ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ‘ጃ’ በዓለም አቀፉ ምናብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዛሬ ስልሳ ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ- ነጻነታቸውን ያገኙ አፍሪካውያን ሊመክሩ ነው ተባለ።
የግብፁን መሪ ጋማል አብደል ናስርን ለመቀበል ከጅማ፣ ከሐረር እና ከአርሲ በርካቶች ተመሙ።
ድህነትን የተጠየፈችው አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት የሚመጡ እንግዶቿን ለመቀበል የኔቢጤዎችን፣ የቀን ሠራተኞችን እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎችን አጎረች።
ሚሊዮኖች አፍሪካውያን ዜጎችን በጭቆና ቀንበር ካንበረከከው፣ ሰብዓዊነትን ከማማ ላይ ካወረደው እንዲሁም የነጮችን የባህል፣ የእሳቤ እና የፖለቲካ የበላይነት ለዘመናት የሰበከውን ቅኝ ግዛትን ታግለው ያሸነፉ ተምሳሌቶችም ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።
በአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመምከር ከተገኙትም መካከል ነጻነቷን ካገኘች ዓመት የሆናት የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት የሆኑት አህመድ ቤንቤላ፣ የታንጋኒካው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የጊኒው አህመድ ሴኩቱሬ፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ፣ የግብፁ ጋማል አብደል ናስር ይገኙበታል።
አዲስ በተገነባው በአፍሪካ አንድነት አዳራሽ በአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ እየመከሩ የነበሩት አብዮተኞች ክርክር ጦፈ።
የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባታል ሲሉም አጥብቀው ተከራከሩ።
ይህ ዕድል ሊያመልጠን አይገባም የአፍሪካ ሕዝብም ይቅር አይለንም አሉ።
የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም በአፍሪካዊ መልክ የቀረጹት ጁሊየስ ኔሬሬ በበኩላቸው አፍሪካውያን በአንድ ጥላ ስር ሆነው መንግሥት መመሥረት ቀስ በቀስ የሚሆን ነው አሉ።
በአንድ በኩል ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ላይቤሪያን ጨምሮ አብላጫውን የያዙት ሞኖሮቪያ የተሰኘው ቡድን የአፍሪካ መዋሃድ ቀስ ብሎ የሚመጣ ነው የሚል እምነት ነበራቸው።
በሌላኛው ጎን ቁጥራቸው አነስ ያሉትና በግራ ዘመም አብዮተኞቹ እንደነ ንክሩማህ፣ ሴኩቱሬ የሚመራው የካዛብላንካው ቡድን በእሳቤ ደረጃ ሳይሆን አፍሪካውያን በአንድ ጥላ ስር መንግሥት መመሥረት ይገባል ብለው ተሟገቱ።
የአንድነት ህልማቸው ተቀባይነት ያላገኘው ክዋሜ ንክሩማህ ስብሰባውን ረግጠው ለመውጣት ዛቱ።
በዚያች ዕለት፤ በሰባዎቹ ዕድሜ ላይ የነበሩት አጼ ኃይለ ሥላሴ የጊኒው ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን ወደ ጎን ጠሯቸው።
የግራ ዘመም አብዮተኞቹን ሴኩቱሬን እና ንክሩማህን ጥብቅ ወዳጅነት ኃይለ ሥላሴ ያውቁ ነበር።
ኃይለ ሥላሴ በፈረንሳይኛ ‘mon fils’ ትርጉሙም ‘ልጄ’ እንደማለት ነው።
“ልጄ፤ እለምንሃለሁ፣ ሂድና ወንድምህን አምጣ” አሉት።
ሴኩቱሬም በፈረንሳይኛ ‘oui pere’ (እሺ አባቴ) የሚል ምላሽ ሰጡ።
ሴኩቱሬ በፍጥነት ወጥተው ክዋሜ ንክሩማህን ተመልሰው ይዘው ሲመጡ የአፍሪካ አንድነት አዳራሽ ውስጥ ተሳታፊው በጭብጨባ፣ እንዲሁም የአፍሪካን አንድነት ለመመሥረት በነቂስ ሲጠባበቅ የነበረውም በደስታ ፈነደቀ።
ንክሩማህ ተመልሰው ከመጡም በኋላ “ለአፍሪካ ስል ተሳትፎዬን እቀጥላለሁ” አሉ።
“ንክሩማህ ረግጦ ቢወጣ አስከፊ ይሆን ነበር። በወቅቱ አጼ ኃይለ ሥላሴ ድንቅ የተባለውን የዲፕሎማሲ መንገድም በመጠቀም መልሰውታል” ይላሉ የወቅቱን ሁኔታ በማስታወስ ከቢቢሲ ወርልድ ጋር በአንድ ወቅት ቆይታ አድርገው የነበሩት ዶክተር በረከት ሃብተ ሥላሴ።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኝ የነበሩት ዶክተር በረከት ሃብተ ሥላሴ የጉባኤውን ረቂቅ ቻርተርም ከጻፉት አንዱ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“የአፍሪካ አባት” በመባል የሚጠሩት እና ኢትዮጵያን ለ44 ዓመታት የገዟት አጼ ኃይለ ሥላሴ ዛሬ፣ ሐምሌ 16 የተወለዱባት ዕለት ናት።
‘ያህዌ’ በሚለው መጠሪያ ‘ጃ’ እያሉ የሚጠሯቸው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮችም፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 131ኛ የልደት በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል።
በተለይም ንጉሡ ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ጥቁር ዲያስፖራዎች ሻሸመኔ ላይ በሰጡት 500 ሄክታር መሬት ላይ በሚኖሩ ራስ ተፈሪያውያን ዘንድ ዕለቷ በደመቀ ሁኔታ ትታሰባለች።
በተለም ጃማይካ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አጼ ኃይለ ሥላሴ ይወደሳሉ፣ የሞዓ አንበሳ ምልክት ያለበት ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ይውለበለባል።
ኢትዮጵያ የተስፋይቱ ምድር እንደሆነች ይዘመራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘የፊውዳሉ ጨቋኝ?’ ‘ነጻ አውጭ?’
