የአውሮፓ ኅብረት 185 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሩሲያ ሃብት ላይ ዘላቂ እገዳ ጣለ

የፎቶው ባለመብት, Thierry Monasse/Getty Images
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ ላይ ጥሎት የነበረውን ጊዜያዊ ማዕቀብ ወደ ዘላቂ እገዳ ማሸጋገሩ ተገለጸ።
185 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሩሲያ ሃብት ላይ ዘላቂ እገዳ ተጥሏል። አብዛኛው ሃብት የሚገኘው በቤልጄሙ ዩሮሴለር ባንክ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት እገዳ የጣለበትን ሃብት ለዩክሬን እርዳታ ለማዋል በቀጣይ ሳምንት ስምምነት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የገንዘብ ክምችቷ እየተመናመነ ያለው ዩክሬን በቀጣይ ሁለት ዓመታት 119 ቢሊዮን ዶላር ትፈልጋለች።
የአውሮፓ አገራት ሁለት ሦስተኛውን ለመሸፈን አቅደዋል። ሩሲያ ግን የአውሮፓ ኅብረትን በምዝበራ ወንጅላለች።
የሩሲያ ብሔራዊ ባንክ የቤልጄሙን ባንክ በሞስኮ ፍርድ ቤት እንደሚከስሰው አስታውቋል።
የዩክሬን ጦርነት በተጀመረ ማግሥት በአውሮፓ የሚገኝ የሩሲያ ሃብት ላይ ማዕቀብ ተጥሏል።
የሩሲያ ሃብት ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት መዋል እንዳለበት የአውሮፓ አገራት ገልጸዋል። ብራሰልስ ይሄንን ሃብት "የማካካሻ ብድር" ብላ የጠራችው ሲሆን፤ የዩክሬንን ምጣኔ ሃብት ወደ 90 ቢሊዮን ዩሮ ለማሳደግም ታቅዷል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ "የሩሲያ ሃብት ያወደመችውን አገር መልሶ ለመገንባት መዋሉ ፍትሐዊ ነው" ብለዋል።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ "ገንዘቡ ዩክሬን በቀጣይ ከሩሲያ ወረራ ራሷን እንድትከላከል ይረዳል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ ብራሰልስን እና የአውሮፓ የምጣኔ ሃብት ኮሚሽነር ቫልዲስ ዶምበርኮቪስን ለመክሰስ ወስናለች። ሆኖም የአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት እንዳይከሰሱ "ሙሉ ከለላ ይሰጣቸዋል" ተብሏል።
ነገሮች እንደታቀዱ ካልሄዱ ቤልጄም ከፍተኛ የገንዘብ እዳ ውስጥ ልትገባ ትችላለች። የዩሮሴለር ዋና ኃላፊ ቫለሪን ኡርበን "ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ሊቃወሰ ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቤልጄም ጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ደ ዌቨር እንዳሉት የአውሮፓ ኅብረትን ዕቅድ የሚቀበሉት "ምክንያታዊ እና ስልታዊ" ከሆነ ብቻ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት ቤልጄም ልትቀበለው የምትችለውን ዕቅድ በቀጣይ ሳምንት ያቀርባል።
የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ተጥሎበት ከቆየውን የሩሲያ ሃብት ላይ እስካሁን ድረስ ምንም አልቀነሰም።
ሆኖም ግን ባለፈው ዓመት ከዚህ ሃብት የተገኘውን "ወለድ" ለዩክሬን አስረክቧል።
ሩሲያ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ስለሆነች የአውሮፓ ኅብረት ወለዱን ቢጠቀም ሕጋዊ ጥያቄ አያስነሳም።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ካቋረጡ በኋላ የአውሮፓ መሪዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ሀንጋሪ እና ስሎቫኪያም ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ አይፈልጉም።
ሩሲያ ቤልጄምን በአገሯ ፍርድ ቤት ብታቆምም ውሳኔው በአውሮፓ ኅብረት ዕውቅና የሚያገኝ አይሆንም።
በአውሮፓ የሚገኝ የሩሲያ ብሔራዊ ባንክ ሃብት ላይ የአውሮፓ ኅብረት ቋሚ እገዳ መጣል እንደሚችል የኅብረቱ አምባሳደሮች ተስማምተዋል።
ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲቀጥል የኅብረቱ አባል አገራት በየስድስት ወሩ ድምጽ ሲሰጡ ቆይተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ስምምነት አንቀጽ 122 "ለኅብረቱ ስጋት የሆነ ምጣኔ ሃብት ላይ ቋሚ እገዳ መጣል ይቻላል" ይላል።
የስዊድን የገንዘብ ሚኒስትር ኤልዛቤት ስቬትሰን ሩሲያ ላይ የተወሰደው እርምጃ "ዩክሬንን ከመደገፍ በተጨማሪ ለዴሞክራሲ የሚከፈል ዋጋ ነው" ብለዋል።
ቤልጄም ዩክሬንን ብትደግፍም ምጣኔ ሃብቷን የሚጎዳ ውሳኔ ማጽደቅ አትሻም።
የፋይናንስ ሕግ ባለሙያው ቨርሊ ኮልበርት "የቤልጄም ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ 565 ቢሊዮን ዩሮ ነው። የ185 ቢሊዮን ዶላር ክስ ቢከፈትባቸው ምን ሊገጥማች እንደሚችል መገመት ይቻላል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ከሩሲያ ጋር የሚዋሰኑ የአውሮፓ አገራት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ አፋጣኝ እርምጃ በኅብረቱ እንዲወሰድ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
ፊንላንድ፣ ዘ ባልቲክስ እና ፖላንድ የሩሲያ ሃብት ላይ ዘላቂ እገዳ የመጣል ደጋፊ የሆኑትም ለዚህ ነው።
ሩሲያ በበኩሏ ሃብቷ እንዳይነካ በጽኑ አስጠንቅቃለች። ሰላም ለማውረድ ዕቅድ እየነደፈች ያለችው አሜሪካም እገዳ የተጣለበት የሩሲያ ሃብት ለዩክሬን ድጋፍ እንዲውል የምትፈልግ አይመስልም።
በሌላ በኩል 100 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ እና ማዕቀብ የተጣለበት የሩሲያ ሃብት ለመልሶ ግንባት እንዲውል አሜሪካ ፈቅዳለች።















