የአየር ጥቃቶችን ተከትሎ የእርዳታ ድርጅቶች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሥራ ማቋረጣቸው ተገለጸ

እርዳታ የሚቀበሉ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሰሜን ምዕራብ ትግራይ 56 ሰዎች በአየር ጥቃት ተገድለዋል መባሉን ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በአካባቢ የሚያደርጉትን የረድኤት ሥራ ማቋረጣቸውን ተገለጸ።

ባለፈው ዓርብ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ካምፕ ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የእርዳታ ድርጅቶች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሥራ ማቋረጣቸውን ሮይተርስ እና አጃንስ ፈራንስ ፕሬስ የተባበሩት መንግሥት አስቸኳይ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ጠቅሰው ዘግበዋል።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ በምትገኘውና የኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ባለች ደደቢት ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት መሆኑንም የእርዳታ ሠራተኞቹ መናገራቸው ይታወሳል።

የመድኃኒት፣ የነዳጅ እና የሌሎች መሠረታዊ ቁሶች እጥረት፤ "ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለሚደረገው ምላሽ እክል እየሆነ ነው" ብሏል የመንግሥታቱ ድርጅት የአስቸኳይ እርዳታ ተቋም የረድኤት ድርጅቶቹ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራቸውን ማቋረጣቸውን ባስታወቀበት መግለጫ።

ኦቻ ስለእርዳታ ሥራው መቋረጥ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ለሮይተርስ የዜና ወኪል በሰጠው ምላሽ "የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ አጋሮች በአካባቢው ባለው የድሮን ጥቃት ስጋት እንቅስቃሴያቸውን ለጊዜው አቋርጠዋል" ብሏል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ጋብ ያለ ቢሆንም ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች እንዳጋጠሙ የመንግሥታቱ ድርጅት ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ጎረቤት አገር ኤርትራ በኃይሎቻቸው ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን፣ አስካሁን ከኤርትራም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥታት በኩል ስለሁኔታው የተባለ ነገር የለም።

የኤርትራ ኃይሎች ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው አማጺያኑን መውጋታቸው ይታወሳል።

የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ሄንሪኢታ ፎር

የፎቶው ባለመብት, UNICEF

የምስሉ መግለጫ, የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ሄንሪኢታ ፎር

'ጥቃቶቹ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ጥሰት ጋር ሊስተካከ ይችላሉ'

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው እና ለተፈናቃዮች መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን አለማክበር እና ከጥቃት አለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ጥሰት ጋር ሊስተካከል ይችላል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ተጠልለው በሚገኙባቸው መጠለየ ጣቢያ ላይ የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸው የሚመሩትን ድርጅት እንዳሳዘነ ገልጸዋል።

"የታኅሣሥ 27 እና 29 ጥቃቶች ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን መግደሉን እና ማቁሰሉን ሪፖርት ተደርጓል" ብለዋል።

ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የስደተኛ ጣቢያዎች እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰፈሩባቸው ቦታዎች እንዲሁም ለተፈናቃዮች መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሲቪል ቦታዎች ናቸው ካሉ በኋላ፤ እነዚህን ስፍራዎች "አለማክበርን እና ከጥቃት አለመጠበቅ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ይሆናል" ብለዋል።

ሄንሪታ ፎር 14 ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ በክልሉ በሕጻናት ላይ ጨምሮ መጠነ ሰፊ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል ብለዋል።

የሕጻናት አድን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተቋማቸው ግጭት እንዲቆም ዳግም ይጠይቃል ብለዋል ትናንት ባወጡት መግለጫ።

ዋና ዳይሬክተሯ የጦርነቱ ተሳታፊዎች፤ "ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን፣ የስደተኛ ሕጎችን እንዲያከብሩ እና የሰብዓዊ እርዳታ ሥራውን እንዲያስተባብሩ እንዲሁም ሕጻናትን ከጉዳት እንዲጠብቁ" ዩኒሴፍ ይጠይቃል ብለዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱ የተነገረ ሲሆን በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከ9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።