ደቡብ አፍሪካ በስፋት እየተሰራጩ ባሉ የሩሲያ ሥራዎች ሴቶች እንዳይታለሉ አስጠነቀቀች

ሲያን ቡጄ

የፎቶው ባለመብት, Cyan Boujee/TikTok

የምስሉ መግለጫ, በሩሲያ የተቀረፀው ሲያን ቡጄ የሥራ መስታወቂያ ቪዲዮ ከቲክቶክ ገጿ ላይ ተነስቷል

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ወጣት ሴቶች በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በስፋት በተሰራጩ የሩሲያ ሥራዎች እንዳይታለሉ እያስጠነቀቀ ነው።

መንግሥት ይህን ማስጠንቀቂያ ያወጣው በደቡብ አፍሪካዊያን የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በኩል በርካታ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያዎች በስፋት ከተሰራጩ በኋላ ነው።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሲያን ቡጄ በተባለች የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ተፅዕኖ ፈጣሪ የተሰራጨ እና አሁን ከገጿ የጠፋን የሥራ ማስታወቂያ እየመረመሩ ነው።

በቪዲዮው ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ሙያዊ ክህሎትን ማግኘት ለሚፈልጉ ሥራ ጀማሪ ወጣት ሴቶች የሁለት ዓመት "መርሃ-ግብር" ታስተዋውቃለች።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣት ደቡብ አፍሪካዊያን ሥራ አጥ ሲሆኑ፤ በርካቶች ደግሞ ሥራ ለማግኘት በእጅጉ የሚሹ ናቸው።

'ታታርስታን ሩሲያ የተቀረፀው የተፅዕኖ ፈጣሪዋ ቪዲዮ ምልምል ሠራተኞች የሚጠበቃቸውን ማረፊያም ያሳያል።

ትክክለኛ ሥሟ ሆነር ዙማ የሆነው ተፅዕኖ ፈጣሪዋ፤ መርሃ-ግብሩን "አዲስ ጅማሮ" በሚል የምትገልፅ ሲሆን፤ "በግልፅ እዚህ አገር ለሴቶች ፍትኃዊ ነው፤ ለአፍሪካዊያን፣ እስያዊያን፣ ላቲን አሜሪካዊያን. . ." በማለትም ታክላለች።

1.7 ሚሊዮን የቲክቶክ ተከታዮች ያሏት ቦጂ የሚቀጠሩ ወጣቶች ሥራ እንደሚሰጣቸው እና የሩሲያን ቋንቋ እንደሚማሩም ታብራራለች።

ወጣት ሴቶቹ በምን ሙያ ላይ እንደሚቀጠሩ ግልፅ አይደለም፤ ሆኖም የመርሃ-ግብሩ ማስታወቂያ ከ18 እስከ 22 ዓመት ያሉ ሴቶችን ኢላማ ያደረገ ነው።

ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ወንጀል ስለመስራቷ የሚያሳይ ነገር የሌለ ሲሆን፤ በሳምንቱ መገባደጃ ለቀረበባት ትችትም እስካሁን መልስ አልሰጠችም።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በማኅበራዊ የትስስር ገፅ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚተዋወቁ የውጭ አገር ሥራዎች አዝማማሚያ "በእጅጉ የተጨነቀ" መሆኑን ገልጿል።

የአገሪቱ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ኃላፊ ክሌይሰን ሞኒይላ በኤክስ ገፃቸው ወጣቶችን በተለይ ሴቶችን "ባልተረጋገጡ የውጭ አገር የሥራ ማስታወቂያዎች አትታለሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"አንድ ነገር አጓጊ ከሆነ [አትመኑ]፤ ሁለተኛ አስተያየት ጠይቁ" ሲሉ አክለዋል።

በታታርስታን ሩሲያ ተመልምለው ሥራ የተቀጠሩ ወጣቶች በዩክሬን ጦርነት ለሩሲያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ድሮኖችን በሚያመርት የጦር መሣሪያ ፋብሪካ እየሰሩ ነው የሚሉ ጭምጭምታዎች አሉ።

ከሥራ መልማዮቹ ግንባር ቀደም የሆነው 'የታታርታን ኢኮኖሚክ ዞን' የጦር መሣሪያ እንደሚያመርት ይታመናል።

ዓለም አቀፉ ድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ወንጀሎች መከላከል ባለፈው ግንቦት "ጀማሪ" የሥራ ማስታወቂያዎችን በሚመለከት የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ ለአዲስ ምልምል ሰራተኞች ስለ ሥራው ባህሪ፣ ሁኔታ እና የትምህርት እድል በሚመለከት የሀሰት መረጃዎች የሚያወጡ መልማዮች፤ ዋና ዓላማቸው "የድሮን መርሃ-ግብር" መደገፍ ነው ብሏል።