ለኩላሊት ህመምተኛው የተሳካ የአሳማ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደረገላቸው

ሐኪሞች በቀዶ ህክምና ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኩላሊታቸው ሥራ በማቆሙ የአሳማ ኩላሊት የተተከለላቸው የ62 ዓመቱ አሜሪካዊ ‘በጥሩ ሁኔታ እያገገሙ’ መሆናቸውን እና በቅርቡም ከሆስፒታል እንደሚወጡ ተዘገበ።

ግለሰቡ አዲስ የተተከለላቸው ኩላሊት ከአጠቃላይ የሰውነታቸው ሥርዓት ጋር እንዲጣጣም በሚል በዘረ መል ማሻሻያ ከተራባ አሳማ የተወሰደ ነው።

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና ያደረጉት አሜሪካውያን ሐኪሞች የአሳማ ኩላሊት የተተከለላቸው ታማሚ ሪክ ስሌይማንን ይህንን ፈር ቀዳጅ ኦፕሬሽን ለመሞከር ፈቃደኛ በመሆናቸው “እውነተኛ ጀግና” ተብለዋቸዋል።

የተለያዩ የውስጥ አካላት ችግር ላለባቸው ሰዎች የመጨረሻው ተስፋ ከእንስሳት የሚገኙ ክፍሎችን በንቅለ ተከላ ማሸጋገር መሆኑ ይነገራል።

የአሳማ ኩላሊት ከዚህ ቀደም አንጎላቸው ሥራ ላቆመ ሰዎች በመስጠት ሙከራ ተደርጎበታል።

ከቀናት በፊት ለአራት ሰዓታት የተካሄደው ቀዶ ህክምና “ለህሙማን ሊሰጥ የሚችል ዝግጁ የሆነ የውስጥ አካል መኖሩን ያመለከተ ወሳኝ ምዕራፍ ነው” ሲል ህክምናው የተካሄደበት የማሳቹሴትስ አጠቃላይ ሆስፒታል ገልጿል።

የቀዶ ህክምናው የተደረገላቸው ግለሰብ ሪክ ስሌይማን ኩላሊታቸው በአግባቡ ሥራውን ባለማከናወኑ ለሰባት ዓመታት የኩላሊት እጥበት (ዳያሊሲስ) ሲያደርጉ ቆይተው፣ በአውሮፓውያኑ 2018 በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ ከሌላ ሰው የተወሰደ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው ነበር።

ነገር ግን ከአምስት ዓመታት በኋላ የተሰጣቸው ኩላሊት ሥራ በማቆሙ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ የኩላሊት እጥበት ማድረግ መልሰው ጀምረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም ምክንያት ውስበስብ የጤና እክል አጋጥሟቸው በየሁለት ሳምንቱ ወደ ሆስፒታል በመሄድ የደም ሥሮቻቸው ላይ ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተዋል።

ግለሰቡ የአሳማ ኩላሊት እንዲተከልላቸው ከመወሰናቸው በፊት ጥቅሙን እና ጉዳቱን በመመዘን ንቅለ ተከላው እንዲካሄድ መፈቀዳቸውን ተናግረዋል።

“ለእኔ በሚደረገው በዚህ ቀዶ ህክምና ለእኔ የሚሆን ውጤትን ብቻ ሳይሆን፣ ውሳኔዬ በሕይወት ለመቆየት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለሚያስፈልጋቸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋን መፈንጠቅ ነው።”

ለንቅለ ተከላ የሚውሉ የሰው ልጅ የውስጥ ክፍሎችን የሚለግሱ ሰዎችን ማግጀት እጅግ አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ስለዚህም እንዲህ ዓይነት ከእንስሳት የሚገኝ የውስጥ አካል ክፍል ችግሩን ይቀርፋሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

አሁን ከተደረገው የአሳማ ኩላሊትን በንቅለ ተከላ ለሰው ከመስጠት በተጨማሪ በቅርቡ የአሳማ ልብ ወደ ሰው የማዘዋወር ሙከራ መደረጉ ይታወሳል።

አሁን ለንቅለ ተከላ የዋለው ለየት ያለው የአሳማ ኩላሊት ኬምብሪጅ ማሳቹሴትስ ውስጥ በሚገኝ ማዕከል ውስጥ የዘረ መል መሻሻያ ከተደረገበት አሳማ የተገኘ ነው።

በዚህ ሂደትም ከአሳማው ዘረመል ላይ ለኩላሊቱ ተቀባይ ግለሰብ ጎጂ የሆኑት እንዲወገዱ የተደረጉ ሲሆን፣ የአሳማው ኩላሊት ከተቀባዩ ሰው ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ደግሞ ለአሳማው የሰው ዘረ መል እንዲሰጠው ተደርጓል።

የአሳማው ኩላሊት በንቅለ ተከላ የተሰጣቸው አዛውንት ኩላሊቱ ከአጠቃላይ የሰውነት ሥርዓታቸው ጋር እንዳይቃረን የሚያደርግ መድኃኒት በአሁኑ ወቅት እየተሰጣቸው ነው።

ይህ የመጀመሪያ የሆነው የአሳማ ኩላሊትን በንቅለ ተከላ ወደ ሰው የማሸጋጋሩ ህክምና ውጤቱ ገና በዝርዝር ያልታወቀ በመሆኑ ኩላሊቱ ለግለሰቡ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያገለግል የታወቀ ነገር የለም።

የኩላሊቱን ንቅለ ተከላ ካካሄዱት ሐኪሞች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ታሱኦ ካዋይ ይህ ቀዶ ህክምና “በዓለም ዙሪያ በኩላሊት ችግር እየተሰቃዩ ላሉ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ህሙማን የሕይወት ተስፋን የሚሰጥ ነው” ብለዋል።