ከሶቪየት እስከ ሩሲያ፡ የምዕራባውያን የነዳጅ ማዕቀብ የፑቲንን አቋም ያስለውጣል?

አሜሪካ በሁለት የሩሲያ ነዳጅ አምራች ድርጅቶች ላይ አዲስ ማዕቀብ ጥላለች።
በሁለቱ ግዙፍ ነዳጅ አምራቾች ሮስኔፍት እና ሉክኦይል ላይ ማዕቀብ የተጣለው ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት እንድትደርስ ጫና ለማሳደር ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር ከተወያዩ በኋላ "ከፑቲን ጋር ጥሩ ንግግሮችን ባደርግም ውጤት አያመጡም" ብለዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ማዕቀቡ "አይጎዳንም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ታሪክን ወደኋላ መልስ ብለን ስንመለከት ነዳጅ እንዴት ጦርነትን ለማስቆም እንደዋለ ማየት ይቻላል።
ከአገሩ የተሰደደው ፖላንዳዊ ጋዜጠኛ አዳም ሚችሚንክ "ኮምኒስቶች ምክንያታዊ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ታሪክ ምስክር ነው" ይላል።
ሶቪየት ኅብረት ላይ ጫና ለማሳደር የነዳጅ ማዕቀብ አንዱ መንገድ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ የነዳጅ ዋጋ ይዋዥቅ ነበር። የድኅረ ጦርነት የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ በዓለም የነዳጅ ገበያ ተስተውሏል።
ከ1973-74 እና ከ1978-80 የነዳጅ ዋጋ መጨመር በአሜሪካ እና ምሥራቅ አውሮፓ የዋጋ ንረትን አባብሷል።
የምጣኔ ሃብት መቀዛቀዝ፣ ሥራ አጥነትና የዕዳ ክምችትም ተከስቷል።
ሶቪየት ኅብረት በውጭ ንግድ ምጣኔ ሃብት ማረጋጋት ችላ ነበር። የኢንዱስትሪ መስፋፋትና የጦር መሣሪያ ምርትም ጨምሯል።
ሶቪየት ኅብረት በአፍሪካ እና እስያ በጦር መሣሪያ ንግድ የምታሳድረው ተጽዕኖም ከፍ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Keystone-France/Gamma-Keystone via Getty Images
ሰላም እና ጦርነት
እአአ ጥቅምት 6/1973 በግብፅ እና ሶሪያ የሚመራ የአረብ አገራት ጥምረት እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸመ።
'ዮም ኪፑር' የተባለው ጦርነት መነሻ ነው።
አሜሪካ እስራኤልን ስትደግፍ ሶቪየት ኅብረት ከአረብ አገራትን ጎን ቆማለች።
የአረብ አገራት ወደ አሜሪካ የሚላክ ነዳጅን ስለቀነሱ የነዳጅ ዋጋ ናረ።
በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ ያሳተሙት ዳንኤል የርጊን "በ1973 የተጣለው የነዳጅ ማዕቀብ ዓለም አቀፍ ገበያውን አናግቷል። የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጧል" ይላሉ።
ግብፅ እና እስራኤል የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ በ1979 ኢራን ወደ ነዳጅ ውዝግቡ ገባች።

የፎቶው ባለመብት, GPO / Getty Images
ባለ ድል እና ተሸናፊ
አሜሪካ እና ምዕራብ አውሮፓ የምጣኔ ሃብት ውድቀት ሲገጥማቸው ሶቪየት ኅብረት አንጻራዊ መረጋጋት ውስጥ ነበረች።
ከባሕረ ሰላጤው አገራት ውጪ ከፍተኛው የነዳጅ ክምችት የነበረው በሰርቢያ ነበር።
በ1980 ሶቪየት ኅብረት ከዓለም ቀዳሚዋ ነዳጅ ላኪ ነበረች።
የምሥራቅ አውሮፓ አጋር አገራት ከኩባ እና ቬትናም ጋር በመሆን የሶቪየትን የነዳጅ ዋጋ አነቃቁ።
ለምዕራባውያን አገራት ነዳጅ በመላክ የውጭ ምንዛሬም ይገኝ ነበር።
ሶቪየት ወደ ሶሻሊስት ምጣኔ ሃብቷ ከፍተኛ ገንዘብ ታስገባ ጀመር። ከኢንዱስትሪ ምርት በተጨማሪ ነዳጅም ዋነኛ የውጭ ንግድ ዘዋሪ ሆነ።
በነዳጅ ዘርፍ ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ በሌሎች ዘርፎች ውስንነት መፍጠሩ ግን አልቀረም።
ከነዳጅ ውጭ ሌላው ገንዘብ በሰፊው የሚመደበው ለመከላከያው ዘርፍ ነበር።
የያኔው የጀርመን መራሔ መንግሥት "ሶቪየት ኅብረት ማዕድን ያላት ቡርኪና ፋሶን መስላለች" ብለው ወርፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጊዜ እና ገንዘብ
ሶቪየት በ1979 አፍጋኒስታንን ከወረረች በኋላ ምዕራባውያን አገራት ወደ ሶቪየት የሚላኩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ማዕቀብ ጣሉ።
የነዳጅ ምርት ላይ ጫና ያሳደረ ውሳኔ ነበር።
በ1980ዎቹ መባቻ የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ ሶቪየትን ይደግፍ የነበረው የነዳጅ ሽያጭ ገቢ ተቀዛቀዘ።
በሶቪየት የተቀጣጠለው ተቃውሞ በፖላንድ ወታደራዊ አገዛዝ እንዲደነገግ ምክንያት ሆኗል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን የአውሮፓ ታሪክን በተመለከተ መጽሐፍ የጻፉት ቶኒ ጁድ እንደሚሉት ሶቪየት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጊዜም መበደር ነበረባት።
ከ1980 እስከ 1986 የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ35 ዶላር ወደ ከ10 አስከ 15 ዶላር ወረደ።
ምዕራባውያን ኃይል መቆጠብ ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ። ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፊታቸውን አዞሩ።

