የወንድ ዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ልገሳ በኢትዮጵያ: ለመካንነት አዲስ መፍትሔ?

የወንድ ዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ልገሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአርባዎቹ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ሔለን ተስፋይ (ስሟ የተቀየረ) ትዳር ከመሠረተች ሁለት ዓመት ገደማ ሆኗታል። ነገር ግን እሷ እና ባለቤቷ ልጅ የመውለድ ፍላጎት ቢኖራቸውም ሳይሳካላቸው ቆይቷል።

“ቤተሰብ ጋር ስንሄድ ‘ለምንድነው የማትወልጂው?’ ይላሉ። ይህ ደግሞ ያስጨንቃል፣ ያሳስባል። ልጅ ስለሌለኝ አሁን ላይ በጣም ይሰማኛል። እህቶቼ በሙሉ ወልደዋል። ባለመውለዴ በጣም ነው የሚሰማኝ” ስትል ትዳር ከመሠረተች በኋላ ልጅ አለመውለዷ የፈጠረባትን ተጽዕኖ የመቀለዋ ነዋሪ ትናገራለች።

“ልጅ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ቤት ብሠራም፣ ምን ብል ብቻዬን ከሆንኩ ምን ያደርግልኛል?” ስትል ትጠይቃለች።

ሔለን የወር አበባ ማየት ብታቆምም ልጅ ለማግኘት የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎችን መጎብኘቷን ለቢቢሲ ተናግራለች። ለዚሁ ተብሎ የተሰጣትን መድኃኒት ብትወስድም ለውጥ አላመጣም።

አሁን ግን ተስፋ ሊሰጥ የሚችል መፍትሔ እንዳገኘች ትናገራለች።

ሔለን፤ ምንም እንኳ የወር አበባ ማየት ብታቆምም፤ እንቁላል የሚለግሳት ሰው ካገኘች ማርገዝ እንደምትችል ተነግሯታል።

ይህን ዓይነቱን ህክምና የሚሰጠው ደግሞ በትግራይ መቀለ ከተማ የሚገኘው አዶ የእናቶች እና የህጻናት እንዲሁም የመካንነት ህክምና ማዕከል ነው።

ስለ አዲሱ ልጅ መታቀፊያ መንገድ ከማዕከሉ የህክምና ባለሙያዎች የሰማችው ሔለን፤ ባለፉት ሳምንታት የምታውቃቸውን የቅርብ ሴቶች እንቁላል እንዲሰጧት ስትጠይቅ መቆየቷን ታስረዳለች።

ጥያቄውን ካቀረበችላቸው አብዛኞቹ ሰዎች የሚያስደስት ምላሽ ባታገኝም፤ የወንድሟ ባለቤት እንቁላል ልትሰጣት ፈቃደኛ መሆኗን እንደገለጸችላት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ይህንን ዓይነቱን የመካንነት ህክምና የሚሰጠው አዶ፤ ከለጋሾች በሚገኝ የወንድ የዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ለመሰብሰብ የሚያስችል ፈቃድ ከትግራይ ክልል የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና ቁጥጥር ባለሥልጣን ያገኘው ከሦስት ወራት ገደማ በፊት ታኅሣሥ 24/2016 ዓ.ም. ነው።

ማዕከሉ፤ ይህንን ፈቃድ ካገኘ በኋላ በልገሳ የተገኘን የወንድ የዘር ፍሬ እና የሚስትን እንቁላል በማገናኘት የመጀመሪያውን ጽንስ በተሳካ ሁኔታ ማስገኘቱን የአዶ ባለቤት ዶ/ር ሳምሶን ሙሉጌታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ነፍሰ ጡር የሆነችው ሚስት እና ባለቤቷ የልጁን መወለድ እየተጠባበቁ መሆኑን የክልሉ የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ የሱፍ ኢብራሂምም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሌሎች የማዕከሉ ታካሚዎችም በልገሳ ከሚገኝ የወንድ የዘር ፍሬ ወይም የሴት እንቁላል ልጅ ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆኑን የአዶ ባለቤት ዶ/ር ሳምሶን ይናገራሉ። ለዚህም ሲባል ማዕከሉ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የወንድ የዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል እንዲለግሱ ጥሪ እያደረገ ነው።

