“ስለ አዕምሮ ጤና በግልፅ መነጋገር ለሁላችንም ጤንነት ነው” ያዕቆብ ተክዔ

የፎቶው ባለመብት, Yakob
ያዕቆብ ተክዔ (ዶ/ር) በአሜሪካው ፔንሲልቬንያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አዕምሮ ባለሙያ ነው። ያዕቆብ በትምህርቱ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት፣ በሥራው ቴራፒስትና የሙሉ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነው።
ያዕቆብ ተውልዶ ያደገው በኤርትራ ሲሆን የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል ከበቃበት ጊዜ አንስቶ የሥራ ዓለሙን እስኪቀላቀል ድረስ ኑሮው በአሜሪካ ነው።
የያዕቆብ ሥራ የሚያተኩረው በስደትና በስደተኞች ላይ ሲሆን በተለይም ደግሞ ከአፍሪካ፣ አብልጦም ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ለተሰደዱ ሰዎችን የአዕምሮ ጤና ድጋፍ እና ክትትል ያደርግላቸዋል።
ያዕቆብ ከባድ አደጋ፣ የፆታ ወይም የወሲብ ጥቃት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል።
ኮሮናቫይረስ እና የአእምሮ ጤና
ሥራው በይበልጥ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት መክበዱን የሚናገረው ያዕቆብ በነባር አዕምሯዊ ተፅዕኖዎች ላይ ተደርቦ ከወርሽኙ ጋር የመጡ የተለየያዩ ውጥረቶችንም ጭምር ለማቃለል ብዙ ሥራ መሠራት እንደነበረበት ይናገራል።
ወረርሽኙ የጀመረበት ወቅት በተለይ ፍራቻ፣ መገለልና የመሳሰሉ ተያያዥ ችግሮች ስለነበሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራውያን በተለየ መልኩ እገዛ ያስፈልጋቸው እንደነበር ያስታውሳል።
በስደተኞች ላይ ተዘውትረው ይታዩ የነበሩ የቋንቋ ቀርነቶች፣ የባህል ልዩነቶችና ከሃገሩ ማህብረሰብ ጋር የመዋሃድ ችግሮች ላይ ወረርሽኙ ያመጣው የመራራቅ፣ ያለ መጠያየቅና የብቸኝነት ኑሮ አዕምሮ ላይ ከበድ ያለ ተፅዕኖ እንደነበረው ገልጿል።
ይህንንም ለመቅረፍ ከመንግሥት የሚመጡና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሚናገሯቸው ቋንቋዎች እንዲደርሷቸው እናደሚያደርጉ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት ተናግሯል።
በተጨማሪም ለአዕምሮ ጤናም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በየጊዜው በሚረዷቸው ቋንቋዎች እና መንገድ እንደሚያደርስ ይናገራል።
ያዕቆብ እነዚህን እና ሌሎች ያሉ ችግሮች በሙሉ በጥሞና ካሰበባቸው በኋላ ሰዎች በቀላሉ፣ ሳይሳቀቁና ሰው አየን አላየን ሳይሉ መረጃዎችን የሚያገኙበትን መንገድ ማሰላሰል ጀመረ።
"በባህላችን ስለ አዕምሮ ጤንነት በግልፅ ማውራት ወይም መነጋገር ከባድ በመሆኑና በግልፅ የሚያወሩም ሰዎች መድልዖ ስለሚገጥማቸው በፈቃደኝነት እርዳታ ለማግኘት የሚጥሩ ኢትዮጵያውያን ወይም ኤርትራውያን የሉም። ይህ ደግሞ ችግሩን አያጠፋውም፣ ማለት ስለችግሩ ስላልተወራ ችግሩ ይሰወራል ማለት አይደለም። በተለይ የአዕምሮ ጤና መጓደል ደግሞ ሥር እየሰደደና እየተባባሰ የሚመጣ በመሆኑ ችግሩን እጥፍ ያደርገዋል። ለዚህም ነው መፍትሄ ማግኘት ፈልጌ የነበረው" ይላል ያዕቆብ።

የፎቶው ባለመብት, Yakob
ዩቲዩብ እንደ መፍትሄ
ኢንተርኔት የበርካቶች ህይወት አካል በሆነት በዚህ ዘመን ቀላሉ መፍትሔ ዩቲዩብ መሆኑ የተገነዘበው ያዕቆብ፣ የራሱን ቻናል በመጀመር ማስተማር፣ አስፈላጊ መረጃዎችንና ምክሮችን ማስተላለፍ ጀመረ።
እንደዚህ ማድረጉ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ቢያንስ ከቤታቸውም ሆነው መድልዖን ሳይፈሩ አስፈላጊውን እርዳታ ለማግኘት ያስችላቸዋል ብሎ አስቦ እንደሆነ ይገልፃል።
"በርግጥ አንድ ባንድ እያገኘሁ ጊዜ ወስደን እንደምረዳቸው ሰዎች ያህል በዩቲዩብ ጥልቀት ያለው እርዳታ ለማድረግ ይከብዳል። እንደዚያም ቢሆን ግን ዋና ዋና መልዕክቶችን ስለማስተላልፍበት ሰዎች ሳይሳቀቁ በእራሳቸው ጊዜ የሚጠቅሟቸውን የምክር አገልግሎቶች ማግኘት ይችላሉ" ይላል።
ያዕቆብ በዩቲዩብ የሚያሰራጨው መልዕክት የሚኖረውን ጥቅም ሲያስረዳም "አብዛኛውን ጊዜ ስሜታቸውንና አዕምሮዋቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ነገሮችን አምቀው ስለሚይዙ በጊዜ ሂደት ጉዳቱ የከፋ ይሆንባቸዋል። ለዚህ ነው ሰዎች ቢያንስ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማወቃቸው በእራሱ የመጀመሪያው እርምጃ የሚሆነው" ይላል።
