ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ በማድረግ ቀዳሚ መሆናቸው ተገለጸ

የሞት ቅጣት እንዲቆም የሚጠይቅ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2023 ጥፋተኛ በተባሉ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ በማድረግ ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ ቀዳሚ አገራት ናቸው አለ።

የመብት ተሟጋቹ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ተፈጻሚ የሚያደርጉትን የሞት ቅጣት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመራቸው በ2023 የተመዘገበው አሃዝ ከባለፉት 8 ዓመታት ከፍተኛው ነው ብሏል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ16 አገራት 1ሺህ 153 ሰዎች የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።

ከእነዚህ መካከል 74 በመቶ የሚሆኑት በኢራን የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሲሆን 15 በመቶ የሚሆኑት የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ደግሞ በሳዑዲ ነው።

በዚህ የአምነስቲ ሪፖርት ላይ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በሞት ከምትቀጣው ቻይና መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ቤይጂንግ በሪፖርቱ አልተካተተችም።

“በአገራዊ ሚስጢር ምክንያት፤ በዓለም ቀዳሚ የሞት ቅጣት ፈጻሚዋ አገር በየዓመቱ የሚፈጸሙ በሺዎች የሚገመት ሞትን በሪፖርቱ ማካተት አልተቻለም” ብሏል አምነስቲ በዓመታዊ ሪፖርቱ።

ከቻይና በተጨማሪ ትንሽ የማይባሉ ጥፋተኞችን በሞት በመቅጣት ከሚታወቁት ሰሜን ኮሪያ እና ቪዬትናም መረጃ ማሰባሰብ አልተቻለም።

አምነስቲ እንደሚለው ባለፈው ዓመት ኢራን ቢያንስ 853 ሰዎችን በሞት የቀጣች ሲሆን አብዛኛዎች ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉ ናቸው።

"የኢራን ባለስልጣናት ለሰው ልጅ ሕይወት ቅንጣት ታክል መጨነቅን ሳያሳዩ በአደንዣዥ ዕጽ ወንጀል የሞት ቅጣት ተግባራዊ አድርገዋል” ሲሉ የአምስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሐፊ አግነስ ካላማርድ ተናግረዋል።

ከኢራን በተቃራኒ ፓኪስታን ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ የሚባሉ ሰዎች የሞት ቅጣት እንዳይተላለፍባቸው ሕግ አሻሽላለች።

ማሌዢያ ደግሞ ከአሁን በኋላ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ እንዳይሆን አዛለች።

እአአ 2022 የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸው በነበሩት ቤላሩስ፣ ጃፓን፣ ማይናማር እና ደቡብ ሱዳን በ2023 የሞት ቅጣት አልተፈጸመም።

አምነስቲ ሰልጥነዋል ከሚባሉት ምዕራባውያን አገራት የሞት ቅጣት ተፈጻሚ በሚሆንባት አሜሪካ ያለውን አሃዝ ተመልክቷል።

በ2023፣ 24 ሰዎች የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል። ከዛ በቀደመው ዓመት በሞት የተቀጡ አሜሪካውያን ቁጥር 18 ነበር።