ኢራን የኒውክሌር ስምምነት ላይ ካልደረሰች "አሰቃቂ" ጥቃት ይጠብቃታል ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸማቸውን ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኢራን በኒውክሊየር ፕሮግራሟ ላይ ከስምምነት ላይ ካልደረሰች ከአሁኑ የከፋ ከባድ ጥቃት ይገጥማታል ሲሉ አስጠነቀቁ።

ኢራን አሜሪካ ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለች እና ለተፈጸመባት ጥቃት እስራኤል ላይ ከባድ አጸፋ እንደምትመልስ እየዛተች በላችበት ወቅት ነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ኢራን በኒውክሊየር ፕሮግራሟ ላይ ስምምነት ካልደረሰች "የባሰ አሰቃቂ" ጥቃት ከእስራኤል እንደሚገጥማት የገለጹት።

ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ አንስቶ ዋና ከተማዋን ቴህራንን ጨምሮ በተለያዩ የኢራን ክፍሎች ላይ በተፈጸሙት የእስራኤል ጥቃቶች የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናትን ጨምሮ ወደ 70 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ኢራን አስታውቃለች።

እስራኤል ግን ዒላማ ያደረገችው ዋነኛውን የኒውክሌር ጣቢያን ጨምሮ ወታደራዊ ተቋማትን መሆኑን ገልጻለች።

በተጨማሪም የኢራን የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን እና ከመሬት ወደ አየር ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን መደምሰሳቸውን ገልጻለች።

አሜሪካ በጥቃቱ ውስጥ እጇ እንደሌለበት እና ኢራን ወደ ስምምነት እንድትመጣ ግፊት ስታደርግ፣ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገራት አገራቱ ከተጨማሪ ጥቃት እንዲታቀቡ ጥሪ እያደረጉ ነው።

የፈረንሳይ እና የጀርመን መሪዎች የኢራንን የኒውክሊየር ፕሮግራምን በማውገዝ ሁለቱ አገራት ግጭቱን ከማባባስ እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፣ የእስራኤልን "ራስን የመከላከል መብትን እንደሚደግፉ" ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ እስራኤል እና ኢራን "ወደ ኋላ በመመለስ ውጥረቱን እንዲያረግቡ" ጠይቀዋል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ባወጡት መግለጫ እስራኤል የፈጸመችው ጥቃት "ዓለም አቀፍ ሕግን ችላ ያለ ግልጽ ጠብ አጫሪነት ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።

ባለፈው እሁድ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተካሄደውን ንግግር ያስተናገደችው ኦማን "ለተባባሰው ውጥረት እና ለሚያስከትለው ጉዳት እስራኤልን ተጠያቂ " ስታደርግ፤ ሳዑዲ አረቢያ የእስራኤልን ጥቃት አውግዛ ድርጊቱ "ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ ያጣሰ ነው" ብላለች።

ቻይና በበኩሏ የተፈጸመው ጥቃት በእጅጉ እንዳሳሰባት እና እስራኤል እና ኢራን የበለጠ መካረር እንዳይከሰት ራሳቸውን እንዲቆጥቡ ጥሪ አርባለች።

ሌሊት ጀምሮ መቀጠሉ እየተነገረ ያለውን የእስራኤን ጥቃት ተከትሎ ኢራንም የአጸፋ ምላሽ እንደሰጠች በሰሜናዊ የእስራኤል ክፍል ውስጥ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ መስማቱን እንዲሁም አንድ ድሮን ተመትቶ መውደቁ እየተነገረ ነው።