በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የሞት ቅጣት፣ ወንጀልን ለመግታት አስተዋጽኦ አለው?

የሞት ቅጣት

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት ቅጣት እየጨመረ ነው።

የሰብአዊ መብት ቡድኑ እአአ በ2023 ብቻ 1153 የሞት ቅጣት መዝግቧል። በ2022 ከነበረው 883 አንጻር የ31 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከስምንት ዓመታት ወዲህ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የተመዘገበው ከፍተኛው አሃዝ ነው። በ2015 ብቻ 1634 የሞት ቅጣት መዝግቦ ነበር።

የመብት ተሟጋቹ ተቋም ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ “የሞት ቅጣቶች ከፍተኛ ጭማሪ ያሳዩት በዋነኝነት በኢራን ምክንያት ነው። የኢራን ባለሥልጣናት ለሰው ሕይወት ፍጹም ንቀት አሳይተዋል። ከአደንዛዥ እጽ ጋር ለተያያዙ ወንጀሎች ግድያዎችን አስፋፍተዋል። የሞት ቅጣቱ በኢራን በጣም የተገለሉ እና ድሃ በሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ ያለውን አድሎአዊ ተጽዕኖም ያሳየ ነው” ብለዋል።

ምንም እንኳን በሪፖርቱ ለተመዘገበው አብዛኛው የሞት ቅጣት ኢራን [853 ሰዎች ተገድለዋል] ተጠያቂ መሆኗን ቢያሳይም፣ አምነስቲ ከፍተኛ የሞት ቅጣት የሚተላለፍባት አገር ቻይና ነች ብሎ ያምናል።

በቻይና ስለተፈጸመው የሞት ፍርድ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ሲል አምነስቲ ይገምታል።

አምነስቲ አክሎም በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት ፍርድ በ20 በመቶ ጨምሯል ብሏል።

የሞት ቅጣትን በብዛት የሚጠቀሙ አገሮች የትኞቹ ናቸው?

አምነስቲ እአአ በ2023 ከፍተኛ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው አምስት አገራት ቻይና፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሶማሊያ እና አሜሪካ መሆናቸውን አስታውቋል።

ከእነዚህ የሞት ቅጣቶች ውስጥ 74 በመቶ ያህሉ በኢራን የተመዘገቡ ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ 15 በመቶውን ትይዛለች።

እንደ ቻይና ሁሉ አምነስቲ ከሰሜን ኮሪያ፣ ከቬትናም፣ ከሶሪያ፣ ከፍልስጤም ግዛቶች እና ከአፍጋኒስታን ይፋዊ መረጃዎችን ማግኘት አልቻልኩም ብሏል።

የአገራት ካርታ

ስንት አገራት የሞት ቅጣትን አስቀሩ?

በአውሮፓውያኑ 1991 የሞት ቅጣትን ያስወገዱ አገራት ቁጥር 48 ነበሩ። ይህ ቁጥር በ2023 ወደ 112 ከፍ ብሏል።

ዘጠኝ አገራት በጣም ከባድ ለሆኑ ወንጀሎች ብቻ የሞት ቅጣትን የሚተገበሩት ሲሆን፣ 23 የሞት ቅጣት ያለባቸው አገራት ደግሞ ቢያንስ ለአስር ዓመታት ፍርዱን አልተጠቀሙበትም።

በዓለም ዙሪያ የሞት ቅጣት እንዴት ይፈጸማል?