የህክምና ማዕከሉ ባለቤት ዶ/ር ሳምሶን ሙሉጌታ

የፎቶው ባለመብት, ado

የምስሉ መግለጫ, የህክምና ማዕከሉ ባለቤት ዶ/ር ሳምሶን ሙሉጌታ

በተለገሰ እንቁላል እና የዘር ፍሬ ልጅ የሚያስታቅፈው ህክምና

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ሳምሶን እንደሚገልጹት፤ በልገሳ በሚገኝ እንቁላል ልጅ እንዲወልዱ የሚደረጉት ሴቶች “ጽንስ የሚሸከም ማህጸን እያላቸው፤ እንቁላል የሌላቸው” እንደሆኑ ይናገራሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የሚለገሳቸው እንቁላል እና የባለቤታቸው የዘር ፍሬ እንዲገናኝ ተደርጎ ጽንስ እንደሚፈጠር አስረድተዋል።

በወንድ የዘር ፍሬ ልገሳ የሚወልዱት ደግሞ፤ ባል “የዘር ፈሳሽ ቢኖረውም የዘር ፍሬ ህዋስ የሌለው” ከሆነ መሆኑን የሚናገሩት ስፔሻሊስቱ፤ በልገሳ የተገኘው የዘር ፍሬ እና የሚስት እንቁላል ተገናኝቶ ጽንስ እንደሚፈጠር አብራርተዋል።

በሰው ሠራሽ መንገድ ኢንቪትሮ ፈርቲላይዜሽን (Invitro fertilization-IVF) በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ የሴት እንቁላል እና የወንድ ዘር ፍሬ እንዲገናኙ በማድረግ ጽንስ የመፍጠር ሂደት ነው። ይህ የሰው ሰራሽ የተዋልዶ ህክምና ሲከናወን እንቁላል እና የዘር ፍሬ እንዲገናኙ የሚደረገው ከማህጸን ውጪ ላብራቶሪ ውስጥ ነው።

ላብራቶሪ ውስጥ የተፈጠረው ጽንስ ተመልሶ ወደ ማህጸን እንዲገባ ተደርጎ የተለመደው ተፈጥሯዊ የእርግዝና እና ልጅ የመውለድ ሂደት ይቀጥላል።

ይህ የህክምና ዘዴ ሲከወን ባል ወይም ሚስት የመውለድ ችግር ካለባቸው በልገሳ የሚገኝ እንቁላል ወይም የዘር ፍሬ ጥቅም ላይ ይውላል። በዚህ የህክምና ዘዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጅ የተወለደው በአውሮፓውያኑ በ1978 ሲሆን፣ ካለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ወዲህ የህክምና ዘዴው በተለያየ መንገድ እያደገ ሄዶ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ሆኗል።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ጽንስ የመፍጠር ዘዴ ጥቅም ላይ መዋል ከመጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካለፈው ዓመት ድረስ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህጻናት በዚህ ሂደት ተወልደዋል።

የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ሳምሶን፤ ልጅ ለመውለድ የተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ይህንን ህክምና ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ወደ ሕንድ እንደሚጓዙ ይናገራሉ። ከ15 እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚጠይቀው የሕንድ ህክምና፤ “ብዙ ድካም” እንዳለውም ያክላሉ።

