ቭላድሚር ፑቲን፡ ከኬጂቢ ሰላይነት እስከ ረጅም የፕሬዝዳንትነት ዘመን

የፎቶው ባለመብት, GAVRIIL GRIGOROV/POOL/AFP
ቭላድሚር ፑቲን ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ሩሲያ እየመሩ ነው።
በዚህም ከቀድሞዋ ሶቭየት አምባገነን መሪ ከጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል ለረጅም ዓመታት አገራቸውን ያስተዳደሩ መሪ ሆነዋል።
የ71 ዓመቱ ፑቲን ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን በፕሬዝዳንትነት ለመመረጥ ሲዘጋጁ ጠንካራ ተፎካካሪዎች በዙሪያቸው አልነበሩም። በመሆኑም ከድል የገታቸው ምንም ነገር አልነበረም።
እርሳቸው ከሻቱም እስከ አውሮፓውያኑ 2036 ድረስ በመንበራቸው ላይ ለመቆየት የሚያግዳቸው እዚህ ግባ የሚባል ምክንያት የሚኖር አይመስልም።
ፑቲን ክሬሚሊንን ለመምራት ወደ ፕሬዝደንትነት የመጡት በአጋጣሚ ነበር።
ብዙም እውቅና ያልነበራቸው የቀድሞው የኬጂቢ ሰላይ በቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ውስጣዊ ቡድን ውስጥ በትክክለኛው ቦታ እና ሰዓት መገኘታቸው ነበር የሥልጣን ማማውን ያቆናጠጣቸው።
ፑቲን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከሰባት ዓመታት በኋላ ነው የተወለዱት። በጦርነቱ ታላቅ ወንድማቸውን አጥተዋል። ወላጆቻቸውም ከመከራ ማጥ ውስጥ ነው የወጡት።
በሰሜን ምዕራብ ሩሲያ በምትገኘው ሌኒንጋርድ [በአሁኗ ሴንት ፒተርስበርግ] በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት ያደጉት ፑቲን፣ በልጅነታቸው በተደባዳቢነታቸው ነበር የሚታወቁት። ከሚበልጧቸው እና ጠንካራ ከሆኑ የሰፈር ወጣቶች ጋር ይጣሉ ነበር።
ከባድ የልጅነት ጊዜም ነበራቸው።
ይህም እስካሁን ድረስ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ይነገራል።
ለመሆኑ ፑቲን ማን ናቸው? ከየት ተነስተውስ እዚህ ደረሱ? እንዴትስ ይታወሳሉ?
የተዛባ የታሪክ አተያይ
ፑቲን ብዙውን ጊዜ ለሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት የሚሰጡት በተዛባ የታሪክ አረዳድ እና በኔቶ ላይ ከያዙት ቂም በመነሳት ነው።
ለዚህም እንደ አንድ ምሳሌ የሚመዘዘው ከዩክሬን ወረራ በፊት እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዩክሬን ናዚዎች የተሞላች የውሸት አገር ናት ሲሉ በሐሰት መክሰሳቸው ነው። በዚህም ምክንያት ዩክሬን ከኔቶ ጋር ያላትን ቀረቤታ ለማስቆም ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል።
ከምዕራባውያን መሪዎች መካከል የተሻለ ያውቋቸዋል የሚባሉት የቀድሞዋ የጀርመን መራሔተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም በአንድ ወቅት ፑቲንን “ከእውነታ የራቁ እና በሌላ ዓለም ያሉ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
