ሩሲያ የምዕራባውያንን ማዕቀብ ለማለፍ እና ለስለላ የምትጠቀምባቸው ስውር ነዳጅ ጫኝ መርከቦች

ባሕር ላይ በማጉያ መነጽር ክትትል የሚያደርግ ሰው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የፕሬዝዳንት ቭላርሚር ፑቲን ቤተ መንግሥት 'ክሬምሊን'፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱን ሁለት ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ጥቁር መዝገብ ውስጥ በማስገባት የጣሉት ማዕቀብ ሩሲያን "እንደማይጎዳት" ይገልጻል።

ለዚህም ምክንያቱ የሩሲያን ነዳጅ የሚያንቀሳቅሱት በድብቅ የሚጓዙ የአገሪቱ መርከቦች በመሆናቸው ነው።

'ጎስት' እና 'ዞምቢ' ጫኝ መርከቦች በዓለም ዙሪያ እየተጓዙ ነዳጅ በቅናሽ መግዛት ለሚፈልጉ በሚሊዮን ዶላሮች ዋጋ ያለው ነዳጅ ዘይት ያከፋፍላሉ።

የኢራን አያቶላዎች፣ የቬንዙዌላ ጄነራሎች እና አጋጣሚውን የሚጠቀሙ ምዕራባውያን የንግድ ሰዎች የመርከቦቹ ደንበኞች ናቸው። እነዚህ አካላት መውጫ አጥተው አንዳንድ ጊዜ ባሕር ላይ ለወራት ወይም ለዓመታት ከሚያሳልፉ የመርከብ ሠራተኞች ደኅንነት እንዲሁም አካባቢ ላይ ከሚደርስ ጉዳት ይልቅ ትርፍን ያስቀድማሉ።

ሩሲያ በ2022 ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ በድብቅ የሚደረግ መርከብ ጉዞ ጨምሯል። የዚህ እንቅስቃሴ ዋነኛ ተጠቃሚ የፕሬዝዳንት ፑቲን መንግሥት ነው።

ትራምፕ እንደሚናገሩት ከሆነ የሩሲያ መንግሥት የመርከብ ጉዞውን የሚጠቀመው ነዳጅ አጓጉዞ በሚያገኘው ገንዘብ "የጦርነት ማሽኑን" ለመደገፍ ብቻ አይደለም።

በአውሮፓ በሚገኙ የኔቶ አባል አገራት እንዲሁም እነዚህ አገራት የሚጠቀሙባቸውን ከባሕር ስር ያሉ ኬብሎች እና መተላለፊያ መስመሮችን የመሰለል እንዲሁም የማስተጓጎል "ጥምር" ዘመቻ ለማከናወን ጭምር እንጂ።

በሲንጋፖር ባሕር ላይ ቆሙ መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በድብቅ የሚገወዙ መርከቦች የምዕራባውያንን ማዕቀቦች በማለፍ በባሕር የሚተላለፍን 80 በመቶ የሩሲያ ነዳጅ እንደሚያጓጉዙ ተንታኞች ይገምታሉ

ሩሲያ ከአሜሪካ እና ከሳውዲ አረቢያ ቀጥሎ ሦስተኛዋ የዓለም ነዳጅ አምራች አገር ነች። የአሜሪካ የኤነርጂ መረጃ አስተዳደር መሥሪያ ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው በ2024 አስር በመቶ ያህሉ የዓለም ነዳጅ የተመረተው በሩሲያ ነው።

የዩክሬኑ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ሁሉም በሚባል ደረጃ በባሕር የሚጓጓዝ የውጭ ምርት የሚጫነው በምዕራባውያን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ነው። አብዛኞቹም የግሪክ መርከቦች ነበሩ። የንግድ እንቅስቃሴው መቀመጫውን ስዊትዘርላድ ሲያደርግ፤ የኢንሹራንስ ዋስትናውን ያገኘው ደግሞ ለንደን ውስጥ ነበር።

አሁን ግን የሩሲያን ነዳጅ ከሚያጓጉዙ አምስት መርከቦች ውስጥ አራቱ ከሚታወቅ የኢንሹራንስ ተቋም ዋስትና ያልተገባላቸው እንደሆኑ ተንታኞች ይገልጻሉ። ይህም 80 በመቶ የሚሆነውን የሩሲያ ነዳጅ የሚያጓጉዙት መርከቦች በምዕራባውያን አገራት የተጣለውን ማዕቀበ ጥሰው እንደሚንቀሳቀሱ ያመለክታል።

