ድምጽ አልባዎቹ የሩሲያ ቢሊዮነሮች፡ ፑቲን እንዴት የአገሪቱን ባለሀብቶች ለጦርነት ማሰለፍ ቻሉ?

የፎቶው ባለመብት, ALEXEY NIKOLSKY/SPUTNIK/AFP
የዩክሬን ጦርነት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በሩሲያ ውስጥ የቢሊየነሮች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ነገር ግን ቭላድሚር ፑቲን ሥልጣን በያዙባቸው 25 ዓመታት ውስጥ "ኦሊጋርክ" በመባል የሚታወቁት የሩሲያ ባለፀጎች እና ኃያላን ያላቸውን የፖለቲካ ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አጥተዋል።
ይህ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት መልካም ዜና ነው። ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች የናጠጡትን ባለሀብቶች ወደ ተቃዋሚነት ሊቀይሯቸው አልቻሉም። ይልቁንም የፑቲን የሽልማት እና የቅጣት (carrot and stick) ፖሊሲ ዝምተኛ ደጋፊዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ቀድሞ የባንክ ቢሊየነር የነበሩት ኦሌግ ቲንኮቭ "ቅጣቱ" እንዴት እንደሚሠራ በትክክል ያውቃሉ።
ባለሀብቱ በኢንስታግራም ገፃቸው ጦርነቱን "እብደት" ብሎ በመጥራት ተቃውሟቸውን ባሰሙ ማግስት የኩባንያ ሥራ አስፈፃሚዎቻቸው ከክሬምሊን ተደወለላቸው። በወቅቱ የሩሲያ ሁለተኛው ትልቅ ባንክ የነበረው 'ቲንኮፍ' የተሰኘው ባንክ ከመሥራቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በሙሉ ካላቋረጠ ወደ መንግሥት ሀብትነት እንደሚዛወር ተነገራቸው።
ቲንኮቭ "እንደ ታጋች ነበርኩ፤ የቀረበልህን ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለም። ዋጋ መደራደር አልቻልኩም ነበር" ሲሉ ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሩሲያ በሀብት መጠን አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የቭላድሚር ፖታኒን ኩባንያ ባንኩን መግዛቱን አስታወቀ። ቭላድሚር ፖታኒን የጦር ጄት ሞተሮች ለመሥራት የሚያገለግለውን 'ኒኬል' የተባለ ቁስ አካል የሚያቀ በማቅረብም ይታወቃሉ።
ቲንኮቭ እንደሚናገሩት ባንኩ የተሸጠው ከትክክለኛ ዋጋው 3 በመቶ ብቻ በሆነ ዋጋ ነው። በመጨረሻም ቲንኮቭ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብታቸውን አጥተው ከሩሲያ ወጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Chris Graythen/Getty Images
ይህ ሁኔታ ፑቲን ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ከነበረው በእጅጉ የተለየ ነው። ሶቪየት ኅብረት ከፈረሰች በኋላ ባሉት ዓመታት አንዳንድ ሩሲያውያን ቀደም ሲል በመንግሥት ስር የነበሩ ግዙፍ ድርጅቶችን በመቆጣጠር እና አገሪቱ እየገባችበት የነበረው የካፒታሊዝም መንገድ የፈጠራቸውን ዕድሎች በመጠቀም እጅግ ባለፀጋ መሆን ችለዋል።
በዚህ መንገድ ያገኙት ሀብት በፖለቲካዊ ነውጥ ተሞልታ በነበረችው ሩሲያ ውስጥ ተጽዕኖ እና ኃይል እንዲኖራቸው መንገድ ከፈተላቸው። ይህ ተጽዕኖ የነበራቸው ባለሀብቶችም "ኦሊጋርክ" የሚል ስያሜ ተሰጣቸው።
ኃያሉ የሩሲያ ኦሊጋርክ ቦሪስ ቤሬዞቭስኪ በአውሮፓውያኑ 2000 ፑቲን ወደ ሥልጣን ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውን ይናገራሉ።
ከዓመታት በኋላ ግን ለዚህ ድርጊታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። "ነፃነትን የሚረግጥ እና የሩሲያን ዕድገት የሚያቆም ስግብግብ አምባገነን ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር" በማለት በ2012 ጽፈዋል።
ምንም እንኳ ቤሬዞቭስኪ ፕሬዝዳንቱ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ የተጫወቱትን ሚና አጋንነው አቅርበው ሊሆን ቢችልም፤ የሩሲያ ኦሊጋርኮች መንበሩን የተቆናጠጡትን ሰዎች የመዘወር አቅማቸው የሚካድ አይደለም።
