ዝነኛው አሜሪካዊ ድምጻዊ ጀስቲን ቲምበርሌክ በ'ላይም' በሽታ መያዙን ይፋ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጀስቲን ቲምበርሌክ ላይም በተሰኘ በሽታ መያዙን ይፋ አደረገ።
የ 44 ዓመቱ አሜሪካዊው ድምጻዊ የምርመራ ውጤቱን ሲሰማ "በጣም ደነገጥኩ" ብሏል።
ነገር ግን ከሕመሙ ጋር እየታገለ የመድረክ ሥራዎቹን ማቅረቡን ሲገልጽ "በመድረክ ላይ ከፍተኛ በሆነ የነርቭ ሕመም ወይም ከፍተኛ ድካም እና ሕመም ይሰማኝ ነበር" ብሏል።
ክራይ ሚ ኤ ሪቨር (Cry Me A River) በሚለው የሙዚቃ ስራው የሚታወቀው ቲምበርሌክ 'ፎርጌት ቱሞሮው' የተሰኘውን ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ድግስ ማጠናቀቁን አስመልክቶ በኢንስታግራም ገፁ ላይ የምርመራ ውጤቱን ይፋ አድርጓል።
ላይም የተባለው በሽታ በባክቴሪያ የሚመጣ ኢንፌክሽን ሲሆን ወደ ሰው በመዥገር ንክሻ ሊተላለፍ ይችላል።
በሽታው እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠ እና ሕክምና የወሰዱ ጥቂት ሰዎች እንደ ድካም፣ ሕመም እና ጉልበት ማጣት ያሉ ለዓመታት የሚቆዩ ምልክቶችን ሊታዩባቸው ይችላል።
ቲምበርሌክ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየተዟዟረ የሚያቀርበውን የሙዚቃ ስራ ቀደም ብሎ ለማቆም ፈልጎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ለመቀጠል መወሰኑን ተናግሯል።
ሐሙስ ዕለት በኢንስታግራም ገፁ ላይ "ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት እኔ በጣም ግላዊነት የሚያመዝንብኝ ሰው ነኝ። ነገር ግን በሙዚቃ ስራዎቼ እና ፌስቲቫሎቹ ምን ይመስሉ እንደነበር መለስ ብዬ ስመለከት ምን እየተፈጠረ እንደነበር ትንሽ ላካፍላችሁ ወደድኩ።"
"ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደምሮ፣አንዳንድ የጤና ጉዳዮችን እየታገልኩ ነበር፤ እናም የላይም በሽታ እንዳለብኝ በምርመራ ታውቋል።በዚህ ስለ እኔ ሐዘኔታ እንዲሰማችሁ አይደለም። ነገር ግን ከመጋረጃ በስተጀርባ ያጋጠመኝን ትንሽ ብታውቁት በሚል ነው።
"በዚህ በሽታ ከተያዛችሁ ወይም የታመመ ሰው የምታውቁ ከሆነ፤ ከበሽታው ጋር መኖር አእምሮም ሆነ አካልን ያለማቋረጥ እንደሚያዝል ተረዱ።"
የአሜሪካ የበሽታ እና ቁጥጥር እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) እንደገለጸው፣ በኢንፌክሽኑ መያዙ የታወቀ ሰው ወድያውኑ ፀረ ባክቴሪያ ሊሰጠውና በአብዛኛው በፍጥነት እና ሙሉ በሙሉ ሊያገግም ይችላል።
ዘግይተው የሚታከሙ ግን ለፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ጥሩ ምላሽ ቢሰጡም አንዳንዶች ግን በነርቮቻቸው ወይም በመገጣጠሚያዎች ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳት ያጋጥማቸዋል።
ጀስቲን ቢበር፣ ሻኒያ ትዌይን እና አቭሪል ላቪኝ በላይም በሽታ መያዛቸውን ይፋ ካደረጉ ታዋቂ ድምጻውያን መካከል ይገኙበታል።
ነገር ግን ቲምበርሌክ "በመድረክ ላይ ስራዎቼን ማቅረብ የሚሰጠኝ ደስታ" ሰውነቱ ከተሰማው ጭንቀት እንደሚበልጥ እና "ስራዎቼን ማቅረብ በመቀጠሌም ደስ ብሎኛል" ብሏል።
የሙዚቃ ስራውን ለሁለት ዓመት በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ማቅረብ የጀመረው በሚያዝያ 2024 ሲሆን፣ ይህም ረቡዕ ዕለት በቱርክ ፍጻሜውን አግኝቷል።
"የአእምሮ ጥንካሬዬን ለራሴ ማረጋገጤ ብቻ ሳይሆን፣አሁን ከሁላችሁም ጋር የማልረሳቸው ብዙ ልዩ ጊዜዎች አሳልፌያለሁ" ሲል ያጋጠመው የጤና እክል "በተሳሳተ መልኩ እንዳይተረጎም" የበለጠ ግልፅ ለመሆን እየሞከረ መሆኑን ተናግሯል።
እውቁ አሜሪካዊ ድምጻዊ ጀስቲን ቲምበርሌክ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በሙዚቃ ድግሶቹ ላይ አንዳንድ አድናቂዎቹ ከሚጠብቁት በታች ሆነው እንዳገኙት በመግለጽ ትችት ሲያቀርቡ ነበር።
የቲምበርሌክ የጤና ምርመራው ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በመስከረም 2024 ጠጥቶ ሲያሽከረክር ተገኝቶ በተመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
በወቅቱ "የሠራሁት ስህተት ነው፤ ነገር ግን ይህንን የሚመለከት እና የሚያዳምጥ ሁሉ ከዚህ መማር እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ. . . " ሲል ተናግሯል።
የድምጻዊው የቀድሞ ፍቅረኛ፣ ብሪትኒ ስፒርስ ስለነበራቸው ግንኙነት በመጽሐፏ ላይ በዝርዝር ካሰፈረች እና እርሱን ተከትሎ በቀረበው ዘጋቢ ፊልም ላይ ከተናገረች በኋላ ከአድናቂዎቹ ቅሬታዎችን አስተናግዷል።
የኤንሲንክ (NSYNC) ቡድን አባል የነበረው ቲምበርሌክ 10 ግራሚዎችን በማሸነፍ እና በርካታ ቅጂዎችን በመሸጥ ዝናን አትርፏል።
ጀስቲን ቲምበርሌክ ከተዋናይት ጄሲካ ቢኤል ጋር ትዳር መስርቷል።