በ 'ኪዬቭ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ኢንስቲትዩት' ከፍተኛ ኢኮኖሚስት የሆኑት ቤንጃሚን ሂልገንስቶክ እንደሚናገሩት፤ "ሩሲያ ማዕቀቦችን ማለፍ የሚያስችሏትን በድብቅ የሚጓዙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ገንብታለች።"

"ነገር ግን [መርከቦቹ] ያረጁ፣ በአግባቡ ያልተጠገኑ እና ምናልባትን ነዳጅ እንዳያፈስሱ በቂ ዋስትና ያልተገባላቸው ናቸው" ይላሉ።

አንድ ሦስተኛ የሚሆነው በባሕር ላይ የሚጓዝ የሩሲያ ነዳጅ የሚነሳው ከባልቲክ እና ከጥቁር ባሕር ወደቦች መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ በዚህም ምክንያት መርከቦቹ በአውሮፓ አገራት ባሕር ላይ በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜ እንደሚመላለሱ ያስረዳሉ።

ወደብ ላይ የቆመ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አብዛኛው የኢራን ነዳጅ የሚጓዘው በምስሉ ላይ እንደሚታየው የቻይና ሻንዶንግ ግዛት ባሉ ወደቦች ነው

የኤስ ኤንድ ፒ መረጃ እንደሚያመለክተው ባሕር ላይ ከሚታዩ አምስት መርከቦች ውስጥ አንዱ በድብቅ የሚጓዝ ነው። እነዚህ መርከቦች ያረጁ እና የማይታወቅ ባንዲራ ሰቅለው ማዕቀብ የሚጣልባቸው አገራትን ነዳጅ እንደሚያዘዋውሩም መረጃው ይገልጻል።

ከእነዚህ መርከቦች ውስጥ የሩሲያን ነዳጅ እና የነዳጅ ምርቶች የሚጭኑት 50 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። 20 በመቶ ያህሉ የኢራን፣ 10 በመቶው ደግሞ የቬንዙዌላን ምርቶች ያጓጉዛሉ። ቀሪዎቹ 20 በመቶ መርከቦች ከአንድ በላይ አገራትን ነዳጅ የሚያጓጉዙ ናቸው።

ሩሲያ፣ ኢራን እና ቬንዙዌላን የሚያገለግሉት ትላልቆቹ መርከቦች ዋነኛ የጉዞ መዳረሻቸው ሕንድ እና ቻይና ነው።

ከዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብን በመያዝ ቀዳሚ የሆኑት ሁለቱ አገራት፤ በባሕር የሚጓዙ ነዳጅ እና የነዳጅ ምርቶችን በማስገባትም ስማቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

በአነስተኛ መጠን የሩሲያን ነዳጅ ከሚገዙ አገራት ውስጥ ደግሞ ቱርክ፣ ሲንጋፖር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይገኙበታል።

በጉዞ ላይ ያለ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, "ዞምቢ" ተብሎ በሚጠራው ዘዴ የሚጓዙ መርከቦች የሚጠቀሙት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ለሚደረጉ መርከቦች የሚሰጥን የመለያ ቁጥር ነው

በድብቅ የሚጓዙ መርከቦችን ዳና ለመሰወር እነዚህ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፦

  • የጭነቱን መነሻ ለመደበቅ ሲባል ከአንድ መርከብ ወደ ሌላ መርከብ ነዳጅ ማዘዋወር። ይህ ተግባር የሚከወነው የወደብ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ክትትል ደካማ በሆነባቸው የዓለም አቀፍ ውሃዎች ላይ ሲሆን አንዳንዴም በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ ይፈጸመዋል።
  • መርከቦቹ ያሉበትን ቦታ፣ የጉዞ ፍጥነት፣ ስም፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ የመርከብ ዓይነት መረጃዎችን የሚያስተላልፈውን አውቶማቲክ የመለያ ሥርዓትን ማጥፋት ወይም እንዲሳሳት ማድረግ። መርከቦቹ አንዳንድ ጊዜ የሚያሳዩት ሐሰተኛ የቦታ መረጃ ጉዟቸውን እያደረጉ ያሉት "መሬት ላይ" እንደሆነ ያስመስላል።
  • "ጎስት ሺፕ" መሆን፤ ይህም ማለት የመርከቡን የባለቤትነት መረጃን መደበቅ፣ የተመዘገበበትን አገር ሰንደቅ ዓላማ መቀየር ወይም ጨራሹኑ ያለ ሰንደቅ ዓላማ መጓዝን ያካትታል። በአንድ ወር ውስጥ በርካታ ጊዜ የመርከቡን ስም መቀየርም የዚህ አካል ነው።
  • "ዞምቢ ሺፕ" መሆን፤ ይሄኛው ዘዴ ደግሞ ዓለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት ለሚወገዱ መርከቦች የሰጣቸውን ልዩ የምዝገባ ቁጥሮችን መጠቀም ነው። የሞተን ሰው ማንነት ተጠቅሞ እንደመንቀሳቀስ ያለ ተግባር ነው።
በጉዞ ላይ ያለ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሁኑ ሰዓት በድብቅ የሚጓዙ 1,300 መርከቦች እንዳሉ ይገመታል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ2025 የመጀመሪያዎች ስምንት ወራት ወስጥ ሐሰተኛ ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለው የተጓዙ መርከቦች ቁጥር በ65 በመቶ መጨመሩን 'ዊንድዋርድ' የተሰኘው የማሪታይም ትንተና ኩባንያ መረጃ ያሳያል። በኩባንያው ግምት መሠረት በድብቅ የሚጓዙ መርከቦች ብዛት 1,300 ደርሷል።

