ስለ ሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌይ አራት አስገራሚ እውነታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሬጌ ሙዚቃ ንጉሡ ቦብ ማርሌይ የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው ‘ዋን ላቭ’ ፊልም በዛሬው ዕለት ለዕይታ ይበቃል።
ፊልሙ ቦብ ማርሌይ ከተወለደባት የጃማይካ የገጠር መንደር በዓለም አቀፍ መድረክ ያንጸባረቀበትን እና በሕይወቱ ያከናወናቸውን የታወቁ ተግባራትን ይዳስሳል።
ለሰው ልጅ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ቦብ ማርሌይ የአፍሪካውያንን መተባበር፣ የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ፣ ጥቁር ሕዝቦች ከጭቆና ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል፣ የጦርነትን አስከፊ ገፅታ ቅኔ በተሞላ ግጥሞቹ ማስተላለፍ የቻለ ከጃማይካ የተገኘ ፈርጥ ነበር።
ሙዚቃዎቹ ትውልድን እየተሻገሩ፣ ድንበር ሳይወስናቸው፣ ዘርና ቀለም ሳይገድባቸው አሁን ድረስ ብዙዎችን ማስተሳሰር ችለዋል።
ለኢትዮጵያም ሆነ ለአህጉሪቷ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዩ ቦብ ማርሌይ ኢትዮጵያንም በሕይወት እያለ ጎብኝቷል።
አንዳንድ ሙዚቃዎቹ ብሔራዊ መዝሙር በሚመስል ሁኔታም በአፍሪካውያን ዘንድ ይታወቃሉ። ዘረኝነትን መዋቅራዊ ጭቆናን፣ መገለልን በማውገዝ ፍቅርን፣ መከባበርን ሰላምን በተግባርም አሳይቷል።
የአገሩን ባላንጣ ፖለቲከኞች በአንድ መድረክ ላይ በማምጣት በሙዚቃው ያጨባበጠው ቦብ ማርሌይ፣ አፍሪካውያንን በአፍሪካ ዩናይት’፣ ዚምባብዌ፣ ጌት አፕ ስታንድ አፕ፣ ዋን ድሮፕ፣ ራይድ ናቲ ራይድ፣ ቶፕ ራንኪን፣ ዋን ላቭ እንዲሁም በሌሎችም አይረሴ ዘፈኖቹ ይዘክሩታል።።
ምንም እንኳን ሙዚቀኛው ስሙ ከዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ ቢናኝም፣ እስሱን የሚመለከቱ አንዳንድ አስገራሚ እውነታዎች አሁን ድርስ ይሰማሉ። ስለ ሬጌው ንጉሥ ላያውቋቸው የሚችሉ አራት ነገሮችን እነሆ፡

የፎቶው ባለመብት, Getty images
የጃፓን የሬጌ ፈርጥ ቦብ
ቦብ ማርሌይ በጃፓን ታላቅ ነው። በሙዚቃውም ቢሆን ሬጌ ተወዳጅ ነው።
በአውሮፓውያኑ 1975 ጃፓንን የጎበኘው ቦብ,፥ ከዝነኛው የጃፓን ሙዚቀኛ እና ከበሮ ተጫዋች ማሻይቶ ‘ፔከር’ ሃሺዳ ጋር ጓደኝነት እንደመሠረተ የጃፓኑ መጽሔት ሳቡካሩ አስነብቧል።
ይህም ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸውን አልበሞች ለመሥራት እና በሙዚቃም ለመጣመር ምክንያት ሆኗል። ሁለቱ ሙዚቀኞች ፔከር ፓወር እና ኢንስታንት ራስታ የሚሉ አልበሞችንም በጃማይካ ቻነል ዋን ስቱዲዮ ተጣምረው ቀርጸዋል።
አልበሞቹ የጃማይካ እና የጃፓንን አርቲስቶችን ከማጠመር በተጨማሪ የሬጌ ሙዚቃን ተወዳጅ በማድረግ ፈር ቀደዋል። የሬጌ የሙዚቃ ስልት በጃፓን ተወዳጅ ሙዚቃ ነው።
ታዋቂዎቹ ዮካሐማ የሬጌ ፌስቲቫል እና ዮካሐማ ሬጌ ሳይ የተባሉት ዝግጅቶቹ በየዓመቱ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወቅቶች በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ተሸላሚው ቦብ
