በኢትዮጵያ በአደጋ ሙሉ በሙሉ የተቆረጠ ክንድ እንዴት በተሳካ ሁኔታ ተመልሶ ሊገጠም ቻለ?

በቀዶ ሕክምና ወደ ቦታው የተመለሰው የወጣቱ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Hakim

የምስሉ መግለጫ, በቀዶ ሕክምና ወደ ቦታው የተመለሰው የወጣቱ እጅ

በድንገተኛ አደጋ ሙሉ በሙሉ የተቆረጠ የአንድ ወጣት ክንድ በቀዶ ሕክምና መግጠም እንደተቻለ የሳማሪታን የቀዶ ሕክምና ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አንተነህ ካኽሉ ለቢቢሲ ገለጹ።

እንዲህ ዓይነት የተሳካ ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያ "ለመጀመሪያ ጊዜ" የተከናወነ ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የ20 ዓመት ወጣት የሆነው ታካሚው ከሦስት ሳምንት በፊት የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ላይ ሲሠራ እጁ ተቆርጦ ወደ ሆስፒታሉ መሄዱን ዶ/ር አንተነህ ገልጸዋል።

"ከክርኑ ከፍ ብሎ ነበር እጁ ተቆርጦ የመጣው። እጁ ከሰውነቱ ጋር ሙሉ በሙሉ ተለያየቶ ነበር" ብለዋል ሐኪሙ።

"ታካሚው ቀድሞ መጣ። የተቆረጠው አካል ደግሞ በበረዶ ተደርጎ ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ ተከትሎ መጣ። ቤተሰቦቹ ናቸው ይዘው የመጡት" ሲሉም ዶክተሩ ተናግረዋል።

የተቆረጠው እጅ በበረዶ ውስጥ ባይቀመጥ ኖሮ የቀዶ ሕክምናው የመሳካት ዕድል እንደሚቀንስ ዶክተሩ ገልጸዋል።

"በረዶ ውስጥ መሆኑ የተቆረጠው አካል የደም ዝውውር ስለማያገኝ እንዳይሞት በማድረግ ይጠቅማል።"

ወጣቱ ወደ ቀዶ ሕክምና ማዕከሉ ከመወሰዱ አስቀድሞ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና በተደረገለት ተቋም ውስጥ "ከፍተኛ መጠን ያለው" ደም እንደፈሰሰውም ተነግሯል።

እጁ ሙሉ ለሙሉ የመቆረጥ አደጋው የደረሰበት ወጣት ደሙ ቆሞ ከዚያም ደም ተሰጥቶች ወደ ቀዶ ሕክምና ማዕከሉ የደረሰ ሲሆን፣ ባለሙያዎችም ታካሚውን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

አሰቃቂው አደጋ ከደረሰ በኋላ ወደ ሕክምና ተቋም የተወሰደውን ወጣት እጅ መልሶ ከአካሉ ጋር የማያያዝ ነገር እጅግ ከባድ እና ውስብስብ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ራጅ

የፎቶው ባለመብት, Hakim

የምስሉ መግለጫ, የወጣቱ ክንድ ራጅ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሙሉ በሙሉ የተቆረጠ ክንድ በቀዶ ሕክምና መግጠም "መቶ ፐርሰንት እርግጠኛ ባልሆንም፣ ባለኝ መረጃ መሠረት ኢምፕላንቴሽን መሥራት ለአገራችን የመጀመሪያው ነው" ሲሉም ሜዲካል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ሐኪሙ የአንዳንድ ሰዎች ጣቶች ላይ የመቆረጥ አደጋ ሲያጋጥም 'ማይክሮ' [መለስተኛ] ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግ ገልጸው፤ "ይሄኛው ግን ዋና ክንድ ነው ተቆርጦ የመጣው። ልጁ እና አካሉ ተለያይተው ነው የደረሱት" በማለት አብራርተዋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ እጅግ ውስብስብ የሕክምና ሒደትን ስለሚጠይቅ በተለያዩ ዘርፎች ጥልቅ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ማሳተፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

"ሁሉም ባለሙያ ተሳትፏል። ልጁ ከፍተኛ ደም መፍሰስ ስለነበረው መጀመሪያ 'ስቴብላይዝ' [በመደበኛ ሁኔታ ላይ እንዲሆን] ተደርጓል። ከዚያም የአጥንት ስፔሻሊስት፣ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የደም ሥር ስፔሻሊስት እንዲሁም የማደንዘዣ ባለሙያ በጋራ የቀዶ ሕክምና ዕቅድ አውጥተዋል።"