የመርከቦች የሰንደቅ ዓላማ ምዝገባ አገልግሎትም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ብዙዎቹ ለማጭበርበር የሚውሉ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ምንም እንኳ ሕጋዊ ቢሆኑም ሰንደቅ ዓላማውን የሚሰጡት አገራት ለሥራው አዲስ ናቸው። ወይም ሰንደቅ ዓላማው እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ የመቆጣጠር ፍላጎት ወይም አቅም የላቸውም።

ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በአፍሪካዊቷ አገር ቤኒን ሰንደቅ ዓላማ ስር የሚጓዝ አንድ መርከብ ምሥጢራዊ የድሮን በረራ በማካሄድ ተጠርጥሮ ነበር። በዚህ የድሮን በረራ ምክንያት የዴንማርክ አየር ማረፊያዎች ተዘግተው ነበር።

መርከቡ በፈረንሳይ የባሕር ዳርቻ በተያዘበት ወቅት ሠራተኞቹ "መተባበር ፈቃደኛ እንዳልነበሩ" እንዲሁም "መርከቡ በየትኛው አገር ስር እንደሚንቀሳቀስ ሊገልጹ እንዳልቻሉ" ሲል ዐቃቤ ሕግ አስታቋል።

"ቦራኬይ" ተብሎ የሚጠራው ይህ መርከብ ከዚህ ቀደም ስያሜውን "ፑሽፓ"፣ "ኦዲሲየስ"፣ "ቫሩና" እና "ኪዋላ" እያለ ሲቀያየር እንደነበር ተደርሶበታል። የሰባት አገራትን ሰንደቅ ዓላማ ሲጠቀም እንደነበርም ተገልጿል።

መርከቡ በፈረንሳይ የባሕር ኃይል በተያዘበት ወቅት ከሩሲያ የጫነውን 750 ሺህ በርሜል ድፍርፍ ነዳጅ ወደ ሕንድ እያጓጓዘ እንደነበር ታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሩሲያ ድሮኖች የኔቶ አጋር አገራት ወደ ሆኑት ወደ ስዊዲን፣ ኖርዌይ እና ጀርመን ላይ እንደገቡ ተጠርጥሯል።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በቤልጂየም በሚገኘው የብራስልስ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ እና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ድሮኖች መታየታቸውን ተከትሎ የበረራ አገልግሎቱ በጊዜያዊነት ተዘግቶ ነበር።

ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን አጋሮች ላይ "ቅይጥ የጦርነት እንቅስቃሴ" አድርጋለች በሚል የቀረበባትን ክስ ውድቅ አድርጋለች።

በቦራኬይ መርከብ ላይ የተደረገውን ምርመራ ተከትሎ የኔቶ አገራት "ባልቲክ ሴንትሪ" የተሰኘ የባሕር ተቆጣጣሪ ተልዕኮ አስጀምረዋል።

ብሪታኒያ፣ ዴንማርክ፣ ስዊዲን እና ፖላንድ በዴንማርክ ወሽመጥ፣ በፊንላንድ ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም በስዊዲን እና ዴንማርክ ወሽመጥ መካከል በሚያልፉ መርከቦች ላይ የኢንሹራንስ ሰነድ ምርመራ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።

ኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ አይስላንድ፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዋኒያ፣ ኔዘርላንድስ እና ኖርዌይ ደግሞ በድብቅ የሚቀዝፉ የሩሲያ መርከቦችን ጉዞ "ለማስተጓጎል እና ለመገደብ" ተስማምተዋል።

