የደቡብ አፍሪካው ጄነራል ኢራንን ደግፈው የሰጡት አስተያየት ትችት አስከተለባቸው

የደቡብ አፍሪካ ጦር አዛዥ ሩድዛኒ ማፍዋንያን

የፎቶው ባለመብት, Gallo via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የጄኔራሉን አስተያየት "አሳዛኝ" ሲል ገልጾታል

የደቡብ አፍሪካ ጦር አዛዥ በቅርቡ ኢራንን በጎበኙበት ወቅት ለቴህራን ያላቸውን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ መግለጻቸውን ተከትሎ ትችት ቀረበባቸው።

የደቡብ አፍሪካ ጥምር መንግሥት አባላት ጄነራል ሩድዛኒ ማፍዋንያ "ግዴለሽነት የተሞላበት ድፍረት" አሳይተዋል ሲሉ የተቿቸው ሲሆን፣ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው ከጄነራሉ ጋር "በአግባቡ ያልተመከረበት" ጉዟቸውን በተመለከተ ተገናኝተው እንደሚወያዩ አረጋግጠዋል።

ውዝግቡ ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ ጋር ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅት የተፈጠረ ነው።

አሜሪካ ደቡብ አፍሪካ ከቴህራን ጋር ባላት ግንኙነት እና በሌሎች ጉዳዮች ደስተኛ አይደለችም።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አካል የሆነው ዲሞክራቲክ አሊያንስ ጄነራል ማፍዋንያ "ወታደራዊ ፍርድ ቤት" እንዲቀርቡ ጠይቋል።

የጄነራሉ አስተያየት "ከወታደራዊ ውይይቶች አልፎ የሄደ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ የገባ ነው" ብሏል።

የጄነራል ማፍዌንያ ጉዞ ወታደራዊ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ቢሆንም ከኢራን አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ አገራት የጋራ ዓላማዎች እንዳላቸው እና ሁልጊዜም "ከተጨቆኑ እና ረዳት አልባ ከሆኑ የዓለም ሕዝቦች ጎን እንደሚቆሙ" መናገራቸውን በኢራን የሚታተመው ቴህራን ታይምስ ዘግቧል።

እስራኤል በጋዛ እያካሄደች የምትገኘውን ጦርነት በተመለከተም ሲናገሩ ለፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋፍ ገልጸው፣ ጉብኝታቸው ከራማፎሳ አስተዳደር "ፖለቲካዊ መልዕክት አለው" ሲሉ ለባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከእነዚህ አስተያየቶች ራሱን አግልሏል።

የመከላከያ ሚኒስቴር አስተየየቶቹን "አሳዛኝ" ያለ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ "የመንግሥትን ይፋዊ የውጭ ፖሊሲ አቋም አይወክሉም" ብሏል።

የራማፎሳ ቃል አቀባይ ቪንሴንት ማግዌንያ ፕሬዝዳንቱ ስለጉዞው አያውቁም ወይም ይሁንታ አልሰጡም ነበር ብለዋል።

ማግዌንያ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ "ጉብኝቱ ተገቢው ምክክር ያልተደረገበት እና ጄነራሉ በሚሰጧቸው አስተያየቶች የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባቸው" ብለዋል።

ጄነራል ማፍኒያ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ማግዌኒያ አረጋግጠዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከኢራን ጋር የነበራት ጠንካራ ግንኙነት ከአሜሪካ ጋር ላላት አለመግባባት ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ግንኙነታቸው እንዲበላሽ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጠው እርዳታ እንዲቋርጥ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን፣ አገሪቱ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት "እንደገና በማጠናከር" የአሜሪካ ጠላት ሆናለች ሲሉ ከስሰዋል።

ትራምፕ የራማፎሳን መንግሥት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን ያሳድዳል በማለት በሐሰት የወነጀሉ ሲሆን፣ በእስራኤል ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) አቅርቧል በማለትም አውግዘዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት የሚጀምረው በአውሮፓውያኑ 1995 ሁለቱ አገራት የጋራ የትብብር ኮሚሽን ካቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ነው።