ቤሬዞቭስኪ ይቅርታ ከጠየቁ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በስደት በነበሩባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ምሥጢራዊ በሆነ ሁኔታ ሞተው ተገኝተዋል። የሩሲያ ኦሊጋርኪዎች ፖለቲካዊ ተጽእኖም አብሮ የሞተው የዚያን ወቅት ነው።
ፑቲን በየካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ እንዲፈጸም ትዕዛዝ በሰጡ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የሩሲያ ባለፀጎችን በክሬምሊን ሰበሰቡ።
በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት የተገኙት ባለሀብቶች በጦርነቱ ምክንያት ሀብታቸው ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስበት እንደሆነ ቢረዱም ማድረግ የሚችሉት ነገር አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Hulton Archive/Getty Images
ፑቲን "በዚህ አዲስ ሁኔታ ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ በጋራ እንደምንሠራ እና እንደቀድሞው ውጤታማ እንደምንሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ለባሀብቶቹ ነግረዋቸዋል።
ስብሰባው ላይ የተገኘ አንድ ጋዜጠኛ "የገረጡ እና እንቅልፍ ያጡ ይመስሉ ነበር" ሲል በክሬምሊን የተሰበሰቡትን ቢሊዮነሮች ሁኔታ ገልጾታል።
ወረራ ከመፈጸሙ በፊት በነበረው ወቅት ለሩሲያ ቢሊዮነሮች እጅግ መጥፎ ነበር፤ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ያለው ሁኔታም የተለየ አልሆነም።
የፎርብስ መጽሔት ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ እስከ ሚያዝያ 2022 በነበሩት ወራት ውስጥ የጦርነቱ መጀመር እና ማዕቀቦች እንዲሁም የሩሲያ ገንዘብ የሆነው ሩብል መዳከም የአገሪቱን ቢሊየነሮች ቁጥር ከ117 ወደ 83 ዝቅ አድርጎታል።
ባለሀብቶቹ ድምሩ 263 ቢሊዮን ዶላር ወይም እያንዳንዳቸው ከሀብታቸው ውስጥ በአማካይ 27 በመቶውን አጥተዋል።
ነገር ግን በተከታታይ የመጡት ዓመታት በፑቲን የጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ እጅግ ግዙፍ ትርፍ እንደሚያስገኝ አሳይተዋል።
ለጦርነቱ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ በ2023 እና 2024 ሩሲያ በየዓመቱ ከአራት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ አድርጓል።
ይህ ሁኔታ በቀጥታ የመከላከያ ኮንትራቶችን በመውሰድ ቢሊዮኖችን ማፈስ ላልቻሉት የሩሲያ ባለፀጎች እንኳ መልካም ዜና ነበር።
በፎርብስ የሀብት ጥናት ቡድን ውስጥ የሚሠሩት ጃኮሞ ቶግኒኒ እንደሚናገሩት፤ በ2024 ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሩሲያ ቢሊየነሮች ለሠራዊቱ የተለያዩ ግብአቶችን በማቅረብ ተሳትፈዋል አልያም ከወረራው ተጠቃሚ ሆነዋል።
"ይህ በቀጥታ ያልተሳተፉትን ነገር ግን ከክሬምሊን ጋር የጥቅም ግንኙነት የሚያስፈልጋቸውን አያካትትም። ሩሲያ ውስጥ የንግድ ሥራ የሚያካሂድ ማንኛውም ሰው ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይገባል ብሎ መናገር ስህተት አይመስለኝም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የፎርብስ የባለሀብቶች ዝርዝር እንደሚያሳየው ሩሲያ ውስጥ 140 ቢሊዮነሮች አሉ። ይህ ቁጥር በሩሲያ ታሪክ ከፍተኛው ነው።
አጠቃላይ ሀብታቸው 580 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል። ሀብታቸው ከወረራው መጀመር በፊት ከተመዘገበው የምንጊዜም ከፍተኛው የሀብት መጠን የሚያንሰው በ3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ ነው።