በሐረር፣ ኤጀርሳ ጎሮ ተወልደው ኢትዮጵያን መምራት ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቷ አጋፋሪ መሪም ሆነው ታይተዋል።
በታሪክ ፀሐፊያን ዘንድም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ካሉ መሪዎች የዓለም አቀፉን መድረክ እና ምናብ በመቆጣጠር ከፍተኛ ስፍራ ይሰጧቸዋል።
በታይም መጽሔት ሁለት ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ሰው የሚል ስያሜን አትርፈዋል።
ንግግሮቻቸው በሬጌ ዘፈኖች ተካትተው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ደርሰዋል።
ፎቶዎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ‘የቃል ኪዳኗ ምድር’ መግቢያ ነው ተብለው ለጥቁር ዳያስፖራው ተሰጥቷል።
በሕይወት ያሉ መሲህ፣ ፈጣሪ ተብለው ተሰግዶላቸዋል።
በርካቶች የሳቸውን ልብስ ለመንካት ተሻምተዋል፣ ሲያዩዋቸው አልቅሰዋል።
የምዕራቡ ዓለም ሚዲያም መነጋገሪያ ሆነዋል።
በተጓዙባቸው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ አገራት ያለ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በከፍተኛ አጀብ ተመልክቷቸዋል።
አገራት በስማቸው መንገዶች፣ ጎዳናዎች፣ትምህርት ቤቶች ሰይመውላቸዋል።
አጼ ኃይለ ሥላሴ በታሪካዊው የጃማይካ ጉብኝታቸው ለትምህርት ቤት የመሠረተ ድንጋይ ባስቀመጡባት ስፍራ በስማቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመዲናዋ ኪንግስተን ይገኛል።
ለአፍሪካ ነጻነት በተጫወቱት ሚናም ጁሊየስ ኔሬሬ በስማቸው በዛንዚባሯ ራስ ገዝ አስተዳዳር ስቶን ታውን ከተማም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸዋል።
በኬንያዋ ናይሮቢ እንዲሁም በዛምቢያዋ ሉሳካ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ጎዳናዎች አሁንም አሉ።
በጥቁሩ ዓለም ነፃ አውጭ፣ የአፍሪካ አባት፣ ቅኝ ገዢዎችን ያንበረከኩ፣ ፀረ ኢምፔሪያሊስት የሚል ስያሜን አትርፈዋል።
የፊውዳሉ ሥርዓት መሪ አጼ ኃይለ ሥላሴ የፊውዳልን ሥርዓት በጽኑ ይቃወሙ በነበሩ ጥቁር ግራ ዘመሞችም ዘንድ አንደ ተስፋ እና ነጻ አውጭ ተደርገው እንደተሳሉም የታሪክ ምሁሯ ጁሊያ ቦናቺ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይናገራሉ።
ጁሊያ ቦናቺ ራስ ተፈሪያን ወደ ኢትዮጵያ መመለስን አስመልክቶ ‘ኤክሶደስ፣ ሄይርስ ኤንድ ፓዮነሪስ ራስታፋሪ ሪተርን ቱ ኢትዮጵያ’ (Exodus! Heirs and pioneers, Rastafari return to Ethiopia) የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ ናቸው።
በኢትዮጵያ ባለው ገጽታቸው በአንድ መልኩ ሥርዓተ መንግሥቱን ወደ ተማከለ አስተዳደር በማምጣት፣ ትምህርትን በማስፋፋት፣ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርትን በማስጀመር ዘመናዊ እና ተራማጅ ነበሩ ይባላሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ባላባቶች፣ ጭቃ ሹም እና መኳንንቱ አርሶ አደሩን ከሰው በታች አውርደው እያንገላቱ በገዙበት፣ በባርነት፣ በርካቶች በድህነት እና በጭቆና የሚማቅቅበት ሥርዓት ዋና አጋፋሪ ናቸው በማለትም ይወቀሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእርሳቸው ሥርዓት ትግራይ እና ወሎ ተርበው በመቶ ሺዎች አልቀዋል።
ንጉሠ ነገሥቱ በወሎ ረሃብ በርካቶች በምግብ እጦት እና በጠኔ ሲረግፉ እርሳቸው 80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለማክበር ሚሊዮን ዶላሮችን አውጥተዋል ሲሉም ዶክተር ዮሐንስ ወልደማርያም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተችተዋቸዋል።
የልጅነት ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ ያሳለፉት እና ጭቆናውን አይተው ላደጉት ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ዶክተር ዮሐንስ ወልደማርያም በጥቁሩ ምናብም ሆነ በዓለም ላይ እየተሳሉበት ያለው ገጽታ ሊቆም ይገባል ሲሉም ይከራከራሉ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህንን በተመለከተ ‘ዘ ሮማንቲክ ሪራይቲንግ ኦፍ ኃይለ ሥላሴስ ሌጋሲ መስት ስቶፕ' የሚል ጽሑፍም አቅርበዋል።
