ወላጆች ልብ ሊሉት የሚገባው ልጆችን ቅብጥብጥ እና ትኩረት እንዲያጡ የሚያደርገው እክል

ዶ/ር ናኦድ ፍርዱ

የፎቶው ባለመብት, ናኦድ

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ናኦድ ፍርዱ

ዶ/ር ናኦድ ፍርዱ ይባላል። ገና በሕጻንነቱ ከእኩዮቹ በተለየ መልኩ በአንድ ቦታ ለረጅም ጊዜ የመቀመጥ ብሎም ትኩረት አድርጎ ለመቆየት ይቸገር እንደነበር ያስታውሳል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ጤና ሳይስ ኮሌጅ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የኢፕዲሞሎጂ የትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆነው ዶ/ር ናኦድ፣ በልጅነቱ በተለይም ከመጠን ያለፈ ፈጣን ልጅ እንደነበረ ይናገራል።

“በኤሌክትሪክ ገመዶች በተሞላ የቤታችን ኮርኒስ ውስጥ ገብቼ ስዘዋወር ትዝ ይለኛል። የማልወጣው ዛፍ አልነበርም። በአጠቃላይ ውስጤ የታመቀ ጉልበት ነበረኝ” ይላል።

ኤዲኤችዲ ምንድን ነው?

ልጆች ጨዋታ ይወዳሉ። መሮጥ እና መዝለል የማንኛውም ልጅ ባህሪይ ነው። ነገር ግን በተለየ ሁኔታ ለነገሮች ትኩረት የማይሰጡ ወይም ከተገቢው በላይ መቅበጥበጥ የሚታይባቸው አሊያም ዘወትር ለመረጋጋት የሚቸገሩ ከሆነ ወላጆች ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል።

ይህ ባለሙያዎች Attention-deficit/hyperactivity disorder (ADHD) ኤዲኤችዲ ተብሎ የሚጠራው የአዕምሮ እድገት እክል ያለባቸው ሕጻናት በአንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ለመቆየት ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል።

በዚህም ምክንያት ነገሮችን በቶሎ መርሳት፣ የጀመሩትን ነገር ለመጨረስ መቸገር፣ የተለያዩ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ማድረግ፣ በቸልተኝነት መሳሳት እንዲሁም በአግባቡ የማዳመጥ እና ትዕዛዝን ተረድቶ ያለመፈጸም፣ የኤዲኤችዲ ዋነኛ ምልክቶች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ ማውራት፣ ከልክ በላይ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ አደጋን የመፍራት መጠን ዝቅተኛ መሆን ብሎም ሰዎች ንግግራቸውን እስከሚጨረሱ ያለመጠበቅ እና ማቋረጥ ሌሎቹ ምልክቶች ናቸው።

ነገር ግን አንድ ሰው የኤዲኤችዲ ተጠቂ ነው ወይስ አይደለም የሚለው በበርካታ መመዘኛዎች በሃኪሞች የሚረጋገጥ ነው።

በርካቶች ይህ እክል አለባቸው

ዶ/ር ናኦድ ልጆች በዚህ የኤዲኤችዲ ተጠቂ እንደሆኑ ባለመረዳት ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ እንደ ረባሽ እና አስቸጋሪ በማየት የሚደርሰው ቅጣት እና ፍረጃ ልጆች ገና በለጋ እድሜያቸው ለድባቴ ብሎም ለማንነት ቀውስ እንዲዳረጉ እንደሚያደርግ የራሱን ታሪክ በማጋራት ያስረዳል።

ይህ በተለይም በትምህርት ቤት ውስጥ ይብሳል የሚለው ዶ/ር ናኦድ፣ አንድ ቦታ ለረዥም ሰዓታት መቀመጥን የአዕምሮ ሁኔታው የማይፈቅድለት አንድ ልጅ ቀኑን ሙሉ አንድ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ እንዲውል ማድረግ ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ ይከተዋል ይላል።

በአሜሪካ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 10 በመቶው የአሜሪካ ሕዝብ የኤዲኤችዲ ተጠቂ ሲሆን፣ ይህም ወደ ስድስት ሚሊዮን ገደማው የሚሆኑ ሰዎችን የሚመለከት ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ደግሞ 3.5 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት፣ ብሎም ሁለት በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች የዚሁ የአእምሮ ችግር ተጠቂ ናቸው።

እንዴት መለየት ይቻላል?