ጥቅምት ላይ የተያዘው መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጥቅምት ላይ የተያዘው ይህ መርከብ ቢያንስ አራት ጊዜ ስያሜውን እንደቀየረ እና የሰባት አገራትን ባንዲራዎችን ተጠቅሞ ሲጓዝ እንደነበር ተደርሶበታል

አገራቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በባልቲክ የሚገኙ ኬብሎች በመቆረጣቸው እና ከባሕር ስር በተዘረጉ መሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ነው።

ነገር ግን በድብቅ የሚጓዙ መርከቦች ሊጠለፉ የሚችሉት ወደብ ላይ ወይም በአገራቱ የውሃ ድንበር ውስጥ ሲሆኑ ብቻ ነው። በዓለም አቀፍ የውሃ አካላት እነዚህን መርከቦች መያዝ እጅጉን አስቸጋሪ ነው።

በተለይም ደግሞ በባሕር ላይ በነጻነት የመዘዋወርን መብት በማቀንቀን የሚታወቁት ምዕራባውያን ይህን አቋማቸውን መጣስ ይሆንባቸዋል።

መርከቦች ያለ ጣልቃ ገብነት እንዲጓዙ በሚደነግገው ዓለም አቀፍ መርኅ መሠረት፤ አገራት መርከቦችን መጥለፍ የሚችሉት የደኅንነት ስጋት በደቀኑባቸው ጊዜ ብቻ ነው።

የሩሲያ ፖለቲከኞች በበኩላቸው የአገሪቱን ነዳጅ በጫኑ መርከቦች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጠበኛ ድርጊት በሩሲያ ላይ ተፈጸመ ጥቃት ሆኖ እንዲቆጠር ጠይቀዋል።

ግንቦት ላይ ኢስቶኒያ ሰንደቅ ዓላማ ሳትሰቅል በኢስቶኒያ እና በፊንላንድ መካከል እየተጓዘ የነበረች ነዳጅ ጫኝ መርከብን በቁጥጥር ስር ለመዋል በሞከረች ጊዜ የሩሲያ ተዋጊ ጄቶች መርከቡን እንዲከብቡ ተልከው ነበረ።

የዓለም ዋነኛ የመርከብ ጭነት ድርጅቶች የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለ15 ዓመታት የሚጠቀሙባቸው ሲሆን፣ ከ25 ዓመታት በኋላ ብረታቸው ተቆራርጦ ለሌላ አገልግሎት ይውላል። በስውር አገልግሎት የሚሰጡት ግን ፈላጊ የላቸውም። ስለዚህም አስከ 50 ዓመታት ስለሚያገለግሉ ባሕር ላይ ነዳጅ በማፍሰስ ለአካባቢ ደኅንነት አደጋ ይሆናሉ።

ነገር ግን አንዳንድ በሩሲያ የነዳጅ ድርጅቶች ገንዘብ የሚደገፉ የዱባይ ኩባንያዎች አሮጌዎቹን መርከቦች በመግዛት በአዲስ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ሊውል የሚገባን መዋዕለ ነዋይ አደናቅፈዋል ሲል ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል።

በስም በማይጠቀሱ እና አዲስ በተቋቋሙ ኩባንያዎች የሚካሄደው የመርከቦች ፈጣን የሽያጭ እና የግዢ ሂደት ተጠያቂነትን አዳጋች አድርጎታል። የነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ ተገቢው ጥገና ስለማይደረግላቸው ለብልሽት እና ለነዳጅ መፍሰስ የተጋለጡ ናቸው።

በተጨማሪም የግንኙነት እና የአቅጣጫ መጠቋሚያቸው የተበላሸ ወይም እንዲጠፋ ስለሚደረግ በጠባብ መተላለፊያዎች ላይ ከሌሎች መርከቦች ጋር የመጋጨት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

ሆኖም ግን ይህ ስውር ንግድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኝ ነው። 15 ዓመት ያገለገለ አንድ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ዋጋው 40 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፣ ከጥቁር ባሕር የሩሲያን ነዳጅ ጭኖ በአንድ ወር ጉዞ ሕንድ ሲያደርስ ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለባለቤቱ እንደሚያስገባ የመርከብ ሽያጭ እና ጭነት ድርጅቶች ይናገራሉ።

ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ላይ የተጣለው የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ ቢነሳ እንኳን እነዚህ ካለተጠያቂነት እና የኢንሹራንስ ሽፋን አትራፊ ንግድ ላይ የተሰማሩት ስውር መርከቦች ሥራቸውን ያቆማሉ ተብሎ አይታሰብም።