የተነሳባቸውን አመጽ ሁሉ በኃይል ለመመለስም ጥይት አዝንበዋል የሚሏቸው ኃይለ ሥላሴ፣ ከሚጠቀሱትም ውስጥም የጎጃም፣ የባሌ እና የትግራይ የአርሶ አደሮች አመጾችን ነው።
በትግራይ የተነሳባቸውን ተቃውሞም ለመደምሰስ ከብሪታንያው ሮያል አየር ኃይል ጋር በመተባበር የአየር ጥቃት መፈጸማቸውን የታሪክ ድርሳናት መዝግበውታል።
ዶክተር ዮሐንስም ይህንን አንዱ የጭካኔ ማሳያ አድርገው የሚያነሱት ነው።
ለሥልጣን የሚቀናቀኗቸውን ለማስወገድ የጭካኔ በትራቸውን ያነሳሉ የሚሏቸው ኃይለ ስላሴ “ልጅ እያሱን መስዋዕት አድርገው ነው ወደ ሥልጣን የመጡት” ይሏቸዋል።
መፈንቅለ መንግሥት ሞክረዋል የተባሉትን መንግሥቱ እና ገርማሜ ንዋይን በስቅላት መገደላቸው፣ እንዲሁም የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎችን ለመቅጣት በሚል የተፈጸሙ ግድያዎችን ይጠቅሳሉ።
የአጼ ኃይለ ሥላሴ ገጽታ በተቃርኖ የተሞላ ነው።
አፈታሪኮች፣ እምነቶች፣ ውክል እና ብዙ ሁነቶችም የተቀላቀሉበት ነው።
ሆኖም በሥርዓታቸው ላይ የሚነሱ ወቀሳዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላቸውን ገጽታ አላጠለሸውም።
“ውክልናው እና እውነታው የተለያዩ ነገሮች ናቸው” የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ የሚባሉትን “ነጻ አውጪ፣ የጥቁር መብት ተሟጋች” ሳይሆኑ ትከክለኛ ገጽታቸው “አምባገነን መሆናቸው” ሊነገር ይገባል ሲሉም ለቢቢሲ ያስረዳሉ።
የአንዱ ነጻ አውጪ ለሌላኛው ጨቋኝ መሆን የተለያዩ የታሪክ ታላላቆች እውነታ ቢሆንም የኃይለ ሥላሴን ያህል ግን የታሪክ እንቆቅልሽ የሆነ እንደሌለ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታን በጥቂቱ
በርዕዮተ ዓለም እና በአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ተከፋፍለው የነበሩትን አዲሶቹን መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ቀላል አልነበረም።
በተለይም ጉዳዩን አወዛጋቢ ያደረገው በወቅቱ የሞኖሮቪያ አባል የነበሩት የቶጎው መሪ መገደል ያኛውን ቡድን መወንጀል እና ሁኔታዎችም መካረር ጀመረ።
በርካታ ነገሮችንም ለማለሳለስ እና ለዚህ ጉባኤ ስኬት ዋነኛው የአጼ ኃይለ ሥላሴ ቀኝ እጅ የነበሩት በንጉሡ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ያገለገሉት አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ።
አቶ ከተማ፣ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸውን ዝና እና ክብርን በመጠቀም ነው እነዚህን መሪዎችን ማሰባሰብ የቻሉት።
በዚህም ጉባኤ ላይ ነጻ ላልወጡ አገራት የአፍሪካ የነጻነት እንቅስቃሴ (አፍሪካን ሊበሬሽን ሙቭመንት) እንዲመሠረት ተወሰነ።
በመጨረሻም በ32 አባል አገራት በጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25 ቀን 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመሥረት ተጠናቀቀ።
“ያለፉ የፍትሕ መጓደል ትዝታዎች አሁን ካለንበት ጠቃሚ ምዕራፍ ሊያዘናጋን አይገባም። የጥላቻ አሲድ ነፍሳችንን እንዳይሸረሽር እና ልባችንን እንዳይመርዝ ቂም በቀልን በመተው ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻችን ጋር በሰላም መኖር አለብን” ሲሉም ኃይለ ሥላሴ በምሥረታው ወቅት ተናገሩ።
ንክሩማህ ይህ ሁሉ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በተለይም በአዲስ አበባ በነበራቸው አስደሳች እና የማይረሳ ቆይታ ከልብ የመነጨ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ለማጠቃለያም በጋናዊ ገጣሚ ለኢትዮጵያ ክብር የተጻፈች ግጥም ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አነበቡላቸው።
ግጥሙም “ኢትዮጵያ ትነሳለች፣ የአፍሪካ ብሩህ ዕንቁ፣ በለመለመ ኮረብታዎች መካከል ከፍ ያለች