ቦብ ማርሌይ በአገሩ ውስጥ የሰፈነውን ጭቆና፣ የጥቁሮችን ሰቆቃ የሚቃወሙ እና የሰውን ልጅን እኩልነትን እና ሰላምን በሚሰብኩ የፖለቲካ ግጥሞቹ ይታወቃል።
በአውሮውያኑ 1978 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። ይህም ጃማይካ በፖለቲካ ቀውስ በምትናጥበት ወቅት ሰላምን እና ፍትህን ለማስፍን ላከናወነው ተግባርም ዕውቅና ለመስጠት ነው።
ሽልማቱን ከመቀበሉ ከአንድ ዓመት በፊትም በጃማይካ መዲና ኪንግስተን ዋን ላቭ በተሰኘ የሰላም የሙዚቃ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።
በሙዚቃ ዝግጅቱ ዐይን ለዐይን መተያየት የማይችሉ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ቡድኖችን መድረክ ላይ ለማጨባበጥ ችሏል።
አገሪቱንም እያናወጣት የነበረው የተደራጁ ቡድኖችን ጥቃትም ለመግታት ያለመ ነበር የሙዚቀኛው ጥረት። በዓመቱም የተባበሩት መንግሥታት ሙዚቀኛውን ወደ ኒው ዮርክ ጋብዞ ሽልማቱን አበርክቶለታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእጅ መዳፍ አንባቢው ቦብ
ቦብ ማርሌይ እንዲህ ዝነኛ ሙዚቀኛ ከመሆኑ በፊት በጃማይካ በምትገኘው ሴይንት አን በተሰኘው መንደሩ የእጅ መዳፍ ያነብ ነበር።
በልጅነቱ የጓደኞቹን እና የጎረቤቶቹን መዳፍ በማንበብ የሕይወታቸው ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ይተነብይላቸው ነበር። የሙዚቀኛው የቅርብ ጓደኛ አለን ኮል እንደሚያስታውሰው ትንበያዎቹ ዝንፍ የማይሉ መሆናቸውን በመግለጽ “ተዓምራዊ” ይላቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ በነበረው የቦብ ማርሌይ ኮንሰርት ላይ በዝግጅቱ ትልቅ ሚና የነበረው ኮል የመዳፍ ንባብ በጃማይካ ውስጥ የተከለከለ እንደነበር ያስታውሳል።
በቦብ ዙሪያ የነበሩት የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮችም ቦብ የእጅ መዳፍ ንባቡን እንዲያቆም ይጎተጉቱት ነበር። ቦብ ማርሌይ ትንበያውን ከማቆሙ በፊት የራሱ የሙዚቃ ስቱዲዮ እንደሚኖረውም ተንብዮ ነበር።
የፋብሪካ ሠራተኛው ቦብ
ቦብ ማርሌይ በአሜሪካ በነበረበት ወቅት በሙዚቃው ኑሮውን ማሸነፍ ስላልቻለ አጠር ላለ ጊዜ በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ ሠርቷል።
በዴላዌር ግዛት ክራይስለር በተባለ የመኪና ፋብሪካ ውስጥ ነበር የሰራው። ቦብ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ በሠራቸው ሙዚቃቹ በአገሩ ጃማይካ በተወሰነ ደረጃ ዝነኛ የነበረ ቢሆንም በኢንዱስትሪው ይህ ነው የሚባል አሻራ ማሳረፍ አልቻለም ነበር።
አገሩን ትቶ እናቱ ሴዴላ ቡከር ይኖሩበት ወደነበረው የአሜሪካ ግዛት ዴላዌር አቀና። እናቱ በአውሮፓውያኑ 1955 የቦብ አባት ከሞቱበት ወቅት ጀምሮ ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው ነበር።
ቦብ በአስር ወር የፋብሪካ ሥራ ቆይታውም በምሽት ፈረቃ ነበር የሠራው። ይህም ሥራው በአውሮፓውያኑ 1976 ባወጣው ራስታማን ቫይብሬሽን በተሰኘው አልበሙ ለተካተተው ናይት ሽፍት ለተሰኘው ሙዚቃው መነሻ መሆኑን ጓደኞቹ ይናገራሉ።