ኤዲኤችዲ የፊተኛው የቀኝ የአንጎል ክፍል እድገቱን ሳይጨርስ ሲቀር የሚከሰት የአእምሮ ጤና ሁኔታ ነው። ይህ የአንጎል እድገት ችግር በዋነኝነት በዘር የሚሸጋገር ሲሆን፣ ነፍሰ ጡር ሆነው ሲጋራ የሚያጨሱ እናቶች ልጆቻቸው ኤዲኤችዲ ተጠቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ዶ/ር ናኦድም ወላጅ አባቱ ኤዲኤችዲ እንደነበራቸው ይናገራል። ነገር ግን እርሱ ሐኪም ሆኖ እና ኤዲኤችዲ እንዳለበት እስኪያውቅ ድረስ ይህንን ሳያውቁ መኖራቸውን ይናገራል።

ኤዲኤችዲ ያለበትን ልጅ በቅድሚያ መለየት የሚችሉት ቤተሰቦች እንዲሁም መምህራን ናቸው ይላል ዶ/ር ናኦድ።

ቤተሰቦች ወይም መምህራን ልጆች ትኩረት የሚጠይቁ ሥራዎችን እና የትምህርት የቤት ሥራዎቻቸውን መስራትን የመሳሰሉ ተግባራትን ማከናወን የማይፈልጉ ከሆነ ከሆነ አንድ ምልክት ሊሆን ይችላል።

በተጨማሪም የሚቀርብላቸው ጥያቄ እስኪያልቅ ሳይጠብቁ መልስ ለመስጠት የሚቸኩሉ ከሆነ፣ በየቀኑ ሊደረጉ የሚገቡ መደበኛ ተግባራትን የሚረሱ፣ ከሆነ ምልክቶቹን በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል ሲል ዶ/ር ናኦድ ይመክታል።

ከጀርባ የሚታይ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ ከልጆቹ አስተዳደግና አያያዝ ጋር በተገናኘ የሚከሰት የባህሪይ ችግር አድርጎ ስለሚመለከተው በቁጣና በቅጣት እንደሚስተካከል ያምናል።

ነገር ግን በተፈጥሮ የሚከሰት የአእምሮ እድገት ውስንነት ስለሚሆን በቅርበት መከታተል፣ እንዲሁም ከባlሙያዎችና ከመምህራን ጋር መመካከር ያስፈልገዋል።

“ልጆቹ ጤነኛ ቢሆኑም እንኳን ሁሉም ሰው ኤዲኤችዲ ምንድነው የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ሊያውቅ ይገባል። ምክንያቱም ኤዲኤችዲ በርካታ ሰዎችን የሚያጋጥም ውሱንነት ስለሆነ” ሲል ዶ/ር ናኦድ ያሳስባል።

በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት ልጆች ይህ አይነቱ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ካላቸው ለመለየት የሚያስችሉ መጠይቆች ችግሩን ለመለየት መነሻ ሊሆን እንደሚችልም ያክላል።

ነገር ግን ይህንን ውሱንነት ለመለየት የሐኪም እርዳታ እንደሚያስፈልግ እና ልጆች የሚያሳዩትን የልጅነት ባህሪይ ከኤዲኤችዲ ጋር ለመለየት ቤተሰቦች ጥረት ማድረግ አለባቸውም ይላል።

እነዚህን ልጆች ውጤታማ እንዲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመላው ዓለም ከ100 ሕጻናት ውስጥ 10ሩ ኤዲኤችዲ የሚኖርባቸው ሲሆን አስፈላጊውን ሕክምና ካገኙ ግን እጅግ አመርቂ ውጤትና መሻሻል የሚታይበት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ።