መቼም የማይነጥፈው የአባይን ወንዝ (የናይል ወንዝ) የወለደች
ኢትዮጵያ ትነሳለች፣ ኢትዮጵያ፣ የጥበብ ሃገር
ኢትዮጵያ፣ የጥንታዊ የአፍሪካ ጀግንነት አገዛዝ መገኛ፣ የአፍሪካ ባህል ትምህርት ቤት
ኢትዮጵያ፣ ጥበበኞች ይነሱብሻል። የአፍሪካን ተስፋ እና ዕጣ ፈንታንም እንደገና ያሰርጻሉ” አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በጥቁሮች ምናብ
ለተወሰኑ ማኅበረሰቦች ኢትዮጵያ እና ነገሥታቶቿ የግፍ ምንጭ፣ በደሎች፣ ግዛት ለማስፋፋት እና ሕዝብ ለማስገበር ጭፍጨፋዎችን የፈጸመች እንዲሁም ባርያዎችን በሕይወታቸው የቀበረች ናት።
ለሌሎች ደግሞ የሥልጣኔ መነሻ፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ የጥበቦች መዳረሻ ለነጮች ያልተንበረከከች፣ የራሷ ፊደል እና የቀን መቁጠሪያ ያላት፣ የበርካታ ድንቅ ባህሎች መዳረሻ ናት።
ለተለያዩ ማኅበረሰቦች የተለያየ ገጽታ ነበራት ብለው የሚቀበሉት ያሉትን ያህል እንደ ራስ ክዊንታሰብ ላሉት ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የተቀደሰች አገር በመሆኗ ‘በጫማም’ ለመርገጥ የሚሳሱላት ናት።
የካሪቢያኗ ደሴት ትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ ተወላጁ እና ኃይለ ሥላሴ የሙዚቃ ማዕከላቸው የሆነው የሬጌው ሙዚቃ ተጫዋቹ ራስ ክዊንታሰብ፣ አገሬ ወደሚሏት ኢትዮጵያ ከመጡ እርሳቸው እንደሚሉት ‘ከተመለሱም’ 27 ዓመታትን ደፍነዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ስሟ ተደጋግሞ የተነሳው እና ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች’ የተባለላት ኢትዮጵያ ለራስ ተፈሪያን የቃል ምድር፣ ጽዮን ናት።
ራስ ክዊንታሰብ ከቢቢሲ ጋር በስልክ ባደረጉት ዘለግ ያለ ቆይታ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሲናገሩ ዋቢ የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስን ነው።
ስለ ኢትዮጵያ ‘የተስፋዋ ምድር’ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት ልጅ እያሉ ነበር።
ህጻን እያሉ ኢትዮጵያ የተጠቀሰችበትን የግሪክ አፈታሪክ መጽሐፍ አነበቡ።
መጽሐፉ የግሪክ አማልክት ከሰዎች ጋር መዝናናት ሲፈልጉ ወደተመረጠችው ኢትዮጵያ ጎራ ይላሉም ይላል።
የልጅነት አዕምሯቸውም ትክክለኛ ስፍራ አልመሰላቸውም።
አጼ ኃይለ ሥላሴ በታሪካዊው የካሪቢያን ደሴቶች ጉብኝታቸውም የእሳቸው ትውልድ ቦታ ወደሆነችው ትሪንዳድ እና ቶቤጎ መጡ።
በወቅቱ ልጅ የነበሩት ክዊንታሰብ በጋዜጣ ላይ የአጼ ኃይለ ሥላሴን ፎቶ ተመለከቱ።
በነጭ ፈረስ ላይ ከሚታዩት ኃይለ ሥላሴ ፎቶ ስርም ‘ታላቁ የአፍሪካ ንጉሥ’ የሚል ተጽፎበት ነበር።
ከዚያን ጊዜም ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ ቃል የተገባላት የተስፋይቱ ምድር፣ አጼ ኃይለ ሥላሴም አምላክ መሆናቸው መነሻ እንደሆናቸው ያስረዳሉ።
በፈረንሳይ 'ኢንስቲትዩት ኦፍ ሪሰርች ፎር ሰስቴይነብል ዴቨሎፕመንት' በተሰኘ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ጁሊያ ለበርካታ ዓመታትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርተዋል።
ለታሪክ ተመራማሪዋ የኃይለ ሥላሴ በዓለም አቀፉ ያላቸው ገጽታም ሆነ ዋነኛው መነሻ ኢትዮጵያ የነበራት ስፍራ ነው።
ጥቁር ዓለም ተብሎ በሚጠራው ዘንድ ኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ስለነበራት እና የትግል ተምሳሌት መሆኗም ነው። እንዲሁም ሉዓላዊነትን ወክላ መታየቷ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የሰው ልጆች እንደ ሸቀጥ በተሸጡበት እና በተለወጡበት፣ አፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቿን በባሕሮች በገበረችበትወቅት ኢትዮጵያ እንደ ተስፋ መታየቷ መጠቀስ አለበት ይላሉ።
ለዚያም ነው የታሪክ ተመራማሪዋ በምዕራቡ ዓለም በጥቁሮች የተመሠረቱ ጽዮን፣ አቢሲኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ምኒልክ የሚሉ ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት የተሰየሙት ይላሉ።