በተደጋጋሚ ከፑቲን ጋር ለመደራደር ጥረት ያደረጉት ሜርክል፣ ፑቲን ወደ ኪዬቭ ወታደሮቻቸውን ከላኩ በኋላ “አውሮፓን ማውደም ይፈልጋሉ” ሲሉ ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር።
“. . . የመጀመሪያውን ቡጢ መሰንዘር”
ፑቲን በ2000 በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በልጅነታቸው ካሳለፉት አንድ አጋጣሚ ትልቅ ትምህርት መውሰዳቸውን ተናግረው ነበር። ይህ ቃል መፈናፈኛ ማሳጣት የሚል ነው።
ልጅ እያሉ በአሁኗ ሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤታቸው ደረጃ ላይ አንድን ትልቅ አይጥ ሲያባርሩ እንደቆዩ እና በኋላ ላይ ደረጃው ላይ እንዴት ማምለጫ እንዳሳጡት በቃለ ምልልሳቸው አስታውሰዋል።
ከዚያም አይጡ ወዴትም መሄድ እንዳልቻለ እና አይጡን ደብድበው እንደወረወሩት ገልጸዋል።
“ከዚህም 'መፈናፈኛ ማሳጠት' የሚለውን የመጨረሻ ትምህርት ወሰድኩ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ወጣቱ ፑቲን በሰፈራቸው ካሉ ትላልቅ እና ጠንካራ ወጣት ወንዶችም ጋር ይደባደቡ ነበር።
በኋላ ላይ ያንን ጊዜ በማስታወስ ራሳቸውን ሆሊጋን [ችግር ፈጣሪ] ሲሉ ገልጸውታል።
ይህንን ተከትሎ ነው እራሳቸውን ለመከላከል በሚል የጁዶ ስፖርትን በልጅነታቸው መማር የጀመሩት።
ፕሬዝዳንት በሆኑበት ጊዜም ሥልጠናውን ቀጥለው ጥቁር ቀበቶ ማግኘት ችለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ሴንት ፒተርስበርግ ጎዳና ላይ የቆየ ልምዳቸውን ሲያካፍሉም “ከ15 ዓመት በፊት የሌኒንግራንድ ጎዳና አዲስ ሕግ አስተማረኝ። ይህም ፍልሚያው የማይቀር ከሆነ የመጀመሪያውን ቡጢ መሰንዘር አለብህ የሚል” ብለዋል።
ፑቲን በሌኒንግራድ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ በ1975 ወደ ሶቪየት የስለላ ተቋም (ኬጂቢ) ነበር ያመሩት። ይህም የሕግ ምሩቅ ለነበሩት ፑቲን የሚጠበቅ እና ሥራውም ለእርሳቸው ተስማሚ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Other
‘ዘ ስዎርድ' እና 'ዘ ሽልድ’ የተባሉ እና በናዚ ጀርመን የተሰሩ ግፎችን የሚያጋልጡ በሩሲያ የድብቅ ሰላዮች የተቀረጹ የሶቭየት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እያዩ ላደጉት ለያኔው ፑቲን የኬጂቢ ሥራ ህልማቸው ነበር።
በወቅቱ ጥሩ ጀርመንኛ መናገር የሚችሉት ፑቲን፣ በምሥራቅ ጀርመን ከተማ ድሬዝድን የኬጂቢ ቢሮ ተመደቡ።
በ1989 (እአአ) ኮሚዩኒስቷ ሶቭየት ስትፈራርስ ያዩትም እዚያ ሳሉ ነበር።
ከኬጂቢ ቢሮ ካለው መንገድ በአሻጋሪ የሚገኘውን የምሥራቅ ጀርመን የምሥጢር ፖሊስ ጽህፈት ቤትን በቁጣ የተሰባሰቡ ሰዎች ሲወሩት ተመለከቱ። የተወሰኑ ቡድኖች ደግሞ ወደ እርሳቸው ሕንጻ እየቀረቡ ሲመጡ ገለል እንዲሉ አስጠነቀቋቸው።
ይህ አልሆን ሲል የሶቪየት ቀዩ ጦር ታንከኛ ክፍልን ለጥበቃ ሲጠሩ ሩሲያ እርዳታ ማድረግ እንደማትችል ተረዱ። “ያለ ሞስኮ ትዕዛዝ ምንም ማድረግ አንችልም” ተባሉ። ሞስኮም ዝም አለች።ያኔ ሶቭየት መፈራረሷን አመኑ።
በሚቀጥለው ዓመት ወደ ፖለቲካው ሥርዓት በፍጥነት ተመለሱ። ሌተናነት ኮሎኔል የሚል ማዕረግም ተሰጣቸው።
