በወንዶች ላይ መሃንነትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች እና መፍትሄዎቻቸው

ስፐርም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሁኑ ወቅት ዓለማችን ላይ የወንዶች መሃንነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የወንዶች የዘር ፍሬ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀነሱ እንደሆነ አጥኚዎች ይናገራሉ።

ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ወንዶች በወሲብ ወቅት የሚለቁት የወንድ የዘር ፍሬ መጠን (ስፐርም ካውንት) 51 በመቶ መቀነስ አሳይቷል።

ይህ መረጃ በእስራኤል የሚገኘው የሂብሩ ዩኒቨርስቲ እና በአሜሪካ የሚገኘው የሲና ማውንቴን የህክምና ዩኒቨርሰቲ በቅርቡ በጋራ ካሳተሙት የምርምር ውጤት የተገኘ ነው።

ተመራማሪዎቹ ከሃምሳ ዓመት በፊት የነበሩ ወንዶች በአማካይ በአንድ ሚሊሊትር የወንድ ዘር ፈሳሽ ውስጥ ቢያንስ 101 ሚሊዮን ለመራቢያ የሚሆኑ የወንድ ዘር ፍሬ ፈሳሽ ነበራቸው። በአሁኑ ወቅት ይህ አሃዝ ወደ 49 ሚሊዮን ወርዷል።

ከብዛት በተጨማሪ ወደ ሴት እንቁላል መግባት የሚችሉ የወንድ የዘር ፍሬ ህዋሶችም በጥራት ደረጃ ማሽቆልቆላቸውን ከቅርብ አስርት ዓመታት ወዲህ የታዩ መረጃዎች ያመላክታሉ።

“በጣም የሚያስደንቀው ነገር የወንድ የዘር ፍሬ እንቅስቃሴ መገደብ ነው። እንቅስቃሴው ቆመ ማለት የመራባት አቅሙም ይቀንሳል” ሲሉ በብራዚል ሥነ-ተዋልዶን በሳይንስ እየደገፈ ያለው ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ራፋኤል ራዳኤሊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የወንድ የዘር ፍሬ ቁጥር ማሽቆልቆል፣ የጥራት መውረድ እና እንቅስቃሴ መገደብ በጤና ባለሙያዎች መካከል ድንጋጤን ፈጥሯል።

“የወንድ የዘር ፍሬ ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው፤ ይህም ወደየት ሊደርስ እንደሚችል አለማወቃችን አሳሳቢ ነው” ሲሉ የወንድን ሥነ ተዋልዶ የሚያጠናው የብራዚል የዩሮሎጂ ማኅበር አስተባባሪ ኤድዋርዶ ሚራንዳ ተናግረዋል።

የወንድ የዘር ፍሬ ፈሳሽ ህዋስ መቀነስ በሁሉም አህጉሮች ቢታይም በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ አሜሪካ የበለጠ ከፍ ብሎ ታይቷል።

ለወንድ የዘር ፍሬ መቀነስ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ባለሙያዎቸች ቢያንስ አምስት ምክንያቶችን ይጠቁማሉ። ሆኖም ሳይንቲስቶች አትደናገጡ ይላሉ። ጥሩነቱ ይህንን ለመቀልበስም ወይም ለመቀነስ መንገዶች አሉ።

በ50 ዓመታት ውስጥ የወንዶች የዘር ፍሬ መጠን ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱን ጥናት አመልክቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ50 ዓመታት ውስጥ የወንዶች የዘር ህዋሰት መጠን ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱን ጥናት አመልክቷል

1. ከመጠን ያለፈ ውፍረት

ወንዶች ከመጠን በላይ ሲወፍሩ በወንድ የዘር ፍሬ ህዋሶች ላይ ጎጂ ሁኔታዎችን ያስከትላል።

በመላው ሰውነታችን ስብን የሚያከማቸው አዲዮፖዝ ህዋስን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ያደርገዋል። ይህም በወንድ የዘር ፍሬ ህዋስ ውስጥ መሠረታዊ ከሆኑት ሆርሞኖች አንዱ የሆነውን ቴስቴስትሮንን በቀጥታ የሚነኩ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ማመንጨት ይጀምራል።

