ለዩክሬን ጦርነት ኬንያውያንን በሕገወጥ መንገድ ሲመለምል ነበር የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አታይ ሪቨር በሚባል አካባቢ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ 22 ኬንያውያን "ወደ ሩሲያ ለመሄድ እየተጠባበቁ" ሳለ ተይዘዋል

የፎቶው ባለመብት, Directorate of Criminal Investigations-Kenya

የምስሉ መግለጫ, አታይ ሪቨር በሚባል አካባቢ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ 22 ኬንያውያን "ወደ ሩሲያ ለመሄድ እየተጠባበቁ" ሳለ ተይዘዋል

የኬንያ ፖሊስ በሩሲያ ሥራ ትቀጠራላችሁ በሚል ተታልለው ወደ ዩክሬን ለውጊያ ሊላኩ ነበር ያላቸውን 20 ግለሰቦች ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ማስጣሉን ገለፀ።

ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ ወጣ ብሎ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ በተደረገ ክትትል እና ፍተሻ ግለሰቦቹን ለመመልመል የዋሉ ቁሳቁሶች፣ የጉዞ ሰነዶች እና የሥራ ቅጥር ደብዳቤዎች ተገኝተዋል።

ግለሰቦቹን በመመልመል በመስከረም እና ጥቅምት ወር ወደ ሩሲያ ለመላክ ሲያስተባብር ነበር የተባለ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ፖሊስ ምርመራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ ለ10 ቀን በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተወስኗል።

በኬንያ በርካቶች በሩሲያ ሥራ ትቀጠራላችሁ በሚል ማታለያ እየተወሰዱ ነው የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ።

በቅርቡ በዩክሬን የተያዘው ወጣት አትሌት የሩሲያን ጦር እንዲቀላቀል ለማድረግ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል።

ባለሥልጣናት ረቡዕ ዕለት ያካሄዱት ዘመቻ፣ የተለያዩ የደኅንነት እና የፀጥታ ተቋማት በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ኬንያዊያን ሥራ ፈላጊዎችን ከአገር እንዲወጡ የሚያደርግ የወንጀለኞች መረብን ዒላማ በማድረግ በትብብር ያካሄዱት ዘመቻ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም አታይ ሪቨር በሚባል አካባቢ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ 22 ኬንያውያን "ወደ ሩሲያ ለመሄድ እየተጠባበቁ" ሳለ መያዛቸው ተገልጿል።

ፖሊስ "ምስጢራዊ የሰዎች ዝውውር ድርጅት" ኬንያውያንን ወደ ሞስኮ ሥራ አስቀጥራችኋለሁ በማለት የሩሲያ ጦር በዩክሬን ለሚያካሄደው ጦርነት እየላከ ነው ብሏል።

መርማሪዎች ሥራ ትቀጠራላችሁ በሚል የተጭበረበሩት ኬንያውያን ስሙ ላልተገለፀ የውጭ ቀጣሪ ኤጀንሲ የሥራ ውል መፈረማቸውን ተናግረዋል።

በውላቸው መሰረት ለቪዛ፣ ለጉዞ፣ ለመኖሪያ እና ሌሎች የሎጀስቲክ ወጪዎች 18,000 ዶላር ለመክፈል ተስማምተዋል።

የተወሰኑት ግለሰቦች አስቀድመው 1,500 ዶላር መክፈላቸውን ተናግረዋል።

ፖሊስ እነዚህ ሥራ ፈላጊዎች አንድ ጊዜ ተመለምለው ከአገር ከወጡ በኋላ ተጎድተው፣ የሥነ ልቡና ጉዳት አጋጥሟቸው ወይንም ሕይወታቸው አልፎ ሊመለሱ ይችላሉ ብሏል።

ሁለት ኬንያውያን በቅርቡ ከሩሲያ የተመለሱ ሲሆን አንዱ በከተማዋ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተከታተለ ነው ተብሏል።

በቅርቡ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን በሕገወጥ መንገድ ወደ ሩሲያ ተወስደው በዩክሬን የጦር እስረኛ የሆኑ ኬንያውያንን ጉዳይ መንግሥት እየተከታተለ ነው ብለው ነበር።

የዩክሬን ቃል አቀባይ ስለምርኮኞች አያያዝ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ የሶማሊያ፣ ሴራ ሊዮን፣ ቶጎ፣ ኩባ፣ ሲሪ ላንካ እና የሌሎች አገራት ዜጎች በዩክሬን ፔትሮ ያቴሴንኮ በሚባል የጦር እስረኞች ካምፕ እንደሚገኙ ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ስለሌሎች የጦር እስረኞች ሲናገሩ "በርካታ የአፍሪካ አገራት እነዚህን ዜጎቻቸውን ለመመለስ የሚያሳዩት ፍላጎት ደካማ ነው እንዲሁም ለመመለስ አይፈልጉም" ብለው ነበር።