ይህንን ሹመት ኬጂቢ ውስጥ ሲሠሩ አላገኙትም ነበር። ከአዛዦቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት ኒኮላይ ሌኖቭ፣ ፑቲንን እንደ መካከለኛ የስለላ ወኪል ነበር የሚመለከቷቸው።
ከወዳጆቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት
ፑቲን በጣም ቅርብ ከሚሏቸው ወዳጆቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ጠበቅ ያለ ወዳጅነት አላቸው።
እስካሁን ድረስ በጣም ትንንሽ በሆኑ የኬጂቢ የባልደረባ ቡድኖች ጋር ምሥጢረኛ ናቸው። እንደ የሩሲያ የፀጥታው ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ኒኮላይ ፓትሩሼቭ ያሉ አጋሮቻቸውንም የረዥም ጊዜ አጋር አድርገው መያዝን ያውቁበታል።
ታዲያ ወዳጆቻቸውን ሲመርጡ ዝም ብለው የዐይናቸው ቀለም ስለማራቸው ብቻ አይደለም። የሚሆናቸውን ያውቃሉ።
የቀድሞው የጁዶ አሠልጣኝ አናቶሊይ ራክህሊን በአንድ ወቅት “ፑቲን ራሳቸውን በተግባር የሚገልጡለትን ሰዎች ያምናል” ብለው ነበር።
ለሚያምኗቸው ሰዎች ደግሞ የሚበለጽጉበትን መንገድ ይከፍታሉ። የልጅነት ጓደኛቸውን አርካዲይ ሮተንበርግ ሩሲያን ከክሬሚያ የሚያገኛን ድልድይ ለመገንባት የ3.5 ቢሊዮን ዶላር ውል ሰጥተውታል።
ስለ ግላዊ ሕይወታቸውም ቢሆን በጣም ድብቅ ናቸው።
ፑቲን በርካታ ሚሊየኖችን የሚያንቀሳቅሱ ወዳጆች አሏቸው። እራሳቸውም ቢሆኑ ቀላል የማይባል ሃብት እንዳላቸው ይነገራል፤ ነገር ግን የቤተሰባቸውን እና የራሳቸውን ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች በብርቱ ምሥጢርነት ነው የሚይዙት።

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ከባለቤታቸው ሉድሜላ ጋር ከ30 ዓመታት ትዳር በኋላ በ2013 (እአአ) ተፋተዋል።
ሉድሜላ በአንድ ወቅት “በሥራ ፍቅር የሰከረ ሰው” ስትል ፑቲንን ገልጻቸው ነበር።
ከባለቤታቸው ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። አንደኛዋ ማሪያ ቮሮንተሶቫ ስትሆን የትምህርት እና የንግድ ሰው ናት። ሁለተኛዋ ካተሪና ቲክሆኖቫ ደግሞ የምርምር ፋውንዴሽን ኃላፊ ናት።
ከ1991 ጀምሮ ፑቲን የሌኒንግራድ አዲሱ ከንቲባ አናቶሊይ ሶብቻክ ምክትል እና አማካሪ ሆነው ነበር። ከዚያም ሶብቻክ ሳይመረጡ ሲቀሩ ምክትላቸው የነበሩት ፑቲን በሞስኮ የፕሬዝዳንት አስተዳደር ውስጥ እንዲሰሩ ተደረገ።
በዚህ ጊዜ የቦሪስ የልሲን አስተዳደር እያከተመ የፑቲን ደግሞ እየጎመራ ነበር።
ከዚያም የፌደራል የፀጥታ አገልግሎት ኃላፊ ሆነው ለአጭር ጊዜ ከሰሩ በኋላ የፀጥታው ምክር ቤት ፀሐፊ ሆነው ለፕሬዝዳንቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠየቁ።
ለፕሬዝዳንትንት ዕጩ መሆን
እንደ አውሮፓውያኑ ነሐሴ 9/1999 የልሲን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አባረው በቀጣይ ዓመት ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት እምብዛም የማይታወቀውን የ46 ዓመቱ ጎልማሳ ተኩ።
