"ቦብ ማርሌይን ለማየት ከትምህርት ቤት ቀርቼ ፎቶ አንሺው ሆንኩኝ"

የፎቶው ባለመብት, Dennis Morris
በአንዲት ማለዳ የ14 ዓመቱ ዴኒስ ሞሪስ ሕይወቱን ለዘላለም የሚቀይር ውሳኔ ላይ ደረሰ።
ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1973 ነበር።
"ቦብ ማርሌይ የመጀመሪያውን የእንግሊዝ ጉብኝት ሊያደርግ እየመጣ ነበር። ከትምህርት ቤት ቀርቼ ፎቶግራፍ ላነሳው ወሰንኩ። ሙዚቃውን ወደሚያቀርብበት የለንደን ክለብ አቀናሁ።"
ክለቡ ደርሼ "ቦብ ወደእኔ ሲቃረብም 'ፎቶህን ማንሳት እችላለሁ?' አልኩት እሱም ቀለል አድርጎ 'አዎ ግባ' አለኝ" ይላል።
መድረኩ እስኪዘጋጅ ድረስም ቦብ ዴኒስን በእንግሊዝ ማደግ እንዴት እንደሆነ ጠየቀው።
ዴኒስም በምላሹ ቦብን በጃማይካ ስላለው ሕይወት ይጠይቀው ጀመር።
ጨዋታቸው ቀጠለና ቦብ ማርሌይ ስለ መጪው የሙዚቃ ጉዟቸው ለትንሹ ዴኒሰ ነገረው።
"አብሬያቸው መምጣት እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። በነጋታው ሻንጣዬን ሸክፌ ሆቴላቸው ሄድኩኝ። በዚህ ሁኔታ በቀላሉ ተቀላቀልኳቸው" ይላል።
ሆኖም የሙዚቃ ዝግጅቱ ጉዞ ለሳምንታት ብቻ ነው የቆየው።
አንዳንድ የባንዱ አባላት አጥንት ውስጥ የሚገባውን በረዶ መቋቋም ስላልቻሉ ወደ ቤታቸው መመለስ ፈለጉ።
ይህ ጉዞ ለዴኒስ ፈር የቀደደለት ነበር።
በርካታ የዓለማችን ስመ ጥር ሙዚቀኞችን ፎቶ ያነሳበት የሙያው ጉዞው የተጠነሰሰበት ነበር።
በዚያን ወቅት በነበረው የባንዱ የሙዚቃ ጉዞ ቦብ ማርሌይን ያነሳቸው ድንቅ ፎቶዎች በቅርቡ በለንደን ሶሆ ጋለሪ ለአውደ ርዕይ በቅቷል።

የፎቶው ባለመብት, Dennis Morris
ዴኒስ ትውልዱ ጃማይካ ነው፤ በአውሮፓውያኑ 1960።
ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ለንደን ያቀኑትም በአምስት ዓመት ዕድሜው ላይ ነው።
ዴኒስ ለፎቶ ፍቅር ያደረበት ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለ ነበር።
በአካባቢው የነበረው ቤተ ክርስቲያን የመዘምራን ቡድንም የፎቶግራፍ ክለብ ስለነበረው እሱን ተቀላቀለ።
"በአንድ ወቅት በጨለማ ክፍል ውስጥ አንድ ልጅ ፎቶግራፍ ሲያትም ተመለከትኩኝ፤ በዚያች ቅጽበት ይህ ሕይወቴ ምን እንደሚሆን ተረዳሁ" ይላል ዴኒስ ሕይወቱ የተቀየረችበትን ቅጽበት ሲያስረዳ።
ቦብ ማርሌይን በመጀመሪያ የለንደን ጉብኝቱ ፎቶ አንስቶት የነበረው ዴኒስ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 1975 ሲመለስም ዴኒስ ዝግጁ ነበር።
ከፍተኛ ዕውቅና ባገኘው በልሲየም ቲያትር የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ዴኒስ ተገኘ።

