በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችንን ስለ አደጋዎች እንዴት ማስተማር እንችላለን?

ልጆች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
በለጋ ዕድሜያቸው መኪና ሊገጫቸው ወይም ውሻ ሊነክሳቸው ይችላል። ከፍ ሲሉ ደግሞ ለጥቃት፣ ለመጠጥ፣ ለአእምሮ ህመም ወይም ሌላ እክል ይጋለጣሉ።
ሰዎች ወደፊት ሊገጥማቸው የሚችልን አደጋ ሲያውቁ ራሳቸውን በተሻለ ሁኔታ ይጠብቃሉ። ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረግ ለጤና፣ ለገቢ፣ ለአእምሮ ወይም ሌላ ችግር ይዳርጋል።
ዕድሜ ሲጨምር ስለ አደጋ ያለ ግንዛቤም ያድጋል። ልጆች ግን ሊገጥማቸው የሚችለውን አደጋ ባለማወቅ በቀላሉ ሊወድቁ ይችላሉ።
ታዲያ ልጆችን ስለ አደጋ እና ቅድመ ጥንቃቄ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?
በተለያየ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ስለ አደጋ ማስተማር የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ።
የሥነ ልቦና ምሁር ጆሽዋ ዌለር እንደሚሉት የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የሚለውጡ ውሳኔዎች መወሰንን የምንማርባቸው መንገዶች አሉ።
ልጆች ግን በተፈጥሯቸው በለጋ ዕድሜያቸው ላይ ወደፊት ሊመጣ ስለሚችል አደጋ ለማወቅ ያዳግታቸዋል።
ገና ዳዴ የጀመረ ልጁ ራሱን ከአልጋ ላይ ወይም ከጠረጴዛ ላይ ሊጥል ይችላል። ቢወድቅ የሚገጥመው አካላዊ ጉዳት ስለማይታየው ለአደጋ ሊጋለጥ ይችላል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍታ መፍራት የሚጀመረው ስለ ከፍታ ልምድ እና ግንዛቤ ከዳበረ በኋላ ነው።
የፍርሀት መገለጫ የሆኑት እንደ ልብ መምታት ያሉ ምልክቶች በልጆች ላይ የሚታዩት ዕድሜ ሲገፋ ነው።
አንዴ ስለ አደጋ ካወቁ በኋላ ግን ሐሳቡን ቶሎ ነው የሚረዱት።
የሰዎችን ፊት ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ በማየት አደጋን በቀላሉ ይገነዘባሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሰርሊ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ክሪስ አስኪው በጥናታቸው ልጆችን አሳትፈዋል።
ጥናቱ በአውስትራሊያ ብቻ የሚገኙ ማርሱፒያልስ የተባሉ እንስሳትን ያማከለ ነው። አጥኚው ከእነዚህ እንስሳት የሦስቱን ዝርያዎች ምሥል ለስምንት ዓመት ልጆች አሳዩ።
የተወሰኑት ምሥሎች ለብቻቸው ሲታዩ ከተቀሩት ጎን ግን የፈራ ሰው እና ደስተኛ ሰው ይታያል።
ልጆቹ ፍርሃት ያደረባቸው ከፈራ ሰው ምሥል ጋር ተጣምረው የቀረቡትን እንስሳት ሲመለከቱ ነበር። ይህም ማለት የፈራ ሰው እና አብሮት የቀረበውን የእንስሳ ዝርያ የልጆቹ አእምሮ አዛምዶታል።
ጥናቱ ከተሠራ በኋላ በነበሩት ወራት ልጆቹ ፍርሃትን ከእንስሳቱ ጋር አጣምረው ያወሩ ነበር።
በእርግጥ አደጋ ምን እንደሆነ ማወቅ ብቻ የልጆችን ደኅንነት አያስጠብቅም። ለምን? ቢባል የተለያዩ የስሜት ሕዋሳት መረጃ እንዲለዋወጡ ልጆች 10 ዓመት ሊሞላቸው ይገባል።
ማየት እና መስማት እስከሚተሳሰሩ ድረስ ጊዜ ሲወስድ፣ ወደ አንድ ልጅ አደጋ እየመጣ መሆኑን ልጁ ቢያውቅም ራሱን ለመከላከል ጊዜ ይወስድበታል ማለት ነው።
ሌላው ልጆች በቀላሉ ትኩረት ማጣታቸው ነው። ትኩረታቸውን የሚያስቷቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። አንድ ነገር ላይ አተኩረው ዘለግ ላለ ጊዜ ላይቆዩም ይችላሉ።
የመኪና መንገድን ከመሻገራቸው በፊት ግራ እና ቀኝ ማየት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ሊነገራቸው ይገባል። እንዳይዘነጉት ማስታወስም ግድ ይላል።