በዚህ የታሪክ ማማ ላይ ነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሥልጣን የመጡት።
ዶክተር ዮሐንስም ቢሆኑ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰች መሆኗ፣ በቅኝ ያልተገዛች እንዲያውም አውሮፓውያኑን ያሸነፈች አገር መሆኗ፣ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ባይኖሩም የአድዋ አሻራ እንደተከተላቸው ይጠቅሳሉ።
“አንድ ጥቁር ኃይል መብቱን ለማስከበር አድዋ ላይ ተዋግቶ፣ አሸንፎ፣ አሳፍሮ ላካቸው ይሄም ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ጠቅሟቸዋል። የእሳቸው ማንነት ሳይሆን የነበረው ታሪካዊ ሁኔታ ተጠቃሚ አደረጋቸው። ማንነታቸው ቢታወቅ ኖሮ ብዙ ሰው የሚያደንቅበት ላያገኝ ይችላል” ይላሉ።
ጥቁሩ ዓለም በጭቆና በሚማቅበት ወቅት “ሁሉንም ሊያነቃንቅ የሚችል አንድ ተወካይ እና ምልክት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበር። እናም ኢትዮጵያ የምትባል አገር እና አጼ ኃይለ ሥላሴን አገኙ” ሲሉም ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኃይለ ሥላሴ በዓለም አቀፉ ምናብ
ኃይለ ሥላሴን በጥቁሩ ዓለም ምናብ ከፍ ያለ ስፍራ ውስጥ የሚያስቀምጧቸውም በርካታ ክስተቶች አሉ።
የታሪክ ተማራማሪዋ ከሚጠቅሷቸው አንዱ በጎሮጎሪዮሳውያኑ 1920ዎቹ የባርነት ሥርዓት መወገድ ነው።
የዓለም መንግሥታት ኅብረት የሆነውን ሊግ ኦፍ ኔሽንን ለመቀላቀል አንደኛው የተቀመጠው መስፈርት በአገሪቷ ውስጥ የነበረውን የባርያ ፍንገላ ሥርዓትን ማስወገድ ነበር።
ጁሊያ እንደሚሉት ይህ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫን የቀየረ ብቻ ሳይሆን በባርነት ለመጡ እና በቅኝ ግዛት ስር እየማቀቁ ለነበሩ” ተስፋ የሚያንጸባርቅ ነበር።
ኢትዮጵያም ከሌሎች የመንግሥታት ስፍራ ተቀመጠች።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ባርነትን ለማስወገድ አዋጅ ብታወጣም በሕጋዊ መንገድ ሙሉ በሙሉ የታገደው በአውሮፓውያኑ 1942 ነበር።
አጼ ኃይለ ሥላሴ ለጥቁሮች መብትም ሆነ አፍሪካውያን ነጻ እንዲወጡ የተጫወቱት ሚናም የለም የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ እንዲያውም የባሪያ ፈንጋይ ሥርዓትን ለማስወገድ ፈቃደኛም አልነበሩም ሲሉ ይተቻሉ።
ለዚህም አንደኛው የሚያነሱትም የጃማይካዊው መብት ተሟጋች ጋርቬይ “የባሪያ አሳዳሪ ናቸው” ብሎ የተቻቸውን ነው።
ኢትዮጵያ የተወሰኑትን የራሷን ሕዝቦች በባርነት እየሸጠች እና እየለወጠች እንዴት የነጻነት ተምሳሌት ትሆናለች ብለውም የሚጠይቁ አለ።
ሌላኛው ጁሊያ የሚጠቅሱት ደግሞ በ1920ዎቹ መጀመሪያ ኃይለ ሥላሴ ከአንዳንድ ጥቁር ተቋማት ጋር ግንኙነት መመሥረታቸውን ነው።
በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ዘውድ ስም ደብዳቤዎች ስለመጻፋቸው የሚያሳዩ ምንጮች እና የታሪክ ማኅደሮች እንዳገኙ የታሪክ ምሁሯ ይናገራሉ።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የጥቁር ብሔርተኛ ድርጅት ተብሎ የሚጠቀሰውና በማርከስ ጋርቬይ የተቋቋመው universal Negro improvement Association (UNIA) አንዱ ነው።
ሌላኛው የዓለምን ምናብ የተቆጣጠረው ብለው የሚያነሱት የአጼ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ሲመት ነው።
መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት የአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘውድ መድፋታቸው የጥቁር አፍሪካ ሉዓላዊ ፖለቲካዊ ኃይል መወከያም አድርጓቸዋል ይላሉ።
የንግሥና ሲመቱም ናሺናል ጂኦግራፊክን ጨምሮ አሉ በሚባሉ ሚዲያዎች ፎቶዎች መውጣታቸውም በጥቁሮች ምናብም ሆነ በመላው ዓለም የራሱን ሚና ተጫውቷል ይላሉ።
ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዘ እምነገደ ይሁዳ፣ ስዩመ እግዚአብሔር፣ ተብለው በጎሮጎሪዮሳውያኑ ኅዳር 02/1930 ተሰየሙ።