ይህ ውስብስብ ቀዶ ሕክምና በተለያዩ የሕክምና የሙያ ዘርፎች ላይ በተሰማሩ አራት ሰብ-ስፔሻሊስት ሐኪሞች መከናወኑን ዶ/ር አንተነህ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቀው ይህ ቀዶ ሕክምናው በሁለት ዙሮች የተከናወነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ስድስት ሰዓታት የወሰደ ነው።

ሁለተኛው ቀዶ ሕክምና ከመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ከሁለት ሳምንት በኋላ የተካሄደ ሲሆን፤ ስድስት ሰዓት ገደማ ወስዷል።

ስለዚህም ባለሙያዎቹ በየመስኮቻቸው የታካሚውን እጅ ወደ ቦታው በመመለስ ከቀሪው አካሉ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የ12 ሰዓት ቀዶ ሕክምና እና ለሳምንታት የዘለቀ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በቀዶ ሕክምናው ሂደት "ቅድሚያ የተሰጠው ለአጥንት እና ደም ሥር ሲሆን፣ የደም ሥር ሲቀጠል የተቆረጠው አካል እንዳይሞት ለማድረግ ይቻላል። የደም ሥሩ እና አጥንቱ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ ለነርቭ ጅማቶቹ ጊዜ ሰጥተን በደረጃ መሠራት አለበት ብለው ባለሙያዎች ወሰኑ።"

ቀዶ ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተቆረጠ አጥንት ከተቀጠለ በኋላ እንደሚድን የሚናገሩት ዶ/ር አንተነህ፤ የተቆረጠው አካል ምግብ እንዲያገኝ የደም ሥሮቹ እንደሚቀጠሉም አስረድተዋል።

የ20 ዓመቱ ወጣት ነርቩ እና ጡንቻዎቹ ከተቀጠሉለት በኋላ እጁ መደበኛውን ተግባሩን እንዲያከናውን ተከታታይ ፊዚዮቴራፒ (የማገገሚያ ሕክምና) እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

በሁለት ዙር ከተደረገው ቀዶ ሕክምና በኋላ ወደ ቦታው የተመለሰው የወጣቱ "እጅ በሙሉ ጤንነት ላይ" እንደሚገኝ አክለዋል።

በሰውነታችን ውስጥ ትልልቅ ጡንቻዎቻችንን በመጠቀም እንደ መራመድ እና መሮጥ ያለ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን (gross motor skills) ይባላል።

ትንንሽ ጡንቻዎችን በመጠቀም እንደ መጻፍ ያለ ክንውንን ለመፈጸም የሚያስችለው ክህሎት ደግሞ (fine motor skills) የሚባል ሲሆን፤ "ገና ቀዶ ሕክምናው ከተሠራ ሁለት ሳምንት ስለሆነ ፋይን ሞተሮቹ ፊዚዮቴራፒ እና የክትትል ሕክምና ያስፈልገዋል" ብለዋል።

እንደ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለ ፊዚዮቴራፒ (የማገገሚያ ሕክምና) ካደረገ በኋላ የወጣቱ እጅ እንደቀደመው እንደሚሆን ዶ/ር አንተነህ ተናግረዋል።

ከሰው አካል ላይ የተለየን የሰውነት ክፍልን ወደ መልሶ መትከል እና ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተከናወነ ተመሳሳይ ሕክምና ስለመኖሩ መረጃ ማግኘት አልተቻለም።

ይህ አሁን የተደረገው ሙሉ በሙሉ ከሰውነት ተቆርጦ የተለየ እጅን በቀዶ ሕክምና መልሶ መግጠም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከተከናወኑ ታላቅ የሕክምና ተግባራት መካከል አንዱ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ተግዳሮቶች ባሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለውን ውስብስብ ቀዶ ሕክምና ማድረግ እና ለስኬት ማብቃት ፈታኝ ነው።

ዶክተር አንተነህም እንዲህ ያለው ቀዶ ሕክምና በኢትዮጵያ እንዳይከናወን ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር መሰናክል እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሕክምና መሠረተ ልማት ዝርጋታ ውስንነትም ሌላው ፈተና መሆኑን አመለክተዋል።