የፎቶው ባለመብት, Dirck Halstead / Getty Images
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንድሪ ያርሚክ እንደሚሉት፤ የነዳጅን ዋጋ በመቀነስ የሞስኮን የውጭ ንግድ ለማዳከም ተሞክሯል።
"በ198 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን እና የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ፋዑድ የነዳጅን ዋጋ ለመቀነስ ተስማሙ። ወደ 10 ዶላር መቀነሱ ሶቪየት በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር እንድታጣ አድርጓል" ይላሉ።
የነዳጅ ዋጋ በበርሜል እስከ 12 ዶላር ደርሶ ነበር። ሶቪየት በወታደራዊ ኃይሏ ላይ የምታፈሰውን ገንዘብ እንድትቀንስ አድርጓል። ምጣኔ ሃብቷንም አሽመድምዷል።
ከዚያም በ1991 ሶቪየት ኅብረት እንዳልነበር ሆነች። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንድሪ ያርሚክ "የዓለም ትልቁ መሣሪያ እንኳን አላዳናትም" ይላሉ።
ያኔ የተፈጠረውን ነገር የሬጋን አስተዳደር በይፋ ባያምንም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና የታሪክ አጥኚዎች እስከ ዛሬ ይከራከሩበታል።
አሜሪካ የዓለም የነዳጅ ገበያን በርካሽ የነዳጅ አቅርቦት አጥለቅልቃለች?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዲሚትሪ ካርስኮቭ የሚባለው ነገር "እውነት አይደለንም" ይላሉ።
ሚኪል ጎርቫቾቭ የሶቪየት ኅብረት መሪ ሲሆኑ ከነዳጅ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ አስተዳደራቸውን እንደሚያጠናክር አምነው ነበር።
ሆኖም ዓለም አቀፍ ገበያው ተቀዛቅዞ ነበር።
አሁን ላይ የነዳጅ ሽያጭ ከሩሲያ አጠቃላይ ገቢ 60 በመቶ ይሸፍናል። የፌደራል መንግሥቱ 40 በመቶ ገቢም ከነዳጅ ሽያጭ ይገኛል።
ትራምፕ እና ነዳጅ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የነዳጅ ሽያጭ ላይ ያላቸው ጠንካራ አቋም ይታወቃል።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ያደረጉት ንግግር በአሜሪካ ውስጥ ነዳጅ ቁፋሮን እንደማያቆሙ በግልጽ ያሳያል።
ዩክሬን የሩሲያ የኃይል አቅርቦት ላይ ጥቃት ትሰነዝራለች። ሩሲያም በዩክሬን ኃይል አቅራቢ ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረስ ቀጥላለች።
ጦርነቱን ማስቆም ያስችል እንደሆነ ግን እርግጠኛ መሆን ይከብዳል።
በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም በሁለቱ ግዙፍ ነዳጅ አምራቾች ሮስኔፍት እና ሉክኦይል ላይ ማዕቀብ የተጣለው ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት እንድትደርስ ጫና ለማሳደር ነው።
ሁለቱ የሩሲያ ነዳጅ አምራቾች በየቀኑ 3.1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጭ አገራት ይልካሉ።
ሮስኔፍት ከሩሲያ የነዳጅ አቅርቦት ግማሹን ይሸፍናል። ከዓለም አቀፍ ገበያው ደግሞ 6 በመቶ ድርሻ አለው።
ቻይና፣ ሕንድ እና ቱርክ ዋነኛ የሩሲያ ነዳጅ ተጠቃሚዎች ናቸው። የአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የሚገኘውም ከነዳጅ ሽያጭ ነው።
ከ20 በላይ አገራት ዩክሬንን በመደገፍ "የሩሲያን ነዳጅ እና ጋዝ ከዓለም አቀፍ ገበያ ለማስወጣት" ቃል ገብተዋል።
አገራቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጫና በማሳደር ከዩክሬን ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለዩክሬን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ያለፈው ሐሙስ መግለጻቸው አይዘነጋም።
የኅብረቱ አባል አገራት 122 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የሩሲያ ንብረት ላይ ማዕቀብ ይጥላሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ከስምምነት አልደረሱም።