ጃማይካዊው ፖለቲከኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማርከስ ሞሳያህ ጋርቬይ ከሲመታቸው በፊት “ጥቁር ንጉሥ ዘውድ ሲቀዳጅ በአፍሪካ ተመልከቱ። የመዳን ቀን ቀርቧል” በሚልም ተናግሮ ነበር።
ከአጼ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ እና ሥርዓት ጋር ተያይዞ የጋርቬይ ንግግር እንደ ትንቢት መፈጸሚያ ታየ።
በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ለነበሩም ነጻ የመውጫ ቀን መድረሱ ተነገረ።
ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች የንግሥናውን ሲመት ፎቶዎች ይዘው ወጡ።
ከዓለም መሪዎች ስጦታ ጎረፈ።
ለራስ ኩዊንታሰብም ሆነ ለሌሎች ራስ ተፈሪያን ይህች ቀን አምላክ በሥጋ የተገለጠባት ዕለት ናት።
በዚህ ወቅትም ነበር መጽሐፍ ቅዱስ እና የአጼ ኃይለ ሥላሴን የንግሥና ሥርዓት የሚያሳዩ ፎቶዎች በጃማይካ መታየት የጀመሩት።
ከሰለሞን ስርወ መንግሥት ዘራቸው የሚመዘዝ፣ አፍሪካዊ ራስ ተፈሪ የሚባሉ አምላክ አሉ ተባሉ።
የመጀመሪያው ራስ ተፈሪያን እየተባለ የሚጠራው ሰባኪው ሌናርድ ሃውል ከፍተኛ ዕውቅና ማትረፍ ቻለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የራስ ተፈሪያኒዝም እንቅስቃሴ በቅኝ ገዥዋ ብሪታንያ በቀላሉ ሊታይ አልቻለም።
ሆኖም ሌናርድ የቅኝ ገዥዎቹን ትዕዛዝ በመጣስ ኃይለ ሥላሴ አምላክ በሥጋ የተገለጠበት ነው አለ።
ጃማይካውያንንም የብሪታንያ ተገዢዎች አድርገው እንዳያዩም መከረ።
እናንተ ኢትዮጵያውያን ናችሁ አለ።
ኃይለ ሥላሴ ፈቃደኛ የሆኑ ጃማይካውያንንም ቃል ወደተገባላቸው የኢትዮጵያ ምድር ለመውሰድ መርከብ አዘጋጅተዋል ሲልም ለሕዝቡ ነገረ።
አምስት ሺህ የሚሆን የአጼ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ሲመት ፎቶዎችም ታተሙ።
እነዚህ ፎቶዎች ጽዮን ብለው ለሚጠሯት ኢትዮጵያ መግቢያ እንደ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት) እንደሚያገለግልም ለተከታዮቻቸው ተነገረ።
በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት መሠረት ሌሎች ክርስቲያኖች የኢየሱስን ዳግም መምጣት ቢጠባበቁም ለራስ ኩዊንታሰብም ሆነ ለራስታዎች ኃይለ ሥላሴ “(‘jesus reincarnate) ኢየሱስ ራሱን የገለጠባቸው” ናቸው።
ሌላኛው በዓለም አቀፉ ዘንድ ሰብዕናቸው ከፍ ብሎ እንዲወከሉ ያደረጋቸው ለታሪክ ምሁሯ የጣሊያን ወረራ ነው።
ዶክተር ዮሐንስም ቢሆኑ የጣሊያኖች ወረራ እና ያደረሱት ግፍ ንጉሡ ከፍ ያለ ስፍራ አሰጥቷቸዋል ይላሉ።
ክዋሜ ንክሩማህ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በአሜሪካ እየተማሩ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያን መወረር ሲሰሙ “ባቡር ላይ ነበርኩ እናም አለቀስኩ” በማለት መጽሐፋቸው ላይ መጥቀሳቸውንም ያወሳሉ።
ንጉሡ የፋሺስት ወረራውን ለመታገል ከፊት ሆነው መጡ።
መላው ጥቁርም ወረራውን ተቃወመ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያን ከዚህ ወረራ መከላከል እንዲቻልም በርካታ ፀረ ፋሽስት እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ።
ለኢትዮጵያ ጉዳይም የተነሳ ትልቁ ንቅናቄ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ሲሉ ነው የሚጠሩት የታሪክ ባለሙያዋ።
የጥቁሮች የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ መወረር ጥቁሮች እንደተወረሩ ተደርጎ ተቆጠረ።
ትግሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካን ትግል ተደርጎም ተወሰደ።
በጣሊያን አምስት ዓመቱ ወረራ ወቅት ኢትዮጵያን ለመደገፍ የአጼ ኃይለ ሥላሴ የግል ሐኪም በነበሩት ዶክተር መላኩ በያን እና በአፍሪካን አሜሪካውያን የተመሰረተውም Ethiopian World Federation (ኢደብልዩ ኤፍ)ም አንዱ ነበር።
አጼ ኃይለ ሥላሴ የመንግሥታቱ ማኅበር - ሊግ ኦፍ ኔሽን አባል የሆነችው አገራቸው በሌላ አባል በጣልያን መወረሯን አገራቱ ለመተባባር የገቡትን ጽንሰ ሃሳብ በጽኑ የሚጥስ ነው ብለው አጥብቀው ተቹ።
“ሕዝቤ በመርዝ ጋዝ እያለቀ ነው” አሉ። ፋሺስዝምንም አወገዙ።