እንዲህ አይነቱ ውስንነት ባለባቸው በአዋቂዎች ዘንድም እንዲሁ በሚደረግላቸው የህክምና መፍሔዎች አስደናቂ ሊባል የሚችል ውጤት ይታይባቸዋል።

በተለይም ቤተሰቦች ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሳይረሱ እንዲያከናውኑ ማገዝ፣ ቋሚ የሆነ የጨዋታ እና የጥናት ጊዜ ማስለመድ፣ እንደ ቦርሳ እና የትምህር መርጃ መሳሪያዎቻቸውን የመሳሰሉ ንብረቶቻቸውን ቋሚ የሆነ ቦታ እንዲያስቀምጡ በማስለመድ ማገዝ ይችላሉ።

ጥናቶች እንደሚያመለከቱት ኤዲኤችዲ ካለባቸው ልጆች መካከል ድጋፍ ካገኙ እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት መዳን የሚችሉ ሲሆን፣ 60 በመቶ ያሆኑት ግን አስከ አዋቂነት ዕድሜያቸው ድረስ አብሯቸው ይቀጥላል።

ነገር ግን የውስንነቱን ጫና ባግባቡ ለመቋቋም የሚያስችሉ መንገዶችን በመከተል ለመቆጣጠርና ለውጦችን ማምጣት ይችላሉ።

ዶ/ር ናኦድ እንደሚለው ከሥነ ልቦና ምክር፣ ባህሪይን ማሰልጠን ብሎም መሰል የሕክምና ድጋፎች ከማግኘት ባሻገር ለኤዲኤችዲ የሚሰጡ መድኃኒቶች ዋነኛ መፍትሔ ተደርገው እንደሚታዩ ያስረዳል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ውሰጥ አንዱም መድኃኒት እንደማይገኝ በመግለጽ፣ ጉዳዩ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ነው ይላል።

ብዙ ጊዜ ልጆች “አስቸጋሪ፣ ቅብጥብጥ ወይም ረባሽ” ናቸው ከማለት ይልቅ፣ የአዕምሮ እድገት ውሱንነት ከሆነ ማጣራት ይችላል ብሎ ማሰብ ያለመለመዱ አሳሳቢ ነው ይላል።

ኤዲኤችዲ ያለባቸው ሰዎች ለሱስ መጋለጥ፣ የሚያሽከረክሩ ከሆነ ከመኪና አደጋ መጋለጥ፣ በትዳር ውስጥ ለሚያጋጥሙ ችግሮች፣ የገንዘብ ማባከን፣ በሥራ ቦታ ላይ ስኬታማ ያለመሆን፣ ለረጅም ሰዓት ማንበብ ያለመቻል እንደሚያጋጥማቸው ጥናቶች ያመላክታሉ።

ለዚህም ነው ዶ/ር ናኦድ ኤዲኤአችዲን ትኩረት ሰጥቶ መከታተልና መደገፍ ከግለሰብ በላይ ለማኅበረሰብም ጠቃሚ ነው የሚለው።

ዶ/ር ናኦድ በኤዲኤችዲ ላይ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ የሚገልጽ ሲሆን፣ ከእራሱ አንጻርም ምስክርነቱን ሲሰጥ ጠቃሚ ድጋፍ በማግኘቱ አሁን የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደለ ያስረዳል።

ነገር ግን በርካቶች በወላጆችና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ዘንድ ባለ የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት፣ እንደ እሱ ድጋፍ ባለማግኘታቸው በውሱንነቱ ጫና ውስጥ ሕይወታቸውን ለመግፋት ይገደዳሉ።

ስለዚህም በዋናነት ቤተሰብ፣ በልጆቹ ዙሪያ ያለው ማኅበረሰብ እንዲሁም መምህራን የሚያደርጉት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ነው።