ፑቲን ታማኝ የሆኑት ባለሀብቶች ትርፍ እንዲያገኙ ሲፈቅዱ፤ የእሳቸውን መስመር ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆኑትን ግን በተከታታይ ቀጥተዋል።
ቅጣቱ ከደረሰባቸው አንዱ የነዳጅ ምርት ቱጃሩ ሚኻይል ኻዶርኮቭስኪ ናቸው። በአንድ ወቅት የሩሲያ ቁጥር አንድ ባለፀጋ የነበሩት ኻዶርኮቭስኪ፤ በ2001 የዴሞክራሲ ተሟጋች ድርጅት ካቋቋሙ በኋላ ለ10 ዓመታት በእስር ቤት አሳልፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ወረራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሩሲያ እጅግ ባለፀጎች ዝምታን መርጠዋል። በግልጽ ጦርነቱን የተቃወሙት ጥቂት ባለፀጎች ደግሞ አገራቸውን እና አብዛኛውን ሀብታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገድደዋል።
የሩሲያ ባለፀጎች ፑቲን ለሚያካሂዱት ጦርነት አስፈላጊ መሆናቸው ግልጽ ነው። የካቱት 2022 ወደ ክሬምሊን ከተጠሩት 37 የንግድ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ የምዕራባውያን ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ምዕራባውያን ይህንን ማዕቀብ ሲጥሉ ዓላማቸው ባለሀብቶቹን አደህይቶ በክሬምሊን ላይ እንዲነሱ ማድረግ ከነበረ ግን ዕቅዱ ከሽፏል ማለት ይቻላል። የሩሲያ ቢሊየነሮች ሀብት እየጨመረ እና የተቃውሞ ልሳናቸውም እየተዘጋ ነውና።
ሀብቱን ይዞ ወደ ምዕራቡ ዓለም ለመሸሽ የሚያስብ ቢሊዮነር ቢኖር እንኳ የተጣለው ማዕቀብ ይህንን ሀሳብ የማይቻል አድርጎታል።
የአውሮፓ ፖሊሲ ትንተና ማዕከል ባልደረባ የሆኑት አሌክሳንደር ኮሊያንድር "ምዕራባውያን የሩሲያ ቢሊየነሮች በዓላማቸው ዙሪያ እንዲሰለፉ ለማድረግ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል" ይላሉ።
"የትኛውም [ባለሀብት] ከመርከቧ ዘልሎ እንዲያመልጥ የሚያስችል ዕቅድ፣ ሃሳብም ሆነ ግልጽ የሆነ መንገድ አልነበረም። ንብረቶቻቸው ታገዱ፣ የባንክ ሂሳቦቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ ተደረገ፣ ንብረቶቻቸውም ተወረሱ። ይህ ሁሉ ፑቲን ቢሊየነሮችን፣ ንብረቶቻቸውን እና ገንዘባቸውን በማንቀሳቀስ ለሩሲያ የጦርነት ኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲውሉ ለማድረግ እንዲችሉ በሚገባ ረድቷል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዩክሬን ወረራን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የውጭ ኩባንያዎች ከሩሲያ መውጣታቸው ክፍተት ፈጥሯል። የሩሲያ መንግሥት ደጋፊዎቹ የሆኑ ባለሀብቶች እጅግ አትራፊ የሆኑት የውጭ ኩባንያዎች ንብረቶችን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲገዙ በመፍቀድ ክፍተቱን በፍጥነት ደፍኗል።
በካርኔጊ ሩሲያ ዩራሲያ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት አሌክሳንድራ ፕሮኮፔንኮ፤ ይህ ሁኔታ "ተደማጭነት ያላቸው እና ንቁ አዲስ ታማኝ ባለሀብቶች" እንዲፈጠሩ አድርጓል በማለት ይከራከራሉ።
"የእነዚህ ሰዎች የወደፊት ደኅንነት የተመሠረተው በሩሲያ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል በተፈጠረው ቀጣይነት ያለው ግጭት ላይ ነው" ይላሉ። የባለሀብቶቹ ትልቁ ስጋት ደግሞ የቀድሞዎቹ የንብረት ባለቤቶች መመለስ መሆኑን ያስረዳሉ።
የፎርብሱ ጃኮሞ ቶግኒኒ እንደሚናገረው፤ በ2024 ብቻ በዚህ መንገድ 11 አዳዲስ ቢሊየነሮች ሩሲያ ውስጥ ተፈጥረዋል።
ምንም እንኳ ጦርነቱ እና የምዕራባውያን ማዕቀብ ሩሲያ ላይ ቢበረታም፤ ፑቲን በአገሪቱ ቁልፍ አንቀሳቃሾች እና ተጽእኖ ፈጣሪዎች ላይ ያላቸውን ጠንካራ ቁጥጥር ማስቀጠል ችለዋል። የዚህ አንዱ ምክንያትም ውጤቱ ተቃራኒ የሆነው የምዕራባውያን የማዕቀብ እርምጃ ነው።