የፎቶው ባለመብት, Dennis Morris
"በመጀመሪያ የሙዚቃ ዝግጅቱ ወቅት ቦብ እንዴት እንደሚዘፍን ስለተረዳሁ በሁለተኛው ዝግጅቱ የሚገርሙ ፎቶዎችን ማንሳት ቻልኩ። ፎቶዎቼም ለታዋቂዎቹ ኤንኤምኢ፣ ሜሎዲ ሜከር እና ታይም አውት መጽሔቶች ሽፋን መሆን ቻሉ" ሲልም የነበረውን ስኬት ያስረዳል።
ዴኒስ ቦብ ማርሌይ ሕይወቱ እስካለፈበት የአውሮፓውያኑ 1981 ድረስ ሙዚቀኛውን እየተከተለ ድንቅ የሚባሉ ፎቶዎችን አንስቷል።
"ፍላጎቴ የሙዚቃ ፎቶግራፍ አንሺ መሆን አልነበረም። ህልሜ የጦርነት ፎቶግራፍ አንሺ መሆን ነበር። ነገር ግን ይህም ታላቅ የሙያ ጉዞ ነው" ይላል።
ዴኒስ ምንም እንኳን ጦርነቶችን ፎቶ ማንሳት ባይችልም አንዳንድ ግጭቶችን በካሜራው ማስቀረት ችሏል።
በተለይም ማኅበረሰባዊ እሴቶችን ብዙ የማይቀበለው የፐንክ ሙዚቃ ከፍታ ላይ በደረሰበት በአውሮፓውያኑ 1977 ወቅትንም በዴኒስ ፎቶዎች መመልከት ይቻላል።
በወቅቱ ስመ ጥር የነበሩትን የዩናይትድ ኪንግደም ፐንክ ሮክ ባንድ 'ዘ ሴክስ ፒስትልን' ተከትሎ የሙዚቃ ሕይወታቸውን በካሜራው ማስቀረት ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Pearl de Luna
"ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ ነበር። ሁልጊዜም ያለ ማቋረጥ ዛቻ ይደርስባቸው ነበር። እንዲሁም ጎዳና ላይ በሚወጡበት ወቅትም ጥቃት ይደርስባቸው ነበር። የሙዚቃ ዝግጅታቸውም በሁከት የተሞላ ነበር" ሲል ዴኒስ ያስረዳል።
"ከ ዘ ሴክስ ፒስትል ጋር በምሠራበት ወቅት ራሴን ጦርነት ላይ አገኘሁት። ለእኔ ግሩም ወቅት ነበር" በማለት ዴኒስ የነበረውን ሁኔታ ይገልጸዋል።
ታዋቂዎቹን ፓቲ ስሚዝ፣ ኦሳይስ፣ ጎልዲ እና ራዲዮ ሄድ ዴኒስ ፎቶ ካነሳቸው ሙዚቀኞች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሆኖም የለንደን ነዋሪው ዴኒስ ሙዚቀኞችን ፎቶዎች የማንሳት ሥራው የልቡ የሚላቸውን ፕሮጀክቶች እንዲሠራ ገንዘብ ማግኛ መንገድ ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ በለንደን ጥቁር ሆኖ ማደግ ምን ይመስላል? በሚል የሚፈትሸው ሥራው 'ግሮዊንግ ኦፕ ብላክ' አንዱ ፕሮጀክቱ ነው።
ሌላኛው ደግሞ 'ሳውዝ ሆል - ኤ ሆም ፍሮም ሆም' ደግሞ በለንደን በሚኖሩ የሕንድ የሲክ ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ ነው።
"ማኅበረሰቤን፣ ሰፈሬን እና ከዚያም ወጣ ብሎ ያለውን ሕይወት በካሜራዬ እያስቀረሁ ነበር" ሲል ያስረዳል።
"ሰዎች በራቸውን ከፍተው እንዲያናግሩኝ ማድረግ ቻልኩ። በተፈጥሮዬ ይህ ልዩ ችሎታ አለኝ። ልገልጸው በማልችለው ሁኔታ ያዩኛል፤ ያምኑኛል" ብሏል።
ይህ ልዩ ችሎታው በሙዚቃው ኢንዱስትሪም ሆነ በዘጋቢ ሥራዎቹ ስኬታማ አድርገውታል።
"ሙዚቀኞቹን ፎቶ እያነሳሁ ከሆነ ለማድረግ የምሞክረው ያጠለቁትን ጭንብል አውልቆ እውነተኛ ማንነታቸውን ለማሳየት ነው የምሞክረው። ሁሉም ሙዚቀኞች መታየት የሚፈልጉበት መንገድ አለ፤ ከዚያ ባለፈ እንዲታዩ ነው የምፈልገው" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Dennis Morris
"በርካታ ሰዎች ከቦብ ማርሌይ እስከ ዘ ሴክስ ፒስትልስ ያሉ ፎቶዎችን ሲመለከቱ ከእኔ ጋር በስፍራው እንደነበሩ እንደሚሰማቸው ይነግሩኛል። ዝም ብሎ ፎቶዎች ብቻ አይደሉም። በእውነቱ እዚያው በስፍራው እንደነበርክ ይሰማሃል፤ አንተም የዚያ አካል ትሆናለህ" ሲል ይገልጻል።
ዴኒስ ከሰሞኑ እየታየ ባለው የፎቶ አውደ ርዕይ በርካቶች በሰጡት ምላሽ በጣም ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።
እነዚህ ፎቶዎች በለንደን ሶሆ 'ዘ ፎቶግራፈርስ ጋለሪ' በሚል ርዕስ ለዕይታ ከመቅረባቸው በፊት በፓሪስ በሚገኘው 'ሜይሶን ኢዩሮፒየን ደ ላ ፎቶግራፊ' አሳይቶ ነበር።
"በርካቶች ያለፈውን ሕይወታቸውን ወይም የወላጆቻቸውን ሕይወት በእነዚህ ፎቶዎች እያዩ እንደሆነ ይናገራሉ። 'ግሮዊንግ አፕ ብላክ' በተሰኘው ፕሮጀክቴ በቀረቡት ፎቶዎች ላይ በዚያን ጊዜ ጥቁር ሆኖ እንግሊዝ መምጣት የነበረውን ሕይወት የሚያስቃኝ ነው። ልጆቻቸው እነዚህን ፎቶ ሲመለከቱም የወላጆቻቸውን ሕይወት ይረዳሉ። እናም ተደንቀው ይመለከቷቸዋል" ይላል።
"በሙዚቃው በኩል ደግሞ የባንዶቹን የቅርበት እንዲሁም አይተዋቸው የማያውቁ እንቅስቃሴዎችን ይመለከታሉ። የሙዚቀኞቹንም ጉዞ በዚያው ይቃኙታል። በሁሉም በጣም እኮራባቸዋለሁ" ሲል የፎቶ ባለሙያው ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Dennis Morris