ዶ/ር ሳምሶን እንደሚያስረዱት ከወጪው ከፍተኛ መሆን ባሻገር በሕንድ አገር ከሌላ ሰው በሚለገስ እንቁላል ወይም የዘር ፍሬ ጸንሰው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ሌላ ችግር ያጋጥማቸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ “ውጭ አገር ሲሄዱ ይዘውት የሚመጡት እርግዝና የሕንድ ነው የሚሆነው። [የህጻናቱ] ጸጉር የተቀየረ ነው፣ መልካቸው ለውጥ ይኖረዋል። ከማኅበረሰቡ ትንሽ ጫና ይኖረዋል። በመውለዳቸው ደስ ቢላቸውም የሚሰጣቸው የዘር ፍሬ እና እንቁላል የሕንድ ስለሚሆን የራሱ ጫና ይኖረዋል” በማለት ያስተዋሉትን ችግር ያስረዳሉ።

“ወደዚህ ሥራ እንድንገባ የገፋፋንም የማኅበረሰቡ ችግር ነው” የሚሉት ዶ/ር ሳምሶን፤ “የእነዚህን ሰዎች ችግር የሚረዳው ልጅ የሌለው ሰው ነው” ባይ ናቸው። ለሌላው ደግሞ “[መደበኛውን ህክምና] ስንሠራ ‘ከፍሬህ ስፐርም አላገኘንም’ ስንላቸው ቀጥታ ወደ ፍቺ የመሄድ፣ አስር ዓመት የነበራቸው ፍቅር በአንዴ የመፍረስ” ሁኔታን በማየታቸው ነው።

የላብራቶሪ ምስል

የፎቶው ባለመብት, ado

የምስሉ መግለጫ, በህክምና ማዕከሉ የሴት እንቁላል እና የወንድ የዘር ፍሬን ማገናኘት የሚከናወንው በላብራቶሪ ውስጥ ነው

የወንድ የዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ልገሳ ጥሪ

አዶ የእናቶች እና ህጻናት እንዲሁም የመካንነት ህክምና ማዕከል፤ ይህንን ህክምና ለመስጠት ዝግጅት የጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ እንደነበር ዶ/ር ሳምሶን ይናገራሉ። በጦርነቱ ምክንያት ህክምናውን ለማስጀመር የተደረገው ጥረት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፣ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ሂደቱ እንደገና ቀጥሎ ህክምና መስጠት ላይ ተደርሷል።

ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት እየተጠባበቀ ያለው የወንድ ዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ነው።

እንደ ዶ/ር ሳምሶን ገለጻ፤ ሁሉም ሰው የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል መለገስ አይችልም። በሁለቱም ፆታዎች ያሉ ለጋሾች ከፈቃደኝነት ባሻገር ብቁ የሚያደርጋቸው መስፈርት አለ።

ወንድ የዘር ፍሬ ለጋሾች የሚሰጡት የዘር ፈሳሽ ከ1.5 ሚሊ ሊትር በላይ መሆን አለበት። በአንድ ሚሊ ሊትር የዘር ፈሳሽ ውስጥም ከ15 ሚሊዮን በላይ የዘር ፍሬ ህዋሶች ሊኖሩ ይገባል። በተጨማሪም ለጋሾቹ በሚደረግላቸው ምርመራ ከኤችአይቪ፣ ከጉበት ቫይረስ እና ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ነጻ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት።

እንቁላል የሚለግሱ ሴቶች ላይ ደግሞ የዕድሜ ገደብም እንዳለ ዶ/ር ሳምሶን ያስረዳሉ። ለእንቁላል ልገሳ ብቁ የሚሆኑት ሴቶች ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 30 ባለው ውስጥ የሚገኙት ናቸው። ከዚህም ባሻገር ሴት ለጋሾች ከዚህ ቀደም የወለዱ መሆን አለባቸው።