አክሎም "እንደ ኮቪድ ዓይነት ወረርሽኝ ደግሞ ሰዎችን ቤት እንዲቀመጡ የሚያደርግ ከሆነ ወይም የለመዷቸውን ማህበራዊ ስብስቦች በሚያስቀርባቸው ጊዜ ተፅዕኖው ይበዛባቸውና ነባር የአዕምሮ ችግሮችን ያባብስባቸዋል" ይላል።
መገለል እና የአእምሮ ጤና
ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎች በአእምሮ ጤና ላይ ያላቸው አመለካከት እየተስተካከለ እንደሆነ የሚናገረው ያዕቆብ፣ ከአምስት ዓመታት በፊት የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘመቻዎች በሚያካሄድበት ወቅት የነበረው ምላሽና አሁን የሚሰጠው ምላሽ በጣም ልዩነት እንዳለው ይገልፃል።
ያዕቆብ ከአምስት ዓመታት በፊት የነበረበትን መሰናከል በማስታወስ " ስለ አዕምሮ በሽታዎች ግንዛቤ ለማስፋት በምሠራበት ወቅት ብዙ ሰዎች ዓላማዬን ይጠራጠሩት ነበር። እንደውም በርካታ ሰዎች የአዕምሮ በሽታ መኖሩን እራሱ እንደሚጠራጠሩ ይነግሩኝ ነበር" ይላል።
ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንዳያገኙ የሚያከለክሏቸው በማህበረሰባችን ሊገጥሟቸው የሚችለውን መገለል በመፍራት እንደሆነም ያስረዳል።
በተጨማሪም "የአዕምሮ ችግርን ብዙ ሰው በአንድ ጊዜ ሳይታሰብ እንደ ዱብ ዕዳ የሚወርድ ነገር ይመስላቸዋል። ነገር ግን በሂደትና ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረት፣ የመንፈስ ጭንቀት ሲደራረብ ካለበለዚያ በአግባቡና በተገቢው ጊዜ እርዳታ ሳይገኙ ሲቀር የሚከሰት ነው" ይላል።
እንደዚህም ሆኖ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎች ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነና ኮሮና ባይመጣ ኖሮ ሙሉውን የ2020ን ዓመት በተለያዩ የአሜሪካና የካናዳ ከተማዎች በመሄድ ንግግር እንዲያደርግና ለኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እርዳታ እንዲሰጥ ተጠይቆ እንደነበር ይናገራል።
"የአዕምሮ ታማሚ ሲባል እርቃናቸውን እየሮጡ በድንጋያ ሰዎችን የሚያባርሩ ግለሰቦችን ነው ሰዎች በአዕምሮዋቸው የሚስሉት። ይህ ደግሞ በጣም የተሳሳተ አመለካከት ነው" የሚለው ያዕቆብ አስረግጦ ማስረዳት የሚፈልገው "የአዕምሮ በሽታ ወይም የአዕምሮ ጤና መጓደል የተለያየ መልክ፣ ዓይነትና መገለጫ" እንዳለው ነው ይለናል።
ከሁሉም በላይ "በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በቀጣዮቹ የተወሰኑ ዓመታት የአዕምሮ ጤና መጓደል ወረርሽኝ የምናይ ይመስለኛል" በማለት ይህንንም ለመከላከል በቅድሚያ ከወዲሁ ልናስስባቸው፣ ልንነጋገርባቸውና ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸውን ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Yakob
የአእምሮ ጤና መጓደል ምልክቶች
አእምሮ ጤና መጓደልን በተመለከተ በዋነኛነት ልንከታተላቸው ከምንችላቸው ምልክቶች መካከል፡
- የሥራ አቅም፣ ፍላጎት፣ አምሮት መቀነስ
- የአበላልና የምግብ ፍላጎት በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀየር (ከመጠን በላይ መቀነስ ወይም መጨመር)
- ከሰዎች ጋር የመገናኘት ፍላጎት መቀነስ ወይም መጥፋት
- የእንቅልፍ በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀየር (ከመጠን በላይ መተኛት ወይም ለተከታታይ ቀናት እንቅልፍ ማጣት) መሆናቸውን ያዕቆብ ይዘረዝራል።
እንደ ያዕቆብ ገለጻ እነዚህ ምልከቶች ቀድሞ ማወቅ "እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በቶሎ እንድንደርስላቸው ያስችለናል" ይላል።
የአዕምሮ ጤና መጓደል ቋሚ አይደለም የሚለው ያዕቆብ፣ "አካላዊ በሽታ ሲገጥመን ሆስፒታል/ክሊኒክ ሄደን እንደምንታከመው ሁሉ ለአዕምሯችንም ተመሳሳይ እንክብካቤ ማድረጋችን ተገቢ ነው" ሲል ይመክራል።
"ለብዙ ሰዎች የአዕምሮ ጤና መሰናከል ቋሚ ችግር ይመስላቸዋል ግን እውነታው ከዚህ የራቀ ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው በተለያየ ምክንያት የአዕምሮ ጤናው ሊስተጓጎል ይችላል" በማለት ያብራራል
ኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያንን ለመርዳት ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ያለው ያዕቆብ ሥራው ገና ጅማሬው ላይ መሆኑን ይገልፃል።
አክሎም የሰውን ግንዛቤ ከመጨመርና ከማሳደግ ባለፈ ደግሞ የቋንቋ ተግዳሮቱ ላይ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራል።
