እአአ በ2023 አራት የታወቁ የሞት ቅጣት መፈጸሚያ ዘዴዎች አሉ። አንገትን በመቅላት የሞት ቅጣት የምትፈጽው ሳዑዲ አረቢያ ብቻ ናት።

ባለፈው ዓመት ሰባት አገራት በስቅላት፣ ስድስቱ ደግሞ በጥይት የሞት ቅጣት ሲፈጽሙ፣ ሦስት አገራት ገዳይ መርፌዎችን ተጠቅመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ ቮልከር ቱርክ “የሞት ቅጣትን ከሰብዓዊ ክብር እና ከመሠረታዊ የመኖር መብት ጋር ለማስታረቅ በጣም ከባድ ነው” ብለዋል።

አገራት

የሞት ቅጣትን መቀልበስ

ይህ የቅጣት ውሳኔ ከተሰጠ እና የይግባኝ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የተፈረደበት ሰው ከተከሰሰበት ወንጀል ነጻ ሲሆን እና በሕግ ፊት እንደ ንጹህ ሆኖ ሲቆጠር ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሦስት አገራት ማለትም በኬንያ (5)፣ በአሜሪካ (3)፣ በዚምባብዌ (1) ሞት የተፈረደባቸው 9 ሰዎች ቅጣታቸው መቀልበሱን መዝግቧል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ንጹህ ሆነው የሚገኙበት ዕድል በመኖሩ የሞት ቅጣትን ይቃወማሉ።

የሞት ቅጣትን መከላከል

በአብዛኞቹ የሞት ቅጣት በሚተላለፍባቸው አገራት ፍርዱ የሚቀመጠወው “ወንጀልን ይከላከላል ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ የተነሳ ነው” ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ግን የሞት ቅጣት መኖር ወንጀልን የመከላከል ውጤቱ ያልተረጋገጠ መሆኑን ይስማሙበታል።

አንዳንዶች ወንጀልን በጣም የሚከላክለው በቁጥጥር ስር የመዋል እና የመቀጣት ዕድል ነው ይላሉ።

እአአ በ1988 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሞት ቅጣት እና በግድያ ምጣኔ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል።

ይህ ጥናት በ1996 ተሻሽሏል። “የሞት ቅጣት ከዕድሜ ልክ እስራት የበለጠ ወንጀልን የመከላከል አቅም እንዳለው ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ አልተቻለም” ሲልም ደምድሟል።

የሞት ቅጣት

በልጆች ላይ ያለው ተጽዕኖ

እአአ በ2010 አልጄሪያ፣ አርጀንቲና፣ ካዛኪስታን፣ ሜክሲኮ እና ቱርክን ጨምሮ 14 አገራት በሞት ቅጣት ላይ ዓለም አቀፍ የፀረ ሞት ቅጣት ኮሚሽን ለማቋቋም ተሰብስበው ነበር።

ኮሚሽኑ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመን እና ቶጎን ጨምሮ የአባል አገራቱን ቁጥር 24 አድርሷል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው ሪፖርት የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን ድርጊቱን ቢከለክልም፤ በብዙ አገራት ሕጻናት ለሞት ቅጣት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አሳስቧል። ኮንቬንሽኑ በ196 አገሮች ተፈጻሚ ነው።

የአሜሪካ ሳይኮሎጂካል አሶሲየሽን (ኤፒኤ) በበኩሉ ከ 21 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣትን መተግበርን እንዲያስቀሩ የአሜሪካ ግዛቶችን ጠይቋል።

“አሁን ካለው ሳይንሳዊ ጥናት በመነሳት ከ18 እስከ 20 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሕፃናት አእምሮ ከ17 ዓመት ታዳጊዎች ፈጽሞ የተለየ ነው ማለት አይቻልም” ሲል ጽፏል።

“በ16 እና በ17 ዓመት ታዳጊዎች ላይ የሞት ቅጣት አለመስጠትን የሚያረጋግጡ የወጣትነት እና ያለመብሰል ባህሪያት ከ18 እስከ 20 ዓመት ባሉት ታዳጊዎች ላይም ተመሳሳይ ናቸው” ሲል አክሏል።

ሕጻናት የሚጎዱት በሞት ቅጣቱ ብቻ አይደለም። ኮሚሽኑ “ወንጀለኛን ከሚቀጣ ከየትኛውም ዓይነት ቅጣት በተለየ የወላጅ በሞት መቀጣት ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ግንኙነት የመመሥረት ዕድላቸውን በቋሚነት ያሳጣቸዋል” ብሏል።