የልሲን በወቅቱ ተተኪ ይፈልጉ ነበር።
ፑቲን ዕጩ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለየልሲን የጠቆሟቸው ቫለንቲን ዮማሽቭ፣ ፑቲን ሊበራል እና ዲሞክራት እንደሆኑ ነው ራሳቸውን የሚገልጹት ይላሉ።
የየልሲን የፕሬዝዳንትነት ጀምበር ስታዘቀዝቅ ሞስኮ የበርካቶችን ሕይወት በቀጠፈና ምክንያቱ ባልታወቀ የቦምብ ጥቃት ተመታች። ከዚያም ቭላድሚር ፑቲን መጠነ ሰፊ የምድር ጥቃት በመክፈት ሙስሊም ሩሲያውያን የሚኖሩበትን ቼቺኒያን ከተገንጣይ አማጺያን እጅ ነጠቁ።
በዚህም ዝናቸው እየጨመረ መጣ። እንደ አውሮፓውያኑ ታኅሳስ 31/1999 ፕሬዝዳንቱን ተክተው እንዲሠሩ ተሾሙ። ከሦስት ወራት በኋላ የመጀመሪያውን የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸውን አሸነፉ።
በቼቺኒያ ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።
ዋና ከተማዋም የወደመች ቢሆንም የሩሲያ መሪ ግን ድልን ተቀዳጁ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከዚያም የመጀመሪያውን የአገር ውስጥ ፈተናን በአውሮፓውያኑ 2000 ተጋፈጡ። የኑክሌር ሰርጓጅ መርከብ ኩርስክ በባሬንትስ ባሕር በደረሰባት አደጋ ሰመጠች። 118 ሠራተኞችም ሞቱ ። ፕሬዝዳንት ፑቲን ዓለም አቀፍ እርዳታን አልቀበልም አሉ።
በዚህም ምክንያት በርካቶቹ ሠራተኞች ነፍሳቸውን የሚታደግላቸው እየተጠባበቁ ነበር የሞቱት። በወቅቱ በሐዘን የተጎዱ ሴቶች ፕሬዝዳንታቸው ላይ ሲጮሁ በቴሌቪዥን ታይተዋል።
ከአራት ዓመታት በኋላ የቼቺንያ አማጺያን 1 ሺህ ሰዎችን አግተው ወሰዱ። አብዛኞቹ ታጋቾች በሰሜን ኦሴቲያ በሚገኘው ቤስላን የነበሩ ሕጻናት ነበሩ። የሩሲያ ልዩ ኃይሎች ህንጻውን ሲወሩ 330 ሰዎች ሞቱ ። በኋላ ላይ ሩሲያ የታቀደው ጥቃት መረጃ እንደነበራት፤ ነገር ግን እርምጃ ለመውሰድ አለመቻሏ ይፋ ወጣ።
በእነዚህ ምክንያቶች የመጀመሪያው የፑቲን ፕሬዝዳንታዊ ዓመት በደም የተሞላ እና ፈታኝ ቢሆንም የሩሲያ ኢኮኖሚ ግን እየተመነደገ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ውስጥ በሩሲያ ውስጥ የተንሰራፉ በመንግሥት ሃብት የበለጸጉ ቢሊየነሮች ላይ እርምጃ በመውሰዳቸው የሕዝብ ድጋፍን ማግኘት ችለዋል። ቱጃሮቹን ወደ ክሬሚሊን በመጥራት ከፖለቲካ ጋር እስካልተነካኩ እና እርሳቸውን እስከደገፉ ድረስ ገንዘባቸውን እንደማይወርሱባቸው ቃል ገቡላቸው።
በዚህ ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይም በአፋጣኝ ነበር እርምጃ የወሰዱት። ከእነዚህ መካከል አፈሙዝ ተደግኖባቸው ተይዘው በሳይቤሪያ የታሰሩት የሩሲያ ቱጃር ሚካሄል ኮዶርኮቭስኪይ አንዱ ናቸው።
ከምዕራባውያን ጋር ያላቸው ግንኙነት
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ከምዕራባውያን ጋር ብዙም ወደፊት ያልተራመደ ግንኙነት ነበራቸው።
አልቃይዳ የመስከረም 11ዱን ጥቃት ሲፈፅም ለፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ቀድመው ስልክ ከመቱ የውጭ አገር መሪዎች አንዱ ነበሩ።
“ሰውዬውን ዐይኑን ተመለከትኩት ። በጣም ቀጥተኛ እና ታማኝ እንደሆነ አገኘሁት” ብለው ነበር ፕሬዝዳንት ቡሽ።
