ቻይናውያን በደቡብ አፍሪካ ሰው በማገት እና አስገድዶ በማሠራት የ20 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

በሕገወት ሰው ዝውውር እና በጉልበት ስራ ላይ ማሰማራት የተፈረደባቸው ቻይናውያን

የፎቶው ባለመብት, Buthanani Thobela/Department of labour

የምስሉ መግለጫ, በሕገወት ሰው ዝውውር እና በጉልበት ስራ ላይ ማሰማራት የተፈረደባቸው ቻይናውያን

ማላዊያንን ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገ ወጥ መንገድ በማስገባት በጉልበት ሥራ ላይ ያሰማሩ ሰባት ቻይናውያን እያንዳንዳቸው በ20 ዓመት እስር ተቀጡ።

አራቱ ወንዶች እና ሦስት ሴቶች ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ላይ በደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና አፈና ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ቻይናውያኑ የቅጣት ውሳኔያቸው የተሰማው ፖሊስ ከስድስት ዓመታት በፊት በጆሃንስበርግ በፋብሪካቸው ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 37ቱ ሕጻናት የሆኑ 91 ማላዊያንን ያገኘ ሲሆን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሲሠሩ ነበር ተብሏል።

በደቡብ አፍሪካ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ትልቅ ስጋት ሲሆን አገሪቱ እንደ "መነሻ፣ መሸጋገሪያ እና መድረሻ" ተደርጋ እንደምትወሰድ መንግሥት ይገልጻል።

ኬቨን ሳኦ፣ ቼን ሁኢ፣ኪን ሊ፣ ጂያኪንግ ዣሆ፣ ማ ቢያኦ፣ ዳይ ጁንያንግ እና ዣንግ ዛሂሊያን ከተከሰሱባቸው 160 ክሶች ውስጥ በ158ቱ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

እነዚህም ሕገ ወጥ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ እንዲቆዩ መርዳት እና ሥራቸውን ባለማስመዝገብ የአገሪቱን የሠራተኛ ሕግ መጣስ እና ገቢያቸውን መዝግቦ መያዝ እና ሌሎችንም ይገኙበታል።

ፖሊስ በፋብሪካው ላይ ድንገተኛ ወረራ የፈፀመው ማምለጥ የቻለ ሠራተኛ ጥቆማ ከሰጠ በኋላ ነው።

በኋላ ላይ ሠራተኞቹ ያለ በቂ ሥልጠና እና የደኅንነት መሳሪያዎች በቀን ለ11 ሰዓት በሳምንት ሰባት ቀን እንዲሠሩ መገደዳቸው ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ከሚከፈለው ዝቅተኛ ደመወዝ በሰዓት 1.64 ዶላር በጣም ያነሰ ክፍያ ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን የእረፍት ጊዜ ከፈለጉ ደሞዛቸው ይቆረጥ አንደነር ተደርሶበታል።

በደቡብ አፍሪካ የሠራተኛ ሕግ መሠረት ሠራተኞቹ በቀን ከዘጠኝ ሰዓት በላይ መሥራት አይችሉም።

እንዲሁም የተለየ ስምምነት ካልተደረሰ በስተቀር እሁድን ጨምሮ "በሳምንት ቢያንስ ለ 36 ተከታታይ ሰዓታት የእረፍት ጊዜ" የማግኘት መብት አላቸው።

አንድ ግለሰብ ሠራተኞቹ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት የፋብሪካው ቅጥር ግቢ ምግብ ለመግዛት እንኳን ለቅቀው እንዲወጡ እንደማይፈቀድላቸው ተናግሯል።

ፋብሪካውንም ቆሻሻ እና ለሰው ልጅ የማይመች መሆኑን ተናግሯል።

እንደ ባለሥልጣናት ገለጻ በፋብሪካው ውስጥ ሲሠሩ የነበሩት ማሊያዊያን ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡት በኮንቴነሮች ውስጥ ተደብቀው ነው።

ሳኦ 'ቢውቲፉል ሲቲ' በሚል በተሰየመው ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሠራ የነበረ ሲሆን፣ አብረውት የተከሰሱት እና የተፈረደባቸው ደግሞ ተቆጠጣሪዎች መሆናቸውን ኒውስ24 ዘግቧል።

ፋብሪካው በድጋሚ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ብርድ ልብሶች ውስጥ የሚገባ ጥጥ ያመርታል።

የደቡብ አፍሪካ ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ውሳኔውን በደስታ ተቀብሎ "በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የምናደርገውን ትግል ለማጠናከር" ይረዳል ብሏል።

ቃል ዐቀባይ ፊንዲ ምጆኖንድዋኔ በበኩላቸው "ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በአገራችን ወረርሽኝ ሆኗል፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መዳረሻ ሆነናል" ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ፖሊስ ፋብሪካውን በድንገት ሲፈትሽ በስፍራው የተገኘው የሠራተኞች ሚኒስቴር፣ "እነዚህን ጉዳዮች ከሥራቸው ነቅሎ ለመጣል" በመንግሥት ተቋማት መካከል የበለጠ ትብብር እንዲደረግ ይረዳል ሲል የቅጣት ውሳኔውን በደስታ ተቀብሏል።