ዶ/ር ሳምሶን ይህ መስፈርት የተቀመጠበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “[የወለዱ ሴቶች] እንቁላላቸው የተፈተነ ነው። ምክንያቱም ወልደዋል፤ እንቁላላቸው ኖርማል እንደሆነ ማረጋገጫ አለ። ዕድሜያቸው አነስ ሲል ደግሞ እንቁላሉ ጥራት ይኖረዋል። ጥራት ያለው እንቁላል ሲሆን ጽንስ የመፈጠር ዕድሉ ሰፊ ነው፤ ወደ 80፣ 85 በመቶ ይደርሳል። ይህም በዓለም ላይ የሚሠራበት ልምድ ነው” ይላሉ።

እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ለጋሾች ከተቋሙ ጋር የሚገቡት ስምምነትም እንዳለ የማዕከሉ ባለቤት ገልጸዋል። የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስቱ እንደሚያስረዱት፤ በስምምነቱ ላይ ከተቀመጡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የተለገሰው የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል ለማን እንደሚሰጥ የማይገለጽ መሆኑ ነው።

“ደም ሲለገስ ለማን እንደሚሰጥ አይታወቅም። የሰው ሕይወትን ማዳን ነው የሚታሰበው። እዚህም ላይ ሰውን መርዳት ነው የሚታሰበው” ሲሉ አካሄዱ ከደም መለገስ ጋር ተመሳሳይ መርኅን እንደሚከተል ይጠቅሳሉ።

ይሁንና የተለገሰው የዘር ፍሬ ለማን እንደተሰጠ ሊታወቅ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ተቀባዮች ልገሳ የሚያደርጉላቸውን ሰዎች ራሳቸው ይዘው ሲመጡ ነው።

በልገሳ ወቅት የሚፈረመው ስምምነት ለዚህም መፍትሔ ማስቀመጡን ዶ/ር ሳምሶን ጠቅሰዋል። ለጋሾች በሚሰጡት እንቁላል ወይም የዘር ፍሬ አማካኝነት ጽንስ ከተፈጠረ በኋላ የሚወለደው ልጅ ላይ የወላጅነት ጥያቄ ማንሳት እንደማይችሉ የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ይገልጻሉ።

“ውሉ ላይ የሚፈረመው ‘እኔ በፍቃደኝነት እየለገስኩ ነው። የሚፈጠረው ጽንስ፣ ልጅ ባለቤትነቱ የተቀባዮቹ ነው’ ተብሎ ነው። ስለዚህ ብዙ ጭቅጭቅ ውስጥ የሚያስገባ ነገር አይደለም” ሲሉ ከስምምነቱ ዋነኛ ጉዳዮች ውስጥ አንዱን አንስተዋል።

መቀለ የሚገኘው ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, ado

በዚህ ውል ተስማምተው የሚፈርሙ ወንድ እና ሴት ለጋሾች በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ ያልፋሉ። ወንድ ለጋሾች በምርመራ ነጻ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ የዘር ፍሬ እስከሚሰጡበት ቀን ድረስ ከማንኛውም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነት ተቆጥበው መቆየት እንዳለባቸው ዶ/ር ሳምሶን ይናገራሉ።

የዘር ፍሬው በሚወሰድበት ዕለትም “በማስተርቤሽን መንገድ የዘር ፈሳሽ ይሰጣሉ” ሲሉ ሂደቱን ያስረዳሉ። ዘር ፍሬ የሚለግሱ ወንዶች አስር ሺህ ብር “የማበረታቻ ገንዘብ” እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

እንቁላል የሚለግሱ ሴቶች የሚከተሉት ሂደት በአንጻሩ ወንድ ለጋሾች ከሚያልፉበት የበለጠ ቀናትን ይወስዳል። በዚህ ሂደት የሚያልፉ ሴቶች ከመለገሳቸው በፊት “እንቁላል እንዲያድግ የሚያደርግ መርፌ” እንደሚወስዱ ዶ/ር ሳምሶን ይገልጻሉ።

“[ለጋሽ ሴቶች] ወደ 10 ቀን አካባቢ መርፌ ይወስዳሉ። እንቁላሉ አድጓል ብለን ስናስብ [እንቁላል] የምንሰበስበው በማህጸን የሚገባ አልትራሳውንድ አለ በዚያ አማካይነት ነው” ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል።