ብዙም ሳይቆይ ቭላድሚር ፑቲን ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ጋር በጎሪጥ መተያየት ጀመሩ።
የቀድሞው የኬጂቢ ሰላይ እና የክሬሚሊን ተቺ አሌክሳንደር ሊትቪኔንኮ በለንደን በአደገኛ ኬሚካል ሲገደሉም ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጋር ያላቸው ግንኙነት ሻከረ።
በኋላ ላይም የዩኬ ምርመራ ኬጂቢ የፈፀመውን ጥቃት የሩሲያው መሪ ሳይፈቅዱ እንዳልቀረ አመልክቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 በሙኒክ የፀጥታ ስብሰባ ላይ ፑቲን ለአሜሪካ ያላቸውን ስሜት በይፋ አስረድተዋል።
“አንድ አገር [አሜሪካ] በሁሉም መንገድ ብሔራዊ ድንበሯን አልፋለች” ሲሉ ነበር ፑቲን ቅሬታቸውን የገለጹት።
ይህ ንግግራቸው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካ እና በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት መካከል የነበረውን 'ቀዝቃዛውን ጦርነት' ያስታወሰ ሲሆን፣ አሜሪካ በማዕከላዊ አውሮፓ የሚሳኤል መከላከያ ሥርዓት ለመገንባት ያላትን ዕቅድ በተመለከተም የሩሲያን ቁጣ የገለጹበት ነበር።
“በበርሊን ግንብ ለረዥም ጊዜ ሲከፋፍለን ቆይቷል። አሁን ደግሞ በእኛ ላይ አዲስ የሚከፋፍለን መስመር እያሰመሩ እና ግንብ እየገነቡብን ነው” ነበር ያሉት ፑቲን።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፑቲን የጦር ኃይል ትዕይንት
ፑቲን የጦር ኃይላቸውን በመጠቀም በቀድሞው ሶቭየት ግዛቶች ያሉ የምዕራብ መሪዎች ደጋፊዎችን ለማዳከም መዘጋጀታቸውን ለማሳየት ጊዜ አልወሰደባቸውም።
እንደ አውሮፓውያኑ 2008፣ የሩሲያ ኃይሎች የጆርጂያ ጦርን ድል በማድረግ ሁለቱን የተገነጠሉ ክልሎችን አብካዚያን እና ደቡብ ኦሴቲያን ተቆጣጠሩ። ይህ ግጭት ከጆርጂያ ከዚያም የኔቶ ፕሬዝዳንት ደጋፊ ከሆኑት ሚኻይል ሳካሽቪሊ ጋር በነበረ የግል ጠብ ነበር የተቀሰቀሰው።
በዚህ ጊዜ ቭላድሚር ፑቲን ለሦስት ተከታታይ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ሕገ መንግሥቱ ስለከለከላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ከ2008 እስከ 2012 ድረስም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ሆኖም ሥልጣኑ ከእጃቸው እንዳልወጣ ግልጽ ነበር።
በ2021 ላይ ሕጉን በማሻሻል የሥልጣን ጊዜ ገደቡን አንስተውታል። ለዚህም ነው ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር የቻሉት። ከፈለጉ ደግሞ ለስድስተኛ ጊዜም ሊወጥሉ ይችላሉ።
የሩሲያ ተቃውሞ ማብቂያ
እንደ አውሮፓውያኑ 2011 ሶቭየት ኅብረት ከፈራረሰች በኋላ በፓርላማ ምርጫ ማጭበርበር በሚል በሩሲያ ዋና ዋና ከተሞች ሰፊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።
ይህንን ተቃውሞ ከመሩት መካከል ሊበራሉ በ1990ዎቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቦሪስ ኔምስቶቭ አንዱ ነበሩ።
ሌላኛው ደግሞ የፑቲንን ፓርቲ ሩሲያ ዩናይትድን “የሌቦች እና የአጭበርባሪዎች ፓርቲ” ሲል የፈረጀው ፀረ ሙስና አቀንቃኙ ፀሐፊ አሌክሲ ናቫልኒ ነበር። አሁን ላይ እውነተኛ ተቃዋሚዎች ጨርሶውኑ ጠፍተዋል።
ኔምስቶቭ እንደ አውሮፓውያኑ 2015 በክሬሚሊን በሚገኝ ድልድይ ላይ ተገድለዋል።
ናቫልኒም ጥር 2021 ላይ ወደ እስር ቤት ከመወርወሩ እና ከሦስት ዓመታት እስር በኋላ ከመሞቱ በፊት በ2020 ነርቭን በሚጎዳ ኬሚካል ተመርዞ ነበር። የናቫልኒ ባለቤት ለግድያው ቭላድሚር ፑቲንን ተጠያቂ አድርጋለች።
ፑቲን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ድጋፍ ያገኙ ሲሆን፣ ለእርሳቸው በቀጥታ ሪፖርት የሚያደርጉ ብሔራዊ ዘብ አቋቁመዋል።
ፑቲን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲሳተፉም ይታያሉ።
የሕዝብ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎችም የሉም። አዲስ የወጡ የወንጀል ሕጎች ሠራዊቱን የሚያጥላሉ፣ የሐሰት ዜና የሚያሰራጩ ሰዎችን ኢላማ በማድረግ ተቃውሞዎችን ለማፈን በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላሉ።
የሩሲያ ሚዲያም በክሬሚሊን ቁጥጥር ሥር ያለ ነው።
ፑቲን የቀድሞው ታማኛቸው የቅጥረኛ ቡድን መሪ ይቭጌኒ ፕሪጎዥን ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ወታደሮቹን ወደ ሞስኮ እንዲገሰግሱ ባዘዘ ጊዜ ከባድ አመፅ አጋጥሟቸው ነበር። ነገር ግን እንቅስቃሴውን በአጭሩ ቀጭተው ፕሪጎዥን እንቆቅልሽ በሆነው የአውሮፕላን አደጋ ተገድሏል።

የፎቶው ባለመብት, ALEXEY DRUZHININ/SPUTNIK/AFP
የዩክሬን ጦርነት
ፑቲን በዩክሬን ላይ የከፈቱት ጦርነት የጀመረው የካቲት 2022 (እአአ) አይደለም። ጦርነት የጀመሩት የዩክሬንን ግዛት የሆነችውን የክራይሚያን በ2014 (እአአ) ከያዙ በኋላ ነው።
የዩክሬን የሞስኮ መሪ ደጋፊ በኪዬቭ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ከሥልጣን በተወገዱበት ምሽት፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ሌሊቱን ሙሉ ስብሰባ አድርገው ክራይሚያን የሩሲያ የማድረጊያ ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከዚያም የሩሲያ ደጋፊዎች የዩክሬንን ዶንባስ ክልልን ያዙ። ከዚያም ፑቲን በሰሜን በምዕራብ እና በደቡብ የዩክሬን ተመራጩን ፕሬዝዳንት ለማስወገድ እና ኪዬቭን ለመቆጣጠር እስከወሰኑበት 2022 ድረስ ለስምንት ዓመታት ያህል በምሥራቅ ክፍል ጦርነት ተካሄደ።
ሁልጊዜም ጦርነቱ የተካሄደበትን ምክንያት ለማስረዳት ይፈልጋሉ። ረጅም ጽሁፍ ጽፈዋል፣ ንግግር አደርገዋል እና ለጥቂት የውጭ ጎብኚዎች ገለጻም አድርገዋል።
ሆኖም ይህ ሁሉ የተዛባ እና የተመረጠ ታሪክ ነው።
የሶቭየት ጭቆና ሰለባዎችን ለአስርተ ዓመታት ሲዘክር የቆየው የሲቪል መብት ቡድን መታሰቢያም ታግዷል።
የድርጅቱ ፕሬዚደንት ኦሌግ ኦርሎቭ “ፑቲን የፋሽስት ሥርዓትን ይፈልጉ ነበር።አግኝተውታል” በማለታቸውም ታስረው ነበር።












