ትክክለኛ የሕይወት አጋር ማግኘት እና ስኬታማ ግንኙነት መመሥረት ለምን አስቸጋሪ ሆነ?

በዚህ ዘመን በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች ውሃ ጣጫቸውን ለማግኘት እየተቸገሩ ነው። በበርካታ አገራት ውስጥም ለሕይወት አጋርነት የሚጣመሩ ጥንዶች ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በቻይና ውስጥ የተፈጸሙ ጋብቻዎች ቁጥር ከግማሽ በላይ ቀንሰዋል። ቀደም ባለው ዓመት 13 ሚሊዮን ጋብቻዎች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ በተጠናቀቀው 2024 ግን ከ6 ሚሊዮን ብዙም የበለጠ አይደለም።
በፊንላንድ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በጋራ ይኖሩ የነበሩ ጥንዶች ቤተሰብ ወደ መመሥረት ከመሸጋገር ይልቅ አብዛኞቹ ወደ መለያየት እያመሩ ነው።
ለመሆኑ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሰዎች ዘላቂ ግንኙነት መመሥረት ለምን ፈታኝ ሆነባቸው?
ከአሜሪካ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ከ18 አስከ 24 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በተለይ ወንዶች፣ በቡድን ከሌሎች ሰዎች ጋር ጊዜያቸውን ከማሳለፍ ይልቅ ብቻቸውን መሆንን ይመርጣሉ።
በተጨማሪም በአሁኑ ዘመን ወጣቶች ከሌሎች ሰዎች ጋር ጊዜያቸውን ከማሳለፍ ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ፣ ጌም በመጫወት እና ቴሌቪዥን በመመልከት ያጠፋሉ።
ወጣቶች ብዙ ሰዓት በኢንተርኔት ላይ የሚያጠፉ ሲሆን፣ እዚያም ከአቻዎቻቸው ጋር የመተዋወቅ እና ግንኙነት የመመሥረት ዕድል አላቸው። ነገር ግን የፍቅር ተጣማሪዎችን የሚያገናኙ መተግበሪያዎች ተጠቃሚዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ሴንሰር ታወር' የተባለው የገበያ መረጃዎች አጥኚ ተቋም እንደሚለው፣ የዓለማችን ስድስቱ ዋነኛ የፍቅር ጓደኛ አገናኝ መተግበሪያዎችን ለመጠቀም የሚያወርዱ ሰዎች አሃዝ ባለፈው ዓመት በ18 በመቶ ቀንሷል። ይህም በመተግበሪያዎቹ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ቅናሽ ነው ተብሏል።
የመተግበሪያዎቹ ተጠቃሚዎች መሰላቸት፣ መድከም እና በብዙ የግንኙነት መተግበሪያዎች መጨናነቅ ገጥሟቸዋል የሚሉት በአሜሪካ አሪዞና ስቴት ዩኒቨርስቲ የግንኙነት እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሌዝሊ ሻራቢ ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ ትውውቅን እንጂ ከምኞት እና ከፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣሙ ተጣማሪዎችን አለማግኘታቸው ነው።
በዚህ ውስጥ ተመራማሪዋ ተገነዘብኩ የሚሉት አንዱ ጉዳይ ሰዎችን በማጣመሩ ሂደት የጎላ ፈጠራ አለመታየቱ ነው። በተጨማሪም የአብዛኞቹ መተግበሪያዎች አባል የሚሆኑት ከሴቶች ይልቅ በርካታ ወንዶች መሆናቸው ነው።