በዚህም ወቅት ነው ታይም መጽሔት የዓመቱ ምርጥ ሰው ሲል የሰየማቸው።
ኃይለ ሥላሴም በእንግሊዟ ባዝ ከተማ ለግዞት ተዳረጉ።
ምንም እንኳን እንደነ ማርክስ ጋርቬይ የስደቱን ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ የተቹት ቢኖሩም ለአገራቸው ድምጽ ለመሆን እና ድጋፍ ለማሰባሰብ ረድቷቸዋል የሚሉ አልታጡም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአምስት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ በብሪታንያ ድጋፍ ከጭቆና እና ጭፍጨፋ ነጻ ወጣች።
በዓለም ላይ ካሉት ድሃ አገራት መካከል አንዷ ሆና የአውሮፓ ኃያልን አገር ባለ በሌላ መሳሪያዋ እንዴት አሸንፋ፣ ነጻነቷን አስጠበቀች የሚለውም ለራስ ኪውንታሰብ እና በሌሎችም ዘንድ እንደ ተዓምር የሚታይ ነው።
“የአፍሪካውያን ነጻነት ያነሳሳው የኢትዮጵያውያን ድል ነው” ይላሉ ክዊንታሰብ።
“በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን እንኳን እምነት፣ ድፍረት እና ፍትሃዊ ምክንያትን ከያዘ ዳዊት አሁንም ጎልያድን ያሸንፋል” ሲሉም ኃይለ ሥላሴ ተናገሩ።
ኃይለ ሥላሴ ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ መጓዛቸው፣ በዓለም አቀፉ ምናብ ላይ የራሱን ሚና እንደተጫወተ ጁሊያ ይጠቅሳሉ።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ እርሳቸው በርካታ ጉብኝቶችን ያደረገ የአፍሪካ መሪ አልነበረም።
ኃይለ ሥላሴ በአገር ውስጥ “መሬት ለአራሹ” እንቅስቃሴ ተቃውሞ በቀጠለበትም ወቅትም እንኳን በዓለም አቀፉ መድረክ የተከበሩ መሪነታቸው ተጠናክሮ ቀጠለ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፍራንሲስ ቻርለስ ደጎል ቀብር ላይ ተከብረው ፊት ለፊት ከተቀመጡ መሪዎች አንዱ ነበሩ።
በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ መቶ ሚሊዮኖች ዶላር ወጥቶበታል (ቢሊዮን ዶላር ፓርቲ) ተብሎ በሚጠራው የፋርስ 2500 ስርወ መንግሥት ሲከበርም የኢራኑ ሻህ መሐመድ ረዛ ፓህላቪ ከጋበዟቸው አንዱ ናቸው።
ነጻ የሆኑ የአፍሪካ አገራትን መጎብኘት፣ የሰላም ማስከበር ጉባኤዎች፣ የልማት ዕርዳታ ማሰባሰቢያዎች ላይ በክብር ከሚጋበዙት መካከል አጼ ኃይለ ሥላሴን የሚስተካከል አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Life Magazine
የአጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪካዊው የካሪቢያን ደሴቶች ጉብኝት
አጼ ኃይለ ሥላሴ እንደ አምላክ ወደሚታዩባት ጃማይካ ሲያቀኑ የነበረው ስሜት ለየት ያለ ነበር።
ኃይለ ሥላሴ ሚያዝያ 13/1958 ዓ.ም በጃማይካ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሱ።
ሲያዩዋቸው ያለቀሱ፣ ልብሳቸውን ለመንካት ሽሚያ ነበር።
እጃቸው ላይ ኢየሱስ እንደተሰቀለበት የችንካር ምልከት ታይቷል ተባለ።
ጃማይካ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጉብኝት አራት ዓመታትን ቀድማ ነው ነጻነቷን ያገኘችው።
የብሪታንያን እሴት አንቅሮ የተፋው የራስ ተፈሪያኒዝም እንቅስቃሴ ለብሪታንያ ተቀባይነት አልነበረውም።
የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ብሪታንያም ሆነ እንደ አዲስ ለተቋቋመው የጃማይካ መንግሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ጃማይካ ቢመጡም እንቅስቃሴውን ሊገታው ይችላል የሚል እሳቤ እንደነበር ጁሊያ ይናገራሉ።
“አምላክ የሚሉትን ይህንን ግለሰብ አጠር ያለ ጠይም ሰው መሆኑን ሲያዩ ነገሮች ይቀየራሉ” የሚል ነበር።
ነገር ግን የተገላቢጦሽ ተፈጠረ።
ጉብኝታቸው የራስታ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ አዲስ ጉልበት፣ አዲስ መንፈስ ሰጠው።
የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ በማዋቀር ትልቅ ሚና ነበረው።
“ጉብኝቱን እንደ ጥምቀት ልናየው እንችላለን። አምላክ በምድር ላይ የተገለጠበት” ተብሎ እንደሚታመን ይናገራሉ።
ኃይለ ሥላሴስ እነዚህን አገራት ለምን ለመጎብኘት መረጡ?
