የአውሮፓ ኅብረት የሩሲያን 185 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ማበደር ይችላል?

ፑቲን ከወታደራዊ መሪዎቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Alexander KAZAKOV/POOL/AFP

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ ጥሎት የነበረውን ጊዜያዊ ማዕቀብ ወደ ዘላቂ እገዳ ማሸጋገሩ የተገለጸው ባለፈው ሳምንት ነው።

185 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሩሲያ ሃብት ላይ ዘላቂ እገዳ ተጥሏል። አብዛኛው ሃብት የሚገኘው በቤልጄሙ ዩሮሴለር ባንክ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ይሄንን ሃብት ለዩክሬን ለማበደር ለሁለት ቀናት ውይይት እያደረጉ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት እገዳ የጣለበትን ሃብት ለዩክሬን እርዳታ ለማዋል ይፈልጋል። ሆኖም ግን ቤልጄም ገንዘቡን ጥቅም ላይ ማዋልን በተመለከተ በግልጽ ድጋፍ አላሳየችም።

የገንዘብ ክምችቷ እየተመናመነ ያለው ዩክሬን በቀጣይ ሁለት ዓመታት 119 ቢሊዮን ዶላር ትፈልጋለች። የአውሮፓ አገራት ሁለት ሦስተኛውን ለመሸፈን አቅደዋል።

አንድ የአውሮፓ ኅብረት አመራር "ስምምነት ላይ እንደርሳለን ብለን የተለጠጠ ተስፋ አንሰንቅም" ብለዋል።

ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረትን በምዝበራ ወንጅላለች። የሩሲያ ብሔራዊ ባንክ የቤልጄሙን ባንክ በሞስኮ ፍርድ ቤት እንደሚከስሰውም አስታውቋል።

በብራሰልስ እየተካሄደ ያለው የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ውይይት ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም "ከመቼውም በላይ ተቃርበናል" ብለዋል።

የዩክሬን ጦርነት በተጀመረ ማግሥት በአውሮፓ የሚገኝ የሩሲያ ሃብት ላይ ማዕቀብ ተጥሏል።

የሩሲያ ሃብት ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት መዋል እንዳለበት የአውሮፓ አገራት ገልጸዋል።

ብራሰልስ ይሄንን ሃብት "የማካካሻ ብድር" ብላ የጠራችው ሲሆን፤ የዩክሬንን ምጣኔ ሃብት ወደ 90 ቢሊዮን ዩሮ ለማሳደግም ታቅዷል።

ሩሲያ አሜሪካ መራሹ የሰላም ዕቅድ እምብዛም ተቀባይነት እንደማይኖረው ጠቁማለች።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስለ አውሮፓ ያላቸውን አቋም አይደብቁም።

አውሮፓ "የለየለት መላሸቅ" ውስጥ ገብታለች ብለዋል። የዩክሬን ደጋፊዎች ከሩሲያ ውድቀት ተጠቃሚ ለመሆን ቋምጠዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ዘለነስኪ እና የቤልጄም ጠቅላይ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Ukrinform/NurPhoto

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ "የሩሲያ ሃብት ያወደመችውን አገር መልሶ ለመገንባት መዋሉ ፍትሐዊ ነው" ብለዋል።

የፊንላንድ ባለሥልጣን "ዩክሬን ውጊያውን ለአንድ ዓመት እንድትቀጥል መደገፍ አለብን" ብለዋል።

የሰላም ድርድሮች ሲቀጥሉ ዩክሬን በድርድሩ ላይ "ውሳኔ ሰጭ" ለመሆን የሚያስችላት አቅም እንድታዳብር መርዳት እንደሚፈልጉ አክለዋል።

የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርዝ "ገንዘቡ ዩክሬን በቀጣይ ከሩሲያ ወረራ ራሷን እንድትከላከል ይረዳል" ሲሉ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊት ኧርሰላ ቮን ደር ሌይን ሩሲያ ለጦርነቱ የምታወጣው ወጪ ከፍ እንዲል ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እገዳ የተጣለበትን የሩሲያ ሃብት ለዩክሬን ከመስጠት ውጭ ያለው አማራጭ፤ ይሄንን ሃብት የአውሮፓ ኅብረት በዓለም አቀፍ ገበያ ተበድሮ ለዩክሬን መስጠት ነው። ይሄንን ዕቅድ ቤልጄም ትደግፈዋለች።

ነገሮች እንደታቀዱ ካልሄዱ ቤልጄም ከፍተኛ የገንዘብ እዳ ውስጥ ልትገባ ትችላለች። የዩሮሴለር ዋና ኃላፊ ቫለሪን ኡርበን "ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ሊቃወሰ ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ ብራሰልስን እና የአውሮፓ የምጣኔ ሃብት ኮሚሽነር ቫልዲስ ዶምበርኮቪስን ለመክሰስ ወስናለች። ሆኖም የአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት እንዳይከሰሱ "ሙሉ ከለላ ይሰጣቸዋል" ተብሏል።

ከዚህ ቀደም እገዳ ከተጣለበትን የሩሲያ ሃብት የተገኘውን "ወለድ" የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን አስረክቧል።

ዩክሬንን እየደገፉ መቀጠል እንደማያዋጣ የሚያምኑ የአውሮፓ አገራት ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ።

የአውሮፓ ኅብረት የሩሲያን ሃብት የመጠቀም ሕጋዊ መብት እንዳላቸው ያምናሉ። የቤልጄም ጠቅላይ ሚኒስትር ግን በዚህ አይስማሙም።

የቤልጄም መከላከያ ሚኒስትር ቲዮ ፍራንከን እንዳሉት በዩሮሴለር ባንክ ያለውን ሃብት ለዩክሬን ማበደር "ትልቅ ስህተት" ነው።

ሃንጋሪም ይሄንን ዕቅድ ነቅፋለች።

ሩሲያ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ስለሆነች የአውሮፓ ኅብረት ወለዱን ቢጠቀም ሕጋዊ ጥያቄ አያስነሳም።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ካቋረጡ በኋላ የአውሮፓ መሪዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ሀንጋሪ እና ስሎቫኪያም ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ አይፈልጉም።

ሩሲያ ቤልጄምን በአገሯ ፍርድ ቤት ብታቆምም ውሳኔው በአውሮፓ ኅብረት ዕውቅና የሚያገኝ አይሆንም።

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ዕቅዱን ለማጽደቅ ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማግኘት አለባቸው።

ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲቀጥል የኅብረቱ አባል አገራት በየስድስት ወሩ ድምጽ ሲሰጡ ቆይተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ስምምነት አንቀጽ 122 "ለኅብረቱ ስጋት የሆነ ምጣኔ ሃብት ላይ ቋሚ እገዳ መጣል ይቻላል" ይላል።

የስዊድን የገንዘብ ሚኒስትር ኤልዛቤት ስቬትሰን ሩሲያ ላይ የተወሰደው እርምጃ "ዩክሬንን ከመደገፍ በተጨማሪ ለዴሞክራሲ የሚከፈል ዋጋ ነው" ብለዋል።

ቤልጄም ዩክሬንን ብትደግፍም ምጣኔ ሃብቷን የሚጎዳ ውሳኔ ማጽደቅ አትሻም።

ከሩሲያ ጋር የሚዋሰኑ የአውሮፓ አገራት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ አፋጣኝ እርምጃ በኅብረቱ እንዲወሰድ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።

ፊንላንድ፣ ዘ ባልቲክስ እና ፖላንድ የሩሲያ ሃብት ላይ ዘላቂ እገዳ የመጣል ደጋፊ የሆኑትም ለዚህ ነው። ሩሲያ በበኩሏ ሃብቷ እንዳይነካ በጽኑ አስጠንቅቃለች።