ሴት ለጋሾች እንቁላል ለመስጠት የሚያልፉበት ሂደት እንደ ወንዶች “ቀላል” ባለመሆኑ እና ለቀናት ወደ ማዕከሉ ስለሚመላለሱ የሚያገኙት የ“ማበረታቻ ገንዘብ” ከወንድ ለጋሾች ይበልጣል። ማዕከሉ ለለጋሽ ሴቶች የሚሰጠው ገንዘብም 30 ሺህ እንደሆነ ዶ/ር ሳምሶን ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ ግን እንቁላልም ይሁን የዘር ፍሬ የሚለግሱ ፈቃደኞችን ማግኘት አለመቻሉን የማዕከሉ ባለቤት ተናግረዋል። ለዚህም የግንዛቤ እጥረት መሆኑን በመጥቀስ “…በሌላ ዓለም እንደሚሠራ፣ ለተቸገረ ሰው መርዳት እንደሆነ ለማስረዳት ጥረት ላይ ነን። ትንሽ ጊዜ የሚፈጅ ይመስለኛል” ብለዋል።

በልገሳ በተገኘ የዘር ፍሬ እና እንቁላል ጽንስ የመፍጠር ሂደት

ዶ/ር ሳምሶን እንደሚያስረዱት ታካሚዎች በልገሳ በሚገኝ እንቁላል እና የዘር ፍሬ ልጅ እንዲያገኙ ወደሚያስችላቸው ህክምና ከመግባታቸው በፊት በሌላ አማራጭ ልጅ መውለድ የማይችሉ መሆኑ መረጋገጥ አለበት። ይህ ማረጋገጫ ሲገኝ ጉዳዩ ወደ ማዕከሉ ቦርድ ቀርቦ ሂደቱ ይገመገማል።

የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስቱ፤ “[የቦርዱ አባላት] ሂደቱን ያዩታል። ታካሚዎቹ የተመረመሩት ምንድነው? ምን አማራጭ አላቸው? [የሚለውን መርምረው] ‘ያለው አማራጭ መለገስ ብቻ ነው’ የሚለውን በፊርማቸው ያረጋግጣሉ” ሲሉ ታካሚዎች እንዲዘጋጁ የሚነገራቸው ከዚህ በኋላ መሆኑን ይገልጻሉ።

እንቁላል የሚለገሳቸው ሴቶች ማህጸን ግድግዳ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ለ10 ቀናት መድኃኒት እንደሚወስዱ ዶ/ር ሳምሶን ያስረዳሉ። ለእነዚህ ሴቶች ጥቅም ላይ የሚውለው የወንድ የዘር ፍሬ የሚገኘው ከባለቤታቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ባል ላይ በተከሰተ ችግር ምክንያት ከሌላ ወንድ የዘር ፍሬ የሚወሰድ ከሆነ ደግሞ የሚስት እንቁላል እንዲሰበሰብ ይደረጋል። “ባለቤቱ እንቁላል እያመረተች ትቆያለች። [የሚስትን] እንቁላል የሰበሰብን ቀን የተለገሰው የዘር ፍሬ ጽንስ እንዲሆን ከእንቁላሉ ጋር ይገናኛል ማለት ነው” ልዩነቱን አስረድተዋል።

የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስቱ፤ በሁለቱም መንገዶች እንቁላል እና የዘር ፍሬ እንዲገናኝ የሚደረገው በላብራቶሪ ውስጥ መሆኑን ይገልጻሉ።

“እንቁላሉ እና ዘር ፍሬው ተገናኝተው ላብራቶሪ ውስጥ ጽንስ ይፈጠራል። ጽንሱ ለሦስት ቀናት ኢንኩቤተር ውስጥ ይቆያል። የጽንሱን ደረጃ፣ ማደጉን አይተን ኖርማል መሆኑን አረጋግጠን፤ ጽንሱን ወደ ተቀባይዋ ሴት የማህጸን ግድግዳ እናስገባዋለን” ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል።