ጁሊያ እንደሚሉት ኃይለ ሥላሴ ፓን አፍሪካዊ የሆነ ዓላማ ነበራቸው።
አንደኛው የመረጡት ወቅት አገራቱ ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎቻቸው ነጻ ከወጡ በኋላ ነው።
በወረራው ወቅት ጥቁሩ ሕዝብ አቤቱታ በማስገባት እንዲሁም በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምሥጋናቸውን ለመስጠት ነበር።
በወቅቱ በቅኝ ግዛት ውስጥ ሆነውም ኢትዮጵያን ለመደገፍ በጦርነት ሊዘምቱም ባለመቻላቸው ጋዜጦችን በማሳተም ድምጻቸው እንዲሰማ በማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
በርካታ ጥቁር ነዋሪዎች ያሉባቸው እነዚህ አገራት ታማኝነታቸውን ለብሪታንያ የነገሥታት ቤተሰብ ሳይሆን ለኢትዮጵያው ዘውድ መሆኑም የራሱ መልዕክት ነበረው።
በቅኝ ግዛት፣ እንዲሁ ድኅረ ቅኝ ግዛትም በድህነት ሲማቅቅ የነበረው ሕዝብም ብሪታንያን አንቅሮ መትፋቱ ለብሪታንያም ሆነ ለነጻው የጃማይካ መንግሥትም እንዲሁ በቀላሉ የሚያዩት አይደለም።
የራስታ እንቅስቃሴንም በኃይል ለመግታት በአስገዳጅ ሁኔታ ፀጉራቸውን መላጨት፣ እስር፣ ግድያ፣ ስወራ ሌሎች የጭቆና መንገዶች ቀጥለው ነበር።
ራስ ክዊንታሰብ እንደሚናገሩት ለዘመናት ራስታዎች ሥራ አለማግኘት ዘብጥያ መውረድ እና ሌሎች መከራዎችን አስተናግደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Life Magazine
ሬጌ ሙዚቃ እና ኃይለ ሥላሴ
አጼ ኃይለ ሥላሴንም ሆነ ኢትዮጵያን ከስም በላይ ስም እንዲኖራቸው ያደረገ እንደ ሬጌ ሙዚቃ የለም።
ስለ አጼ ኃይለ ሥላሴ መሲህነት፣ ነጻ አውጭነት፣ ባቢሎን ብለው የሚጠሩት የምዕራባውያኑ ዓለም መበስበስ እንዲሁም ቃል ወደተገባላት ምድር - ጽዮን መመለስ ሌላም ሌላም መልዕክቶችን የሰሙት በሬጌ ሙዚቃ እንደሆነ ክዊንታሰብ ይናገራሉ።
ሩቅ በሚመስሉ እንደ ኢንዶኔዢያ ባሉ አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬጌ ባንዶች እንዲኖሩ ሙዚቃው የፈጠረው ተጽእኖ ማሳያ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የታየው ኢንዶኔዢያዊ ሙዚቀኛ ኢትዮጵያውያን በሚጠሩበት ራስ ሙሐመድ ስለ ኃይለ ሥላሴ ማውራት የሚያስደንቅ ሊመስል ይችላል።
ከካሪቢያን ወጥቶም በአውሮፓ እንደ ጀንትል ማን ያሉ ነጭ የሬጌ ሙዚቀኞች፣ እንዲሁም የራስ ተፈሪያኒዝም ዕምነት ተከታይ ነጮችንም በኢትዮጵያ ማየት የተለመደ ነው።
የሬጌ ሙዚቃን ከፍ ወዳለ ስፍራ በማሻገርም በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበረው ቦብ ማርሌይ ተወዳዳሪ ያለው የለም።
ቦብ ማርሌይ በአውሮፓውያኑ በ1963 ኒው ዮርክ ተካሂዶ በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ኃይለ ሥላሴ አድርገውት የነበረውን ንግግራቸውን ‘ዋር’ በሚለው ዘፈኑ ውስጥ አካትቶታል።
“እንዲሁም የዘር ልዩነትን በሚመለከት አንዱ ዘር ከሌላው ዘር ይበልጣል፣ ይሻላል የሚለው እምነት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ ካልተወገደ….” ሰላም አይመጣም የሚለው ድምጻቸው ገብቷል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም እንደ ቴዲ አፍሮ ያሉት ሙዚቀኞችም ‘ጃ ያስተሰርያል’ በሚለው ሙዚቃው ለአጼው ያለውን ክብር ጠቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ ሕዝቧ በረሃብ የረገፋባት፣ ጭቆና የተንሰራፋባት፣ ይህ ነው የሚባል መሠረተ ልማት ያልነበራት አገር እና በድህነት ከዓለም ጫፍ የተቀመጠች ናት ይላሉ ዶክተር ዮሐንስ።
ኃይለ ሥላሴ ለአገሪቱም፣ ለጥቁር ሕዝብም ምንም ፋይዳ ያለው ሥራ አላከናወኑም የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፣ በመላው ዓለም የተሳሉበት ገጽታ ትክክል አይደለም ሲሉም ይሞግታሉ።
አጼ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያም ሆነ እሳቸው በነበራቸው እውቅና “መራብ ሳይሆን ከፍተኛ ዕድገት ላይ መድረስ ይቻል” እንደነበር በመጥቀስ “ለንጉሡ ያልሆኑትን ስም መስጠት እና ማጀገን እና ማድነቅ ተገቢ አይደለም” ይላሉ።
የኃይለ ሥላሴ የግዛት ዘመን በጣም ረጅም፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ክስተቶች የተስተናገደበት ከመሆኑ አንጻር ገጽታቸውም ሆነ ታሪካቸው ይህንን ውስብስብ ሂደት የሚያሳይ ቢሆን ጥሩ ነው ሲሉም ጁሊያ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።