"ሴቶች ለሚያቀርቡት ተጣማሪ የማቅረብ ጥያቄ የበርካታ ወንዶችን ምላሽ ስለሚያገኙ መልስ ለመስጠት ይቸገራሉ። በዚህም ምክንያት ወንዶች ችላ የመባል ያህል ይሰማቸዋል፤ ይህም በተለየ ተስፋ የሚያስቆርጥ ክስተት ነው" ይላሉ ዶ/ር ሻራቢ።
በተጨማሪም እነዚህ የትውውቅ መተግበሪያዎች በግንኙነት ሂደት ውስጥ ተጠያቂነትን ባለማስተዋወቃቸው የሚያስቀይሙ እና ግድየለሽ ባህሪዎች ይንጸባረቃሉ። "በዚህም የተነሳ ከአንዱ ወደ አንዱ ሲታለፍ ከቁስ ጋር እንጂ ከሰዎች ጋር የሚደረግ ምልልስ አይመስልም" ሲሉ ያለውን ተግዳሮት ይገልጹታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግንኙነት ተጣማሪን ለማግኘት በርካቶች መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ እነዚህ መተግበሪያዎችን መጠቀም እራስን በጨረታ መልክ ለሽያጭ የማቅረብ ያህል ነው በሚል አይደግፉትም።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚንጸባረቁ ፆተኛ አመለካከቶች እና በተለይ የሴቶችን ፍላጎት እና አመለካከትን ለመቀበል እና ለማክበር ዝግጁ አለመሆን ሌላኛው ለግንኙነቶች አለመስመር ምክንያቶች ናቸው።
በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ብቸኛ ከመሆን ጋር የነበረው አመለካከት እየተለወጠ መሆኑን የሚጠቅሱት የሶሲዮሎጂ ምሁሯ ዶክተር አሊስ ኢቫንስ "ብቸኛ መሆን የሚያስከትለው መገለል በመቀነሱ፣ ሰዎች ግንኙነታቸውን አስከወዲያኛው ማቋረጥን ቀላል አድርጎላቸዋል።"
አክለውም "እጅግ ዘመናዊ የመዝናኛ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት ሰዎች በግንኙነታቸው በሚሰላቹ ጊዜ እራሳቸውን አግልለው ከቤት ሳይወጡ ፊልሞችን ማየት ወይም የቪዲዮ ጌሞችን መጫወት ይችላሉ።"
በዚህም ሳቢያ በማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው ጫና እየቀነሰ በመሆኑ በግፊት ምክንያት ወደ መጥፎ ግንኙነት ውስጥ እንዳይገቡ እንደሚያደርግ ዶክተር አሊስ ያምናሉ።
ነገር ግን በወጣቶች መካከል ያለው ትስስር እየላላ እና እየተቋረጠ መሄዱ በእጅጉ ያሳስባቸዋል።
"ወንዶች እና ሴቶች አብረው የወዳጅነት ሰዓት በማሳለፍ የውስጣቸውን እና በዙሪያቸው ባሉ ጉዳዮች ላይ ስላላቸው ምልከታ በቅርበት ካልተወያዩ እንዲሁም ሐሳብ ካልተለዋወጡ አንዳቸው ሌላኛቸውን በጥልቀት ለመረዳት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል" ይላሉ ዶክተር አሊስ።
የፍቅር ተጣማጆችን የሚያገናኙ መተግበሪዎችን የሚያጠኑት ዶክተር ሻራቢ እንደሚሉት ቴክኖሎጂ በተጨባጩ ዓለም ሊኖሩ የሚችሉ ጥሩ አጋጣሚዎችን አጥፍተዋል በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ።
ለአብነትም "በመዝናኛ ቦታዎች ቆንጆ የሚሏቸውን ሰዎች ቢያገኙም ደፍረው ለመቅረብ እና ለማናገር ከመሞከር ይልቅ፣ የመቀራረብ ዕድሉ ካመለጣቸው በኋላ የተጣማሪ መፈላጊያ መተግበሪያዎች ላይ ፍለጋ ውስጥ የገቡ ወጣቶች አጋጥመውኛል" ይላሉ።
በአጠቃላይም በእነዚህ መተግበሪያዎች ምክንያት ለጓደኝነት፣ ለትውውቅ ብሎም ለዘላቂ የአብሮነት የፍቅር ሕይወት ስኬት የሚጠቅመው የሰው ለሰው ግንኙነት እና ቅርርብ ችላ ተብሏል ሲሉ ይደመድማሉ።












