ተመራማሪዎች በተሳካ ሁኔታ የኤችአይቪ ቫይረስን ከተበከለ ህዋስ ቆርጠን ማስወገድ ችለናል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኔዘርላንድስ ተመራማሪዎች በኤችአይቪ ከተበከለ ህዋስ ቫይረሱን ነጥለው ማስወገድ መቻላቸውን አስታወቁ።
ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት ቫይረሱን ቆርጠው ማውጣት የቻሉት የኖቤል ሽልማት ያገኘው ክሪስፕር የተሰኘውን ‘ጂን-ኤዲቲንግ’ መንገድ በመጠቀም ነው።
ልክ እንደ መቀስ ከዘረ-መል ላይ “የማይፈለገውን” በመቁረጥ ማስገድ ወይም ‘ንቁ’ እንዳይሆን ማድረግ መቻላቸውን ተመራማሪዎች ገልጠዋል።
ቀጣዩ እርምጃ ቫይረሱን ከሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ቢሆንም ይህንን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ሳይንቲስቶቹ ይናገራሉ።
አሁን ገበያ ላይ ያሉ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች የቫይረሱ መስፋፋት መግታት እንጂ ቫይረሱን ከሰውነት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የማጥፋት አቅም የላቸውም።
በመጀመሪያ ዙር ሙከራው ይህን ስኬት ማምጣት የቻለው በኔዘርላንድስ የሚገኘው የአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ቡድን ነው።
ቡድኑ በአንድ የህክምና ጉባኤ ላይ የደረሰበትን ስኬት ይፋ ባደረገ ጊዜ ሂደቱ ገና ብዙ እንደሚቀረው እና ለኤችአይቪ ፈውስ የሚሆን መድኃኒት ሆኖ ለመቅረብ የሚያስፈልጉ ሂደቶች መኖራቸውን አጽንኦት ሰጥቷል።
የኖቲንግሀም ዩኒቨርሲቲ የስቴም ሴል እና ዘረ-መል ቴራፒ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጄምስ ዲክሰን እንደሚሉት አዲሱ ግኝት በደንብ መመርመር አለበት።
“ኤችይቪ ባለባቸው ሰዎች ላይ ይህን ሥራ መሥራት ከመጀመራችን በፊት ብዙ ሂደት ማለፍ ያስፈልገዋል” ይላሉ።
ሌሎች ሳይንቲስቶችም የኖቤል ሽልማት ያገኘውን መንገድ በመጠቀም ለኤችአይቪ ፍቱን መድኃኒት ለማግኘት እየሠሩ ነው።
ኤክሲሽን የተሰኘ አንድ የሕክምና ተቋም ይህን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሦስት ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች ላይ ለ48 ሳምንታት ሙከራ ካደረገ በኋላ ሰዎቹ ጉልህ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳልታየባቸው አስታውቋል።
ለንደን የሚገኘው የፍራንሲስ ክሪክ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጆናታን ስቶይ፣ ከተበከለ ህዋስ አይችአይቪን ቆርጦ ማውጣት “ሲበዛ ከባድ” ሥራ ነው።
“አሁንም አስጊ የሚሆነው ነገር የጎንዮሽ ጉዳቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው” ይላሉ ዶክተሩ።
“ስለዚህ አዲሱን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ኤችአይቪን ከሰውነት ማስወገድ ገና ብዙ ዓመታት የሚቀረው ሥራ ሊሆን ይችላል። ደግሞ ይሄን ለማድረግ ቴክኖሎጂው ውጤታማ መሆኑን መጀመሪያ ማወቅ አለብን።”
ኤችአይቪ ራሱን በራሱ እያባዛ ሰውነት ውስጥ በመስፋፋት የሰውን በሽታን የመከላከል አቅም የሚያዳብሩ ህዋሳትን ያጠቃል።
ኤችአይቪ ያለባቸው አብዛኞቹ ሰዎች ሕይወታቸውን በሙሉ ፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒት መውሰድ ይኖርባቸዋል።
መድኃኒት መውሰድ ካቆሙ መሰፋፋት አቁሞ የነበረው ቫይረስ ተነቃቅቶ ችግር ሊያመጣባቸው ይችላል።
በጣም ጥቂት ሰዎች ከኤችአይቪ “ሙሉ በሙሉ መዳን” ችለዋል። ይህ የሆነው በጣም አደገኛ የሆነውን የካንሰር ህክምና አድርገው ቫይረሱ መጥፋት በመቻሉ ነው።
ነገር ግን ይህ መንገድ ኤችአይቪን ለማጥፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ባለሙያዎች አይመክሩም።