እንደ ዶ/ር ሳምሶን ገለጻ በዚህ ሂደት ከ350 እስከ 500 ሺህ ብር ሊፈጅ ይችላል። ወጪው አስፈላጊውን ሂደት ለማከናወን የሚለው እንደሆነ እና ይህ ገንዘብ በሌሎች አገራት ከሚከፈለው በብዙ እጥፍ ያነሰ ነው።

የህክምና ማዕከሉ ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, ado

ስለሰው ሰራሽ የተዋልዶ ሂደት ሕጉ ምን ይላል?

የትግራይ ክልል የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ለቢቢሲ እንደተናገሩት መሥሪያ ቤታቸው የወንድ የዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ልገሳን ለመቀበል የሚያስችለውን ፈቃድ ለአዶ የሰጠው ማዕከሉ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኅዳር 2016 ዓ.ም. በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ፈቃዱን ከመስጠቱ በፊት ማዕከሉ የጠየቀውን አገልግሎት ለማቅረብ የሚችል መሆኑን ለማረጋጋገጥ የተለያዩ ምዘናዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ህክምናውን የሚሰጡ ባለሙያዎች የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ እንዲሁም ጥቅም ላይ የሚውለው የቴክኖሎጂ መሳሪያ በባለሙያዎች ተመዝነው መስፈርቱ መሟላቱን አቶ የሱፍ ጠቅሰዋል።

“[በተጨማሪም] የፌደራልን ሕግ ይቃወማል አይቃወምም የሚለውን ነገር በአዋጃችን እናየዋለን። በዚህ አዋጅ መሠረት የሚቃወም ነገር ስላጣን [ፈቃድ ተሰጥቷል]” ሲሉ የአገሪቱ የሕግ ጉዳይም ምዘና ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ፤ “ትግራይ ውስጥ [ውጭ ሀገር በተለገሰ ዘር] የተወለዱ አራት፣ አምስት ልጆች አሉ። የውጭ ዜጋ ነው የሚመስሉት። የሚወለደው ልጅ ከእኛ ቆዳ ጋርም አይሄድም። [በዚህ ምክንያት] በእናቶች ጋር የሚፈጠረውን የሥነ ልቦና ጫና ለመቀነስ በእኛው የዘር ፍሬ፣ በእኛው እንቁላል፣ እዚሁ ህክምናውን ብንሰጥ ይሻላል ብለን ፈቅደናል” ሲሉ ማዕከሉ ፈቃዱን እንዲያገኝ ምክንያት የሆነውን ሌላ ጉዳይ አንስተዋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለአዶ ፈቃድ መሰጠቱን በገለጸበት ደብዳቤ ላይ፤ ጦርነቱ በክልሉ ነዋሪዎች የተዋልዶ ጤና ላይ ተጽእኖ ማስከተሉ እንዲሁም በውጭ አገር ይህንን ህክምና ለማግኘት ያለው ኢኮኖሚያ ጫናም በምክንያትነት ተጠቅሷል።

ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ደብዳቤ ለማዕከሉ ፈቃድ ለመስጠት የሚጠቅሰው ሕግ በ2006 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀውን “የምግብ፣ መድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር” ደንብ ነው። በአቶ ኢብራሂም የተጻፈው ይህ ደብዳቤ በደንቡ አንቀጽ 57 ላይ “የወንድ እና የሴት ዘር ፍሬ ልገሳን በተመለከተ ክልከላ አለመቀመጡን” ይጠቅሳል።

በደብዳቤው ላይ የተጠቀሰው አንቀጽ “ስለሰው ሰራሽ ተዋልዶ ህክምና” የተደነገገበት የደንቡ ክፍል ነው። ይህ አንቀጽ ፈቃድ ያገኙ ተቋማት ይህንን ህክምና መስጠት እንደሚችሉ ደንግጓል።