ሚራንዳ እንደሚሉት ከመጠን በላይ መወፈር በሰውነት ውስጥ ያሉ የተለያዩ ህዋሶች የሚጎዱበት ‘ኦክሲዲቲቭ ስትረስ’ የሚባለውን ሂደት ይፈጥራል።

“በተጨማሪም ከመጠን በላይ የወፈሩ ወንዶች በብልቶቻቸው ላይ የበለጠ የስብ ክምችት አላቸው፤ ይህም ለወንድ የዘር ህዋስ (spermatozoa) በከፍተኛ ሁኔታ አስጊ ነው” ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።

የመራቢያ ህዋሶች በሰውነት ውስጥ ተመርተው የሚከማቹበት የዘር ፍሬ ማከማቻ በደንብ እንዲሰራ ከሰውነት ሙቀት ከ1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እስከ 2 ዲግሪ በታች መሆን አለበት። ለዚያም ነው የሰው ልጅ የዘር ፍሬ ማከማቻዎች ለብቻቸው ተንጠልጥለው የተፈጠሩት።

በሰውነት የስብ መጠን መጨመር የመራቢያ አካላትን ያሞቃል ይህም ሁኔታ በአግባቡ መስራት እንዲያቆሙ ያደርጋቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለማችን ዙሪያ 39 በመቶ ወንዶች ወፍራም የሚባሉ ሲሆኑ፣ 11 በመቶው ደግሞ ከመጠን ያለፈ ውፍረት አላቸው። ይህም አሃዝ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ውስጥ የወንድ የዘር ህዋስ (spermatozoa) መጠን መቀነስን ለማብራራት ጥሩ ማሳያ ነው።

ወፍራም ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

2. በሱስ መጠመድ

አልኮል፣ ሲጋራ፣ ቬፒንግ፣ ማሪዋና፣ ኮኬይን፣ አናቦሊክ፣ ስቴሮይድ… እነዚህ ሁሉ አደንዛዥ፣ አነቃቂ ዕጾች እና መድኃኒቶች የዓለማችን ሰዎች የሚያዘወትሯቸው ሲሆኑ አንድ የሚያመሳስላቸውም ባህርይ አለ።

ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሁሉም የወንድ የዘር ፍሬ ህዋስ ጤናን ይጎዳሉ። 

“ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የወንድ የዘር ፍሬ የሚያመነጩትን ህዋሳት በቀጥታ ይጎዳሉ” ሲሉ ሚሪንዳ ይናገራሉ። 

ሌሎቹ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽእኗቸውን ያሳርፋሉ። የወንድ የዘር ፍሬ ለማመንጨት የሚያነቃቁ ሆርሞኖችን ያኮሰምናሉ።

በተለይም ደግሞ በባለሙያዎች ዘንድ የተጠቀሰው ወንዶች ጡንቻቸውን ለማፈርጠም ሲሉ ቴስትሮንን በመርፌ፣ በጄል እና በእንክብል የመውሰዳቸው ጉዳይ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአስደንጋጭ እና በሚያስፈራ መልኩ ጡንቻቸውን ለማፈርጠም ሆርሞን የመጠቀሙ ጉዳይ ዓለማችንን እያጥለቀለቃት ይገኛል።

ቴስቴስትሮንን ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በሰው ሰራሽ መልኩ በሚተካበት ጊዜ ሰውነት በተፈጥሮው ለማምረት አስፈላጊ እንዳልሆነ ያስባል።

