው የሽንት ቱቦውን እና ደጋፊ አካላቱን ብቻ ስለነበር ሕክምናው በአብዛኛው ውጤታማ አልነበረም ብለዋል።

በመሆኑም የብልትን ደም ሥሮች እና ነርቮችን በመገጣጠም ብልትን ወደ ነበረበት በመመለስ በወጣቱ ላይ የተደረገው ስኬታማ ቀዶ ሕክምና "የመጀመሪያው" እንደሆነ ዶ/ር አብዱረዛቅ ገልጸዋል።

"ብልት ላይ ጡንቻ ስለሌለ ከተቆረጠ በኋላ ነርቮቹ እና ደም ሥሮቹ ሳይሞቱ እስከ 16 ሰዓታት ድረስ መቆየት እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ። ጡንቻ ያለበት አካባቢ መቆየት የሚችለው ለአራት ሰዓታት ብቻ ነው" ሲሉም የተቆረጠው የወጣቱ የብልት ክፍል ለዘጠኝ ሰዓታት ከመላ አካሉ ተነጥሎ ቢቆይም መልሶ ሕይወት መዝራት መቻሉን አብራርተዋል።

ቀዶ ሕክምናው በዋነኛነት ማጽዳት፣ የተለያዩ የሽንት ቱቦ እና ደጋፊ አካላት መዋቅሮችን ማስተካከል ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከፈጀው 7 ሰዓታት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የፈጀው ነርቮችን እና የደም ሥሮችን ማገናኘት እንደነበር ዶ/ር አብዱረዛቅ ተናግረዋል።

ታካሚው በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል መጨረሻ ላይ የሚገኝ ወጣት ሲሆን፣ ይህን አደገኛ ድርጊት በራሱ ላይ ለምን እንደፈፀመ የታወቀ ነገር የለም።

ወጣቱ ከጉዳቱ እያገገመ ሲሆን በሆስፒታሉ ሕክምና እየተከታተለ እንደሚገኝም ተገልጿል።

"ለሽንቱ ቱቦ ተገጥሞለታል።ከሦስት ሳምንታት በኋላ በተፈጥሯዊ መንገድ ይሸናል ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል ዶ/ር አብዱረዛቅ።

ወሲባዊ ግንኙነት ለመፈፀም ግን ቢያንስ የሦስት ወራት ጊዜ እንደሚያስፈልግ፤ ነገር ግን ወደ ቀድሞው ሁኔታው የመመለስ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ዶክተሩ ተናግረዋል።

ዶ/ር አብዱረዛቅ እንዳሉት "ብልቱ በሚወጠር ጊዜ የተሠራውን የነርቭ ጥገና ሊያበላሸው ስለሚችል እስከ ሦስት ወር ድረስ ወሲብ መፈፀም አይፈቀድለትም።"

በመሆኑም የዚህ ሕክምና የመጨረሻው ውጤት በማገገም ሒደት ወቅት በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ላይ የሚወሰን እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙሉ በሙሉ የተቆረጡ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን መልሶ ወደ ቦታቸው በመግጠም ወደ ቀድሞ አገልግሎታቸው የመለሱ ስኬታማ ቀዶ ሕክምናዎች መደረጋቸው እየተሰማ ነው።

በቅርቡ በድንገተኛ አደጋ ሙሉ በሙሉ የተቆረጠ የአንድ የ20 ዓመት ወጣት ክንድን በቀዶ ሕክምና በተሳካ ሁኔታ መግጠም መቻሉ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ወጣቱ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ላይ ሲሠራ ባጋጠመው አደጋ እጁ እጁ ተቆርጦ ነበር አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኘው የሳማሪታን የቀዶ ሕክምና ማዕከል ያመራው።

የታካሚውን እጅ ወደ ቦታው በመመለስ ከቀሪው አካሉ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ 12 ሰዓት የፈጀ ተከታታይ ቀዶ ሕክምና እና ለሳምንታት የዘለቀ ክትትል ተደርጎለታል።

ባለሙያዎቹ እንዲህ ዓይነት የተሳካ ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያ "ለመጀመሪያ ጊዜ" የተከናወነ ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር።

ቀዶ ሕክምናው ምን ያህል ስኬታማ ሊሆን ይችላል?

አንዲህ ያለው በዓለም የመጀመሪያው የተሳካ ቀዶ ሕክምና የተደረገው ከ10 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሲሆን፣ ሕክምናውን ያገኘው ግለሰብ ጤናማ ሕይወት መምራት ችሎ ልጅ እስከ መውለድ መድረሱ ተዘግቧል።

ይህ የተቆረጠ የብልት ክፍልን መልሶ ቦታው ላይ መትከል እጅግ ውስብስብ እና ጥንቃቄን የሚፈልግ ነው። ማይክሮሰርጀሪ በሚባለው ሂደት ጥቃቅን የደም ሥሮችን እና የነርቭ መስመሮችን መልሶ ማያያዝ ያስፈልጋል።

እስካሁን በተደረጉ ተመሳሳይ ቀዶ ሕክምናዎች ታካሚዎች በአግባቡ መሽናት፣ ለወሲብ ዝግጁ መሆን፣ ወሲብ መፈጸም መቻል እና በአንድ ክስተት ደግሞ ልጅ መውለድ መቻላቸውን መስክረዋል።

የተሳካ ቀዶ ሕክምና አከናውነው ያለፉ ታካሚዎች ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ከወራት እስከ ሁለት ዓመት ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የተቆረጠውን የወንድ ብልት በቀዶ ሕክምና ወደ ተፈጥሯዊ ቦታው በተሳካ ሁኔታ መመለስ የሚቻለው አካሉ ከተቆረጠ በኋላ በፍጥነት ቀዶ ሕክምና ከተደረገ፣ የተቆረጠው የብልት አካል በቀዝቃዛ ማስቀመጫ ከ18 አስከ 24 ማቆት ከተቻለ ነው።

ነገር ግን ቀዶ ሕክምናው በተለያዩ ምከንያቶች ላይሳካ የሚችልበት ዕድልም አለው። የቆዳ ህዋሳ መሞት፣ የሽንት ቧንቧ መጥበብ እና የደም ቧንቧ መዘጋትን የመሳሰሉ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ።