ሁለት ጥቁር ሴቶችን ገድለው በአሳማ ያስበሉ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ፍርድ ቤት ቀረቡ

አንድ ወጣት እና በእድሜ ገፋ ያለ ተካሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው
የምስሉ መግለጫ, አንድሪያ ዲ ዌት (በግራ) አለቃው ዘካሪያ ጆሀንሰን ኦሊቪየር (በቀኝ) ላይ ለዓቃቤ ሕግ ምስክርነት ይሰጣል

ሁለት ጥቁር ሴቶችን በመግደል የተጠረጠረው ነጭ ደቡብ አፍሪካዊ ገበሬ ሴቶችን ለአሳማ ተገድጄ ነው ያስበላሁት ማለቱን ጠበቆች ተናገሩ።

ባለፈው ዓመት የ45 ዓመት እድሜ ያላት ማሪያ ማኮጋቶ እና የ34 ዓመቷ ሉሲያ ናድሎቩን በደቡብ አፍሪካ ሰሜናዊ ሊምፖፖ ግዛት ምግብ ፍለጋ እንደወጡ መገደላቸው ታውቋል።

ማስረጃ ለመደበቅ በሚል አስከሬናቸው ለአሳማዎች ለምግብነት እንደተሰጠም ተነግሯል።

አድሪያን ዲ ዌት በግድያው ከተጠረጠሩ ሦስት ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን መካከል አንዱ ሲሆን፤ ትናንት ፍርድ ቤት ቀርቦ ምስክርነት ሰጥቷል።

ሰኞ ዕለት የፍርድ ቤት ሂደቱ ሲጀምር የ20 ዓመት እድሜ ያለው አድሪያን ለዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ በመቅረብ የእርሻው ባለቤት ዘካሪያ ጆሀንሰን ኦሊቪየር ሁለቱን ሴቶች በጥይት መግደሉን መስክሯል።

ሴቶቹ ለአሳማዎች ተብሎ የተቀመጠ የመጠቀሚያ ጊዜው ሊያልፍ የተቃረበ የወተት ምርት እየፈለጉ እያለ ተገድለዋል።

የእርሻው ተቆጣጣሪ የሆነው አድሪያን ዲ ዌት አስከሬኑን ለአሳማዎች ሲወረውር ተገድዶ እንደሆነ እንደሚመሰክር ጠበቃው እና ዐቃቢያን ሕጎች ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ምስክርነቱን የሚቀበል ከሆነ በእርሱ ላይ የቀረበው ክስ ውድቅ ይደረጋል።

ግድያው በመላው ደቡብ አፍሪካ ሕዝባዊ ቁጣ የቀሰቀሰ ሲሆን፤ በአገሪቱ ውስጥ የዘር ውጥረትን ጨምሯል።

ምንም እንኳ የነጮች የበላይነትን ያነገሰው የአፓርታይድ ስርዓት ከተገረሰሰ ከ30 ዓመታት በላይ ቢሆነውም፤ እንደዚህ ዓይነት ውጥረት በተለይም በገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች ይከሰታል።

አብዛኛው የእርሻ መሬት በአናሳ ነጮች እጅ የተያዘ ሲሆን፤ አብዛኞቹ የእርሻ ሠራተኞች ደግሞ ጥቁሮች ናቸው።

ይህም በጥቁር የአገሬው ሕዝቦች ቅራኔን እያባባሰ፤ ነጭ ገበሬዎች ደግሞ በከፍተኛ ወንጀል ምጣኔው ያማርራሉ።

ዊልያም ሙሶራ የተባለው የ50 ዓመት አርሶ አደር ሦስተኛ ተከሳሽ በመሆን ቀርቧል።

እርሱ እና የ60 ዓመቱ የእርሻው ባለቤት ኦሊቪየር እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ገና ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን አልሰጡም።

ሦስቱ ተከሳሾች ግድያው ሲፈፀም አብሮ የነበረው የአንዷ ሟች ባለቤት ላይ መሳሪያ በመተኮሳቸው የግድያ ሙከራ ክስ ይጠብቃቸዋል።

በተጨማሪም ሕገ ወጥ መሳሪያ መታጠቅ እና አስከሬኑን ለአሳማዎች በማብላት ማስረጃ በመደበቃቸው ፍትኅ የማደናቀፍ ክስ ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

ሦስተኛው ተከሳሽ የዙምባቡዌ ዜጋ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የኢምግሬሽን ሕግ በሕገ ወጥነት በመኖርም ተጨማሪ ክስ እንደሚመሰረትበት ይጠበቃል።

የሊምፖፖ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በችሎቱ ወቅት በደጋፊዎች እና በሟቾቹ ዘመዶች ተሞልቶ የነበረ ሲሆን ችሎቱ ወደ ሚቀጥለው ሳምንት ተዘዋውሯል።