በዚህም ምክንያት በወንድ ፈሳሽ ውስጥ ያለው የዘር ፍሬ ቁጥር ዜሮ ላይ ይደርሳል። ይህም አዞአስፔርሚያ ተብሎ የሚታወቀው በሽታ ነው።

3. በወሲብ አማካኝነት የሚተላለፉ ህመሞች

በባክቴሪያ የሚተላለፉ እንደ ቂጥኝ እና ጨብጥ ያሉ ህመሞች የወንዶችን ዘርን የሚያስተላልፉ ቱቦዎች ላይ እብጠት ሊያስከትል ይችላል።

ይህም የወንዶች የዘር ፍሬ ህዋስ ላይ አደጋ ይጋርጣል።

የዓለም ጤና ድርጅት በ2020 ብቻ 129 ሚሊዮን ሰዎች በቂጥኝ እንደተያዙና እና 82 ሚሊዮን ደግሞ በጨብጥ መጠቃታቸውን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። ይህም አሃዝ መቀነስ አላሳየም፤ ወይም በቅርብ አስርት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ጭማሪ አሳይቷል።

ሌላኛው ተመራማሪዎች የሚጠቁሙት ደግሞ ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ወይም በምህጻረ ቃል ኤችፒቪ ተብሎ የሚታወቀው በወሲብ አማካኝነት የሚተላለፈው በሽታ ነው።

ይህ በሽታ የወንድ የዘር ፍሬ መመረት ላይ ብቻ ሳይሆን ስር በሰደደ መልኩ በስፐርም ዘረ መል ላይም ተፅእኖ ያሳድራል ተብሏል።

ኮምፒውተሩን ጭኑ ላይ አድርጎ እየሰራ ያለ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

4. ኮምፒውተርን በጭን ላይ ማስቀመጥ

የሰው ልጅ የዘር ፍሬ ከሰውነት ሙቀት በታች በሆነ ከ1 እስከ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች መቆየት አለበት። ሆኖም ባለፉት አስርት ዓመታት ኮምፒውተርን ጭን ላይ አድርጎ መስራት የወንድ ልጅ የዘር ፍሬን ለተጨማሪ አደጋ አጋልጦታል።

ኮምፒውተሮች በሚሞቁበት ወቅት ወደ ሰውነት በመተላላፍ የወንድ የዘር ፍሬን “መብሰል” በሚችልበት ደረጃ ያደርሱታል።

ሚራንዳ እንደሚሉት ሌሎች ከከፍተኛ ሙቀት ጋር የተያያዙ ሌሎች ልማዶችም በመራባት ላይ አደጋን ጋርጠዋል።

በባለሙያው ከተጠቀሱትም መከካል ረዘም ያለ ሙቅ ሻወር መውሰድ፣ ሙቅ መታጠቢያ ገንዳዎች ላይ መዘፍዘፍና ሳውና ይገኙበታል።

በተጨማሪም እንደ ዋይፋይ እና ኤሌክሮኒክ ሞገዶችም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በወንድ የዘር ህዋስ ላይ ተጽእኖም እንደሚያሳድሩም ተገልጿል።

5. የኢንዶክሪን መጨናነቅ

በሰውነታችን ውስጥ ኢንዶክሪን የተሰኘው ሥርዓት የእጢዎችና የአካል ክፍሎች ውስብስብ ኔትወርክ (መረብን) የያዘ ነው።

የኢንዶክሪንን ሥርዓት የሚረብሹ መርዛማ ውህዶች እንዲሁም በወንድ ልጅ የዘር ፍሬ ላይ የራሳቸውን ተፅእኖ አላቸው።

ከእነዚህም ውስጥ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙ ቆሻሻዎች፣ ፕላስቲኮች እና ፀረ-ተባዮችን ያጠቃልላል።

እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ ካሉት ሆርሞኖች ጋር ተመሳሳይነት ያለው መዋቅር ስላላቸው ወደ ህዋስ ተቀባይ አካላት ውስጥ በመግባት ያልተፈለጉ ነገሮችን ማነሳሳት ይችላሉ።