ደንቡ፤ “አግባብ ያለው አካል ፈቃድ በሚሰጠው የጤና ተቋም እና የጤና ባለሙያ ሰው ሰራሽ የተዋልዶ ህክምና መስጠት ይቻላል” ይላል። የማህጸን ኪራይ እና “ሰውን በክሎኒንግ ቴክኖሎጂ መፍጠር” ግን የተከለከሉ ተግባራት እንደሆኑ በዚሁ አንቀጽ ላይ ሰፍሯል።

ይሁንና በደንቡ ላይ ፈቃድ እንደሚሰጥበት የተጠቀሰው ሰው ሰራሽ ተዋልዶ ከሌላ ሰው በልገሳ የሚገኝን የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል እንደማያካትት በጤና ሚኒስቴር የጤና፣ የጤና ተቋማት እና የባለሙያዎች ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ፀዳል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በ2006 ዓ.ም. የወጣው ደንብ “ሰው ሰራሽ የተዋልዶ ህክምና” የሰጠው ትርጓሜ ህክምናው የሚሰጥበትን ሁለት ዓይነት መንገዶችን ያካትታል። የመጀመሪያው፤ “የወንድን የዘር ፍሬ በተፈጥሮ ከሚታወቀው ዘዴ በተለየ መልኩ ወደ ሴቷ ውስጣዊ የመራቢያ አካላት ለወሊድ ዓላማ ማስተላለፍ” የሚል ነው።

ለ“ሰው ሰራሽ የተዋልዶ ህክምና” የተሰጠው ሌላኛው ትርጉም፤ “የወንድ እና የሴት ዘር ጥምረት ውጤትን፤ ዘሯ ከተወሰደው ሴት ማህጸን ውስጥ ለማስተላለፍ ከሰውነት አካል ውጪ የወንድ እና የሴት ዘርን ማቀላቀል” ይላል።

አቶ እንዳልካቸው እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ ውስጥ “አይቪኤፍ” የተሰኘውን ይህንን ህክምና የሚያከናውኑ የጤና ተቋማት ፈቃድ የሚያገኙበት ስታንዳርድ ቢኖርም ፈቃዱ ከሌላ ሰው በልገሳ ከሚገኝ የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል ጽንስ መፍጠርን አያካትትም።

“እንደ አገር ይሄንን ነገር መሥራት የሚቻለው በባል እና በሚስት መካከል ነው። ከዚህ ውጪ የሆነ ልገሳ የሚባል ነገር በእኛ በኩል እውቅና መስጠት አንችልም” ሲሉ ሚኒስቴሩ የሚከተለውን አሰራር አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት በልገሳ በተገኘ ዘር ስለሚፈጠር ጽንስ “አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ” የጠቀሱት አቶ እንዳልካቸው፤ በትግራይ ክልል ስለተሰጠው ፈቃድ እንደማያውቁም አክለዋል።

ይሁንና ክልሎች የጤና ጉዳይን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የራሳቸውን መንገድ መበየን እንደሚችሉ ጠቁመዋል። መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ “[የጤናን ጉዳይ በተመለከተ] ክልሎች እንደ ክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ የማስተካከል፣ የማሻሻል ወይም የማጣጣም (customize) የማድረግ ነገር አላቸው። አንዳንድ ነገሮችን መቀየር ግን አይችሉም። በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተሰጠ የፌደራል እና የክልሎች ሥልጣን አለ። ስለዚህ ጤና በክልልም በፌደራልም ቢኖርም ክልሎች ከእራሳቸው ጋር ማጣጣም እንዲችኩ ዕድሉ አላቸው” ብለዋል።

የወንድ ዘር ፍሬ እና የሴት እንቁላል ልገሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images