ልጆች ከፍ ሲሉ ሰውነታቸው እንዲሁም ሆርሞኖቻቸውም ይለወጣሉ። ለምሳሌ ከደስታ ጋር የሚያያዘው ዶፓሚን ለውጥ ያሳያል።
ወጣቶች ከታዳጊዎች በበለጠ ቅጽበታዊ ውሳኔ የሚያስተላልፉት ለዚህ ነው።
የበለጠ ለአደጋ የሚያጋልጡ ድርጊቶች የዚህን ሆርሞን መጠን ከፍ ስለሚያደርጉ፣ ወጣቶች ራሳቸውን ለአደጋ አብዝተው ያጋልጣሉ።
ለምሳሌ የተለያየ ቀለም ያላቸው ጠርሙሶች አሽከርክረው ዒላማ ከመቱ 10 ዶላር፣ ለጥቂት ከሳቱ ደግሞ 5 ዶላር እንደሚሰጣቸው ቢነገራቸው፣ ቀላሉን ምርጫ ይከተላሉ።
አንዳንድ ጥናቶች ወጣቶች በስሜት የሚመሩ ሳይሆን ጠንቃቃ ውሳኔ የሚያሳልፉ እንደሆኑ ይጠቁማሉ። በቀላሉ ዒላማ መትቶ ዶላር ማግኘት፣ ዒላማ ሳይመቱ ቀርቶ ምንም ገንዘብ ካለማግኘት የተሻለ ነው።
አይቪ ደፎ እንደሚሉት፣ ይህ ጥናት ወጣቶች ለአደጋ የማያጋልጣቸው ውሳኔን እንደሚመርጡ ያሳያል።
በኔዘርላንድስ፣ የአምስተርዳም ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት አይቪ፣ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ቁጥጥር ሲወጡ መጠጥ ወይም ሌላም ጎጂ ነገር ከመሞከር ወደኋላ አይሉም።
ይህንን መነሻ በማድረግ ሳይንቲስቶች አደጋ በተለያየ ዕድሜ ባሉ ሰዎች አእምሮ እንዴት ይገመገማል? የሚል ጥናት ሠርተዋል።
በጥናቱ የተነሱት ሁለት ንጽጽሮች ናቸው። የመጀመሪያው የኮንዶምን ጠንካራ ጎን ሁለተኛው ደግሞ ክፍተቱን ያጎላ ንጽጽር ናቸው።
ኮንዶም 5 በመቶ ላይሠራ ይችላል ማለት፣ ኤችአይቪ በደሙ ካለ ሰው ጋር ወሲብ ሲፈጸም በቫይረሱ የመያዝ ዕድል 5 በመቶ ነው ማለት ነው።
በተቃራኒው ኮንዶም 95 በመቶ አስተማማኝ ነው ማለት፣ ኤችአይቪ በደሙ ካለ ሰው ጋር ወሲብ ሲፈጸም በቫይረሱ ያለመያዝ ዕድል 95 በመቶ ይሆናል ማለት ነው።
ሁለቱ ንጽጽሮች ተመሳሳይ መረጃ ነው የሚሰጡት። ልዩነታቸው አንደኛው ጥንካሬ ላይ ሌላው ደግሞ ክፍተት ላይ ማተኮራቸው ነው።
አንድ ሰው ሁለቱም አማራጮች ተመሳሳይ መረጃ እንደሚሰጡ ካልተገነዘበ መረጃን የማብላላት አቅሙ ላይ ጥያቄ ያጭራል።
መረጃ በምን መንገድ ቀረበ የሚለውን ከመረጃው ይዘት ጋር መሳ ለመሳ መረዳት ለሚችል ሰው በሁለቱ ንጽጽሮች መካከል ልዩነት አይኖርም።

በዚህ ጥናት የተሳተፉ ወጣቶች ስለቀጣይ ሕይወታቸው የሚያስቡበት መንገድ ተገምግሟል። አነስተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ወጣቶች ኋላ ላይ የአደገኛ ዕጽ ተጠቃሚ እና ወንጀል ፈጻሚም ሆነው ተገኝተዋል።
ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ ከከእምሮ ልኅቀት ጋር ብቻ አይገናኝም። ሰዎች ነገሮችን የሚያዩበት መንገድ ለውሳኔያቸው ግብዓት ይሆናል።
ወላጆች ልጆቻቸው በተለያየ ዕድሜ ላይ ሳሉ ለየዕድሜ ክልሉ በሚመጥን መንገድ ለልጆቻቸው ስለ አደጋ እና ቅድመ ጥንቃቄ ማስተማር እንዳለባቸው ከላይ የተጠቀሱት አጥኚዎች የሚስማሙበት ነጥብ ነው።
ራስን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? ከስሜታዊነት መውጣት የሚቻለው እንዴት ነው? አንድ ውሳኔ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንዴት ቀድሞ ማወቅ ይቻላል? የሚሉት ጥያቄዎች በየዕድሜ ደረጃው መመለስ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
አንድ አሜሪካዊ የ10ኛ ክፍል የታሪክ መምህር ተማሪዎቹ በታሪክ የተፈጠሩ ሁነቶችን መለስ ብለው እንዲቃኙ እና እነሱ በዚያ ዘመን ቢኖሩ ምን ዓይነት ውሳኔ ሊወስኑ እንደሚችሉ እንዲያስቡ ያደርጋሉ።
ይሄን መሰል መንገድ ራሳችንን በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ከተን ውሳኔያችን ቀድመን እንድናገናዝብ ይረዳል። ልጆችም ይሄንን ክህሎት እንዲያዳብሩ ቤተሶች ማስተማር ይኖርባቸዋል።