በቅርብ ጊዜ በተደረጉ ጥናቶች እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን ውስጥ የሚያካሂዷቸው ለውጦች የወንድ የመራቢያ ሁኔታ ላይ ተፅእኖ ማሳደራቸውን ማየት ተችሏል።

ሆኖም የዚህን ችግር በእርግጠኝነት ለማወቅት ብዙ ጥናቶች እየተደረጉም እንደሆነ ተመላክቷል።

በወንድ የዘር ህዋሳት የተደረገው ጥናት ብቁ ያልሆኑትን ለይቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በወንድ የዘር ህዋሳት የተደረገው ጥናት ብቁ ያልሆኑትን ለይቷል

የወንድ የዘር ፍሬ ለመቀነሱ ከሚነሱ አካባቢ እና ባህርያዊ ምክንያቶች በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ጉዳዮችም ተጠቃሾች ናቸው።

የመጀመሪያው የጄኔቲክስ ሁኔታ ነው።

ልጅ ለመውለድ ከሚቸገሩ መካከል ከ10 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት በወንዱ ዲኤንኤ (ዘረ መል) ካለ ችግር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገመታል።

ሁለተኛው ደግሞ ከዕድሜ ጋር የተያያዘ ነው። ወንዶች እድሜያቸው ከጨመረ በኋላ አባት የመሆን ፍላጎታቸው ጋር የተያያዘ ነው።

“ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የመራባት አቅም እንደሚቀንስ እናውቃለን። ምንም እንኳን የወንዶች የመውለድ አቅም መቀነስ እንደ ሴቶች ባይገለጽም ለወንድ ዘር ፍሬ ህዋስ መመረት ጠቃሚ የሆኑት ሆርሞኖች ግን እየቀነሱ ነው” ሲሉ ያስረዳል።

በአጠቃላይ የወንዶች የዘር ፍሬ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የመሃንነት ሁኔታ እየከፋ ይሄዳል ቢባልም የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምጣት ችግሮችን ሊቀርፍ እንደሚችልም ተስፋ ተጥሎበታል።

መፍትሄዎቹ ምን ይሆኑ?

ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ወንዶች በወንድ የዘር ፍሬ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጉዳት ለመቀልበስ የአኗኗር ዘዬ ለውጦችን ሊያደርጉ ይገባል።

ባለሙያዎቹ ከሚጠቅሷቸው መካከለል ተመጣጣኝ ምግብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ክብደታቸውን መቀነስ፣ የአልኮል መጠጦችን ማቆም ወይም መቀነስ እንዲሁም ሲጋራዎችን እና ሌሎች አደንዛዥ እፆችን መጠቀምን ማቆም ይመክራሉ።

ወሲብ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የሚፈፅሙ ከሆነ እንደ ቂጥኝ እና ጨብጥ ካሉ ተላላፊ በሽታዎች ላለመያዝ ሁልጊዜም ኮንዶም ተጠቀሙ ይላሉ።

በጉርምስና መጀመሪያ ላይ የኤችፒቪ ክትባት የሚወስዱ ግለሰቦችም ቫይረሱ በዲኤንኤ ላይ ከሚያስከትለው አደጋም ራሳቸውን ይጠብቃሉ።

ተጨማሪ ቫይታሚኖችን በመውሰድ እንዲሁም ሆርሞኖችን በመቆጣጠር ሁኔታዎችን ሊመረምሩ ይገባል።

እነዚህን ሁሉ የአኗኗር ዘዬዎችን ቀይረው ልጅ ለመውለድ ከተቸገሩ የጤና ባለሙያ ማየት ተገቢ እንደሆነ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

የበሽታዎች ችግር ከሆነ በመድኃኒት ወይም በቀዶ ጥገና ህክምና መስተካከል እንደሚችልም ይጠቁማሉ።