ፑቲን ከምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ "በላይ" ግልጽነት በነበረው ምርጫ አሸናፊ ሆኛለሁ አሉ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ ጠቅላላ ምርጫ አገሪቱን ለአምስተኛ ዙር መምራት የሚያስችላቸውን ድምጽ ማግኘታቸውን ይፋ አደረጉ።

ከአጠቃላይ ከተሰጠው ድምጽ 87 በመቶ የሚሆኑት መራጮች ለፑቲን ድምጽ መስጠታቸውን ምርጫ አስፈጻሚው ማሳወቁን ተከትሎ ፑቲን ምርጫው ከበርካታ ምዕራባውያን አገራት ዴሞክራሲ በላይ ግልጽነት የታየበት ምርጫ ነበር ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ በዚህ ምርጫ ተዓማኒ የሆነ ትክክለኛ ተፎካካሪ የምርጫው ተሳታፊ አልነበረም።

በዚህ ምርጫ ወቅት በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈው የተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር። በተቃውሞ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ 80 ሩሲያውያንም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የአሌክሲ ናቫልኒ ደጋፊዎች ተቃውሞ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ-ስርዓቱን ቢያዘገይም በምርጫው ውጤት ላይ ግን ምንም ለውጥ አላመጣም።

እንደ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አገራት ምርጫው ነጻ እና ገለልተኛ ያልሆነ ነው ሲሉ ተችተውታል።

በሩሲያ በኃይል በተያዙ የዩክሬን ግዛቶች የሚገኙ ነዋሪዎችም ለሦስት ቀናት በቆየው ድምጽ አሰጣጥ ተሳታፊ ሆነዋል።

የምርጫ ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ውጤቱ “የሩሲያን አንድነት እና ሩሲያውያን ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያላቸውን አስደናቂ ድጋፍ ያሳየ ነው” ሲሉ ዘግበዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ባወጁበት ንግግራቸው ሞስኮ ያካሄደችው ምርጫ ከዋሽንግተን በላይ “ተዓማኒ እና ግልጽ የሆነ ዓላማ ያለው ነው” ካሉ በኋላ “በአሜሪካ በፖስታ አማካይነት ድምጽ እንደሚሰጡት አይደለም። . . . እዛ [አሜሪካ] ድምጽ በ10 ዶላር መግዛት ይቻላል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፑቲን ይህን ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ እስከ 2030 በሥልጣን ላይ ይቆያሉ። ፑቲን ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የቆዩ ሲሆን ይህም ከሶቪዬት አምባገነን መሪ ጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል በሩሲያ ታሪክ ለረዥም ጊዜ ሥልጣን ላይ የቆዩ መሪ ያደርጋቸዋል።

በዚህ ምርጫ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የኮሚኒስት ፓርቲ ዕጩ ኒኮላይ ክሃሪቶኖቭ 4 በመቶ የሚሆን ድምጽ በማግኘት ከፑቲን ቀጥሎ ብዙ ድምጽ የሰበሰቡ ተፎካካሪ ሆነዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ድምጻቸውን የሰጡት የክሬምሊን አስተዳደር እውነተኛ ተፎካካሪ በምርጫ እንዳይሳተፍ በማድረጉ ነው።