ሩሲያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ኔቶን ልትወጋ ትችላለች ሲሉ የጥምረቱ ኃላፊ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የኔቶ አባል አገርን ልትወጋ ትችላለች ሲሉ የወታደራዊ ጥምረቱ ኃላፊ አዲስ ማስጠንቀቂያ ሰጡ።
ማርክ ሩቴ በጀርመን ባደረጉት ንግግር "ሩሲያ በኅብረተሰባችን ላይ የምታደርገውን ድብቅ ዘመቻ እያባባሰች ነው። አያቶቻችን ወይም ቅድመ አያቶቻችን ለታገሉት ዓይነት ጦርነት መዘጋጀት አለብን" ብለዋል።
በዚህም ምዕራባዊያን የስለላ ተቋማት ሩሲያን በተመለከተ ያወጡትን ተመሳሳይ መግለጫዎች አስተጋብተዋል። ሞስኮ ግን አስተባብላለች።
ሩቴ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየካቲት 2022 የተጀመረውን የሩሲያን ወረራ ለማስቆም በሚሞክሩበት ወቅት ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው ከአውሮፓ ጋር ጦርነት ለመግጠም ዕቅድ እንደሌላት ተናግረው፤ አውሮፓ ጦርነት ለመጀመር ከፈለገች ግን ዝግጁ ነን ብለው ነበር።
ሞስኮ እአአ በ2022 ተመሳሳይ ማረጋገጫ ብትሰጥም 200 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው ዩክሬን መውረራቸው ይታወሳል።
አሜሪካ በዩክሬን ሠላም ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት የአውሮፓ አገሮች እያደናቀፉ ነው ሲሉ ፑቲን ከሰዋል። ይህንን ያሉት ሩሲያን የሚደግፈውን የመጀመሪያውን የሠላም ረቂቅ የአውሮፓ አጋሮች ለመቀየር ያደረጉትን ሚና ተከትሎ ነው።
ፑቲን ቅን አልነበሩም ሲሉ የኔቶ ዋና ጸሐፊ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ተናግረዋል።
ዩክሬንን መደገፍ ለአውሮፓ ደኅንነት ዋስትና እንደሆነም አክለዋል።
"አስቡት ፑቲን ቢሳካለት ኖሮ፤ ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ሥር ሆና፣ ጦሩ ኔቶ ላይ በረዥም ድንበር ጫና በመፍጠር ጥቃት የመሰንዘር አደጋው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።"
የሩሲያ ኢኮኖሚ ከሶስት ዓመታት በላይ በጦርነት ላይ ቆይቷል። ፋብሪካዎቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የድሮን፣ የሚሳኤል እና የመድፍ ፍላጎት ለማሟላት እየሠሩ ነው።
ኪኤል የዓለም ኢኮኖሚ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ሩሲያ በየወሩ 150 ታንኮችን፣ 550 የእግረኛ ጦር ተሽከርካሪዎችን፣ 120 የላንሴት ድሮኖችን እና ከ50 በላይ የመድፍ ተተኳሾችን ታመርታለች።
እንግሊዝ እና አብዛኛዎቹ የምዕራባውያን አጋሮቿ በዚህ ደረጃ ላይ አይደሉም።
ተንታኞች እንደሚሉት የምዕራብ አውሮፓ ፋብሪካዎች የሩሲያን የጦር መሳሪያ ምርት ለመመጣጠን ዓመታት ይፈጅባቸዋል።
ፈረንሳይ እና ጀርመን ሁለቱም በቅርቡ የ18 ዓመት ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ወታደራዊ አገልግሎት የሚሰጡበትን አሠራር በድጋሚ ለማስጀመር ተንቀሳቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሳይበር ጥቃት፣ የተዛባ መረጃ ማሰራጨት እና በኔቶ አባል አገራት አየር ማረፊያዎች እና ወታደራዊ ሰፈሮች አቅራቢያ ድሮኖችን መመልከትን የሚያካትተው "ድብልቅ" የሚባለው ጦርነት እየጨመረ ይገኛል።
እነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች ቢሆኑም፣ በኔቶ አባል አገር ላይ በሚሰነዘር የሩሲያ ወታደራዊ ጥቃት ምክንያት ከሚከሰተው ቀውስ ጋር ሲነፃፀሩ ቀላል ናቸው።
ኔቶ 30 የአውሮፓ አገሮችን፣ ካናዳን እና የኅብረቱን በጣም ግዙፍ ወታደራዊ አባል የሆነችውን አሜሪካን በአባልነት አቅፏል።
በትራምፕ ጫና ምክንያት አባላቱ ወታደራዊ ወጪያቸውን ለመጨመር ቃል ገብተዋል።
"የኔቶ መከላከያዎች ለጊዜው ሊቋቋሙት ይችላሉ" ሲሉ ሩቴ በበርሊን አስጠንቅቀዋል። ነገር ግን ግጭቱ ከአውሮፓ "ጎረቤት" ነበር ከማለት ባለፈ "በጣም ብዙዎች ቸልተኞች ናቸው፣ አጣዳፊነቱ አይሰማቸውም፣ ጊዜም ከእኛ ጎን እንደሆነ ያምናሉ" ሲሉ ገልጸዋል።
"አባላቱ የመከላከያ ወጪዎች እና ምርትን በፍጥነት መጨመር አለባቸው። የጦራችን ደኅንነታችንን ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን በሙሉ ማግኘት አለበት" ሲሉ አዛዡ